1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ሕብረት፤ ቱርክና ስደተኞች

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2008

ከሊባኖስ ሕዝብ 20 ከመቶዉ የሶሪያ ስደተኛ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የሊባኖስን ያክል ስደተኛ ለማስተናገድ ቢፈቅድ ኖሮ መቶ ሚሊዮን ስደተኛ አዉሮጳ በሠፈረ ነበር። ዓለም ግን እንዲሕ ናት።

https://p.dw.com/p/1ID24
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የአዉሮጳ ሕብረት፤ ቱርክና ስደተኞች

የአዉሮጳ ሕብረት እና ቱርክ ባለፈዉ ሳምንት ካደረጉት ሥምምነት ቱርክ፤ ፖለቲካዊም፤ ምጣኔ ሐብታዊም፤ ሥልታዊ ተፈላጊነትንም አትርፋለች።ከመሸበር ግን አልዳነችም።የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግስታትም ስደተኞች ወደየግዛቶቻቸዉ እንዳይገቡ ለማገድ ጠቅሟቸዋል።«ለሰብአዊ መብት ቆመናል» የሚል መርሐቸዉን ግን በጅግ ሸርሽሮታል።ከሽብር፤ ጦርነትና ጭቆና የሚሸሸዉ ስደተኛ አንደ ሸቀጥ አንዱ በሌላዉ መለወጥ፤በማይፈልገዉ ሥፍራ፤ ለማያዉቀዉ ጊዜ መከማቸት ግዱ ነዉ።የስምምነቱን ምንነት፤ከበጎ መጥፎ ዉጤቱ እንዴትነት ጋር አሰባጥረን እንቃኛለን ።

ቱርክን ከገሚስ ዓለም ገዢ፤ ልዕለ ሐያል ሐገርነት ወደ «ተመፅዋችነት» አሽቀንጥሮ የጣለዉ የዛሬዋ ዓለም አድራጊ-ፈጣሪ የጦር ጥቃት፤የፖለቲካ ግፊትና ሴራ ብቻ አይደለም።ከአረቦች ሻጥር እስከ ገዢዎችዋ ሥሕተት፤ ከዘመናዊ ዕዉቀት ማነስ፤ ሕዝቧን የማስተባበር አቅም እስከ ማጣት የሚደርሱ አያሌ አካባቢያዊ፤ማሕበረዊ-ፖለቲካዊ፤ ሐይማኖታዊ እና ወቅታዊ እዉነቶች ተጨማሪ ሰበብ ምክንያቶች ነበሩ።

1930ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በቀድሞዋ ሐያል ሐገር ፍርስራሽ ላይ ዘመናዊቷን ሪፕብሊክ የመሠረቱት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ እና ተከታዮቻቸዉ ቱርክ የቀድሞ ዋና «ጠላቶችዋን» የምዕራባዉያንን ፖለታካዊ፤ባሕላዊ፤ትምሕታዊ ፈለግና አስተምሮ እድትከተል ቀየሱ እንጂ ሌሎች የወድቀቷ ሰበቦችን ለማስወገድ ብዙም የተከሩት የለም።

ሐይማኖትዋ እስልምና-ማሕበራዊ ፍልስፍናዋ-ግን ምዕራባዊ፤ ጎረቤቶችዋ ሙስሊም-ፅሁፍዋ ግን ላቲን፤ ሕዝቧ ቅይጥ-መንግሥቷ ሪፕብሊክ፤እነ ጄኔራል አታቱርክ የወጡበት ጦርዋ ፖለቲካዉን መዘወር የሚሻ ጠንካራ-ፖለቲካዊ ሥርዓትዋ ግን ዴሞክራሲ፤ ምጣኔ ሐብቷ ደካማ-ታሪኳ ግን ገናና ሆኖባት ግራ-ቀኝ የምትላጋዋ ቱርክ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመንን ምዕራባዉያንን ሙጥኝ እንዳለች ተሻገረችዉ።

Libanon Flüchtlinge in Bar Elias Camp
ምስል Getty Images/AFP/H. Jarrah

የሶቬት ሕብረትን እና የቻይናን ተፅዕኖና መስፋፋት ለመግታት የአሜሪካኖችን ኒዉክሌር አወንጫፊ ሚሳዬል፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮችን፤ የምዕራባዉያን የሥለላ መረብን ለረጅም ጊዜ አስተናጋዳለች።ዛሬም እያስተናገድች ነዉ።ምዕራቡ ዓለም ግን ከኔቶ አባልነት ዉጪ፤ የአንድም ድርጅቱ፤ ማሕበሩ፤ ወይም ተቋሙ አባል እንድትሆን አልፈቀደላትም።

1949 የአዉሮጳ ምክር ቤት የተሰኘዉ ማሕበር ሲመሠረት ከመስራቾቹ አስር ሐገራት አንዷ ነበረች።ኋላ የአዉሮጳ ሕብረት የሆነዉ የአዉሮጳ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (EEC) አባል ለመሆን ያመለከተችዉ በ1987 ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የቀድሞ ኮሚንስት ትናንሽ ሐገራትን በአባልነት ሲያግበሰብስ ቱርክን እስካሁን አባሉ ማድረግ አልፈቀደም።29 ዓመቱ።

ባለፈዉ ሳምንት የሕብረቱ አባል ሐገራት መሪዎች እና የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር ባደረጉት ሥምምነት እንኳ ሕብረቱና ቱርክ ገና ለድርድር ዝግጅት ያደርጋሉ እንጂ-ቱርክ የሕብረቱ አባል የመሆን ሕልሟ-አሁንም ሕልም፤ የመደራደር ጉጉትዋ አሁንም ሩቅ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ቱስክ የ29 ዓመቱን ምኞት በአጭር አረፍተ ተነገር ጠቀለሉት።

«ለመቀራረቡ ድርድር አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት መዘጋጀት።» ብለዉ።ለሱም ቢሆን ተቃዉሞ አለበት።ሕብረቱ ከቱርክ ጋር ድርድር ከጀመረ የግሪክ ቆጵሮስ ድርድሩን ትቃወማለች።እንዲያዉም የግሪክ ቆፕሮስ ፕሬዝደንት ኒኮስ አናስታሲያዶስ ፤ ሕብረቱና ቱርክ ባለፈዉ ሳምንት ያደረጉትን ስምምነት በፊርማቸዉ የሚፀድቁበትን ጉባኤ ረግጠዉ እንደሚወጡ ዝተዋል።የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ሕብረቱ ከቱርክ ጋር ድርድር ከጀመረ የግሪክ ቆጵሮስን ማስቀየሙ እንደማይቀር ተናግረዋል።

«ሁለተኛ፤ ቱርክ ከዚሕ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳለችዉ ሁሉ፤ አሁንም (የሕብረቱ) አባል ለመሆን ድርድር እንዲጀመር ትፈልጋች።ይሕ በርግጥ ለቆጵሮስ የሚስማማ አይሆንም።»

በዚሕም ብሎ በዚያ ቱርክ ብዙ አተረፈችበት የተባለዉ የበቀደሙ ሥምምነት እንኳ ከ1930ዎቹ ጀምሮ እንደ ምሳሌ የምትከተለዉ፤የምትጠጋዉ፤ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት በታማኝነት ያገለገለችዉ ምዕራቡ ዓለም አባል እንደ አቻ አካሉ ሊቀበላት ምንም ፍንጭ አላሳየም።

ይሁንና መንታ አንዳዴም ተቃራኒ ሥልት በመከተሉ የተካነዉ ሐያል ዓለም ባንድ በኩል ኩርዶችን እያስታጠቀ በሌላ በኩል ከቱርክ ጋር መስማማቱ ለኩርዶች ታላቅ ሥጋት ነዉ የሆነዉ።እስካሁን ድረስ የኩርዶችን መብት፤ ትግልና ጥያቄ ትደፈልቃለች የምትባለዉ አንካራ «አሸባሪ» በምትላቸዉ የኩርድ አማፂያን ላይ የምትወስደዉን እርምጃ እንድትቀጥል ካሁኑ ስምምነት ላቅ ያለ «ነፃነት » አትርፋበታለች።

Bildergalerie Flüchtlingskinder Situation in Griechenland
ምስል DW/R. Shirmohammadi

ትርፉ ቢቀር እንኳ ለወትሮዉ በኩርዶች ላይ የምትወስደዉን እርምጃ አንዴ «የሠብአዊ መብት ጥሰት» ሌላ ጊዜ «የብሔር ጭቆና» እያሉ ከሚያወግዟት ትላልቅ ተቋማት አንዱን፤ የአዉሮጳ ሕብረትን የሞራል ነፃነትን የበቀደሙ ስምምነት ሸብቦላታል።በተቃራኒዉ ግን ሥምምነቱን የሚቃወሙት የኩርድ ደፈጣ ተዋጊዎች የአንካራ መሪዎችን «ስስ ብልት« እየፈለጉ ማስደንገጡን ያጠናከሩ ነዉ-የሚመስለዉ።

ስምምነቱ በፊርማ የሚፀድቅበት ዕለት ሲጠበቅ ትናንት የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ (PKK) አንካራን ዳግም ባሸበረ የቦምብ ጥቃቱ ሰላሳ-ሰባት ሰዉ መግደሉ የፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኻንን መንግሥት ከማስደንገጥ ባለፍ ሌላ ትርጉም አልተሰጠዉም።በስምምነቱ መሠረት ቱርክ ከግሪክ የሚጠረዙ ስደተኞችን እንድታሰፍር የጠየቀችዉ ገንዘብ ለአንካራ መንግሥት ሌላ ጥቅም ነዉ።እርግጥ ባለፈዉ ሳምንት በተደረገዉ ጉባኤ ላይ የተካፈሉት የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር አሕሜት ዲቫቱጉሉ የአዉሮጳ ሕብረት ለመስጠት ቃል የገባዉ 3 ቢሊዮን ዶላር በሙሉ ለሶሪያ ስደተኞች እንደሚዉል በአፅንኦት ተናግረዋል።

«3 ቢሊዮኑ ዩሮ ለሶሪያ ስደተኞች እንጂ ለቱርክ እንደማይሰጥ በግልፅ ተወስኗል።ላሰምርበት እፈልጋለሁ፤ ይሕ 3 ቢሊዮን ዩሮ ለቱርክ የሚሰጥ አይደለም።ለሶሪያ ስደተኞች ነዉ አንድም ዩሮ ለቱርክ ዜጋ አይሰጥም።»

ይበሉ እንጂ መንግሥታቸዉ ሌላ ሰወስት ቢሊዮን ዩሮ እንዲሰጠዉ ጠይቋል።ሥምምነቱን የሚፈርመዉም ሕብረቱ ባጠቃላይ ስድት ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ሲፈቅድ ብቻ ነዉ።የመጀመሪያዉ ሰወስት ቢሊዮን ለሶሪያ ስደተኞች ከዋለ የሚቀጥለዉ ሰወስት ቢሊዮን ለቱርክ መዋሉ የማይቀር ነዉ።ሌላዉ ቱርክ ከስምምነቱ ያተረፈችዉ የቱርክ ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ አዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት እንዲገቡ ማስፈቀድዋ ነዉ።

Symbolbild EU Türkei Beitritt
ምስል picture alliance/chromorange/Bilderbox

ሕብረቱ ከስምነቱ ካተረፋቸዉ በርካታ ጉዳዮች አንዱ በስደተኞች ሰበብ በአባል መንግሥታት መካከል የተፈጠረዉን ልዩነት ማጥበቡ ነዉ።ሁለተኛዉ ከ2005 ጀምሮ ወደ ሕብረቱ አባል ሐገራት ስደተኞች እንዳይገቡ ለመገደብ ያደረገዉ ጥረት ሁነኛ ዉጤት ማግኘቱ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወደ ግዛቱ እንዳይገቡ በ2011 ከያኔዉ የሊቢያ አምባገነን ገዢ ጋር ተስማምቶ ነበር።

በስምምነቱ መሠረት ለሊቢያ ጠቀም ያለ ርዳታ ሲሰጥ የሊቢያ ጠረፍ ጠባቂ ወታደሮችን ሲያሰልጥንም ነበር።የቃዛፊ መንግሥት በተወገደ ማግሥት የተቋቋመዉ የሽግግር መንግሥትም የቃዛፊ መንግሥት ያደረገዉን ሥምምነት እንዲያከብር ሕብረቱ ቃል አስገብቶት ነበር።ግን ቃሉም፤ መንግሥቱም በነኑ።

የሊቢያ መንግሥት ሲፈርስ የአፍሪቃ ስደተኞችን በየሚነሱበት ሐገር ለማገድ ሕብረቱ በጋራ፤ ጀርመንን የመሳሰሉ ጠንካራ አባላቱ ደግሞ በተናጥል ከሞሮኮ እስከ ኤርትራ፤ ከኢትዮጵያ እስከ አልጄሪያ ከሚገኙ መንግሥታት ጋር ተስማምቷል።ለየመንግሥታቱም ጠቀም ያለ ገንዘብ ለመክፈል ቃል ገብተዋል።አሁን ደግሞ ከቱርክ ጋር ተስማማ።«ጨዋታዉን ለዋጭ» አሉት የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዠን ክላዉድ ዩንከር

«ይሕ እዉነተኛ ጨዋታ ለዋጭ ነዉ።ጥሩ ሥምምነት ነዉ። ምክንያቱም በብዙ መልኩ ጠቃሚ ነዉ።ለማድረግ ያቀድነዉን በማድረግ በሰዎች ስቃይና ሰቆቃ የሚያተርፉ የሰዉ አዘዋዋሪዎችን ንግድ እንሰብራለን።በተጨማሪም ወደ አዉሮጳ መግቢያዉ መንገድ ሕጋዊዉ መስመር ብቻ መሆኑን እናረጋግጣለን።የሶሪያ ስደተኞች ከእንግዲሕ በአግያን ባሕር በኩል ለሚያሻግሯቸዉ ወንጀለኞች ማበረታችያ ገንዘብ መክፈል አይኖርባቸዉም።ይሕን ማድረግ እናንተን (ስደተኞቹን) ወደ ቱርክ ለመመለስ የሚያስገድድ ብቻ ሳይሆን ወደ አዉሮጳ እንዲገቡ ከሚፈቀድላቸዉ ስደተኞች የመጨረሻዉ ያደርጋችኋል።»

የዩንከርን ንግግር በቅጡ ላጤነዉ ቱርክ ዉስጥ መቆየት ለስደተኞቹ ምን ያሕል መጥፎ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነዉ።የዩንከርን ንግግር በቅጡ ያስተነተነ ድግሞ ከሠርቢያ እስከ አፍቃኒስታን፤ ከሊቢያ እስከ ዩክሬን፤ ከኢራቅ እስከ ሶሪያ ጦር የማዝመት አቅም ያለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ስደተኛ አዘዋዋሪ ደላሎችን መቆጣጠር አልቻለም የሚያሰኝ ነዉ።

የዩከር ንግግር ጠንካራዉ፤ ሐብታሙ፤ ለመብት መከበር የቆመዉ ማሕበራቸዉ ጦርነት፤ ሽብርና ጭቆና ያሰደደዉ ሕዝብ ከአዉሮጳዉያን ጋር እንዳይቀላቀል ማገዱን በግልፅ የሚያረጋግጥ ነዉ።በስምነቱ መሠረት የአዉሮጳ ሕብረት ከግሪክ አስገድዶ ወደ ቱርክ በሚመልሰዉ በእያንዳዱ ስደተኛ ምትክ ቱርክ ዉስጥ ከሰፈረዉ ስደተኛ ተለዋጭ ስደተኛ ወደ አዉሮጳ ያስገባል።ሰዉ በሰዉ ይለወጣል።ልዉዉጡ በምን አግባብ ይደረጋል? አይታወቅም።የሚታወቀዉ ፕሮ አዙል የተሰኘዉ የጀርመን የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት መሪ ካርል ኮፕ «ፌዝ» ማለታቸዉ ነዉ።

«ስደተኞችን ከቱርክ ወደ አዉሮጳ በሕጋዊ መንገድ ለመዉሰድ ማለት ሰዎችን ዳግም አዉሮጳ የማስፈር መርሐ-ግብሩን እንደግፋለን።ይሕ ግን አንዱ ስደተኛ በሌላ መለወጥ የለበትም።የአንዱ የጥገኝነት መብት ለሌላዉ መሰጠት የለበትም።ሰዎችን በጅምላ ወደ ቱርክ መመለስ አንችልም።ስደተኞች ወደ ቱርክ ተጠርዘዉ በተጠረዘዉ በያንዳዱ ሶሪያዊ ስደተኛ ምትክ ሌላ ስደተኛ ከቱርክ ማምጣት? ይሕ በርግጥ (ሰዉን) መያዢያ ማድረግ ነዉ።ፌዝ ነዉ።»

EU Sondergipfel Türkei in Brüssel
ምስል Reuters/Y. Herman

ለአዉሮጳ መንግሥታት ዋና ዓላማ የባልካን መሥመር በሚባለዉ መንገድ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ መግባታቸዉ መቆሙ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት ድንበርም የሕብረቱ አባል ከሆነችዉ ከግሪክ ዝቅ ብሎ አባል ያልሆነችዉ ቱርክን ከሶሪያ በሚያዋስነዉ ግዛት ላይ መዘጋቱ ነዉ።

የአዉሮጳ ሕብረት ከአምስት መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለዉ።የነብስ ወከፍ ገቢዉ 27 ሺሕ ዶላር ነዉ።ባለፈዉ ዓመት ወደ አዉሮጳ የገባዉ ስደተኛ የሶሪያ፤የአፍቃኒስታን፤ የአፍሪቃ ሁሉም ተቆጥሮ ከአንድ ሚሊዮን ጥቂት የሚበልጥ ነዉ።ከአዉሮጳ ሕብረት ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር 0.2 ከመቶ ማለት ነዉ። በየመቶዉ አዉሮጳዊ 0.2 ስደተኛ ማስተናገድ ከብዶትአዉሮጳ በስደተኞች ተጥለቀለቅች»«የስደተኞች ጎርፍ»፤ ስደተኞችን የሚቃወሙ ወገኖች ቁጣ፤ እየተባለ ሲወራ-ዓመት ሔዶ ሌላ አመት መጣ።

Brüssel EU-Türkei Gipfel- Angela Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/O. Hoslet/Pool

ቱርክ አጠቃላይ ሕዝቧ 75 ሚሊዮን ነዉ።የነብስ ወከፍ ገቢዋ 9 ሺሕ ዶላር።እስካሁን ድረስ አዉሮጳ ከገባዉ ስደተኛ ሰወስት እጥፍ ያሕል የሶሪያ ስደተኛ ታስናግዳለች።ሰወስት ሚሊዮን ግድም።ከሊባኖስ ሕዝብ 20 ከመቶዉ የሶሪያ ስደተኛ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የሊባኖስን ያክል ስደተኛ ለማስተናገድ ቢፈቅድ ኖሮ መቶ ሚሊዮን ስደተኛ አዉሮጳ በሠፈረ ነበር። ዓለም ግን እንዲሕ ናት።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ