ብራቲስላቭ-የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ
ዓርብ፣ መስከረም 6 2009ማስታወቂያ
ብሪታንያ ከሕብረቱ አባልነት ለመዉጣት ከወሰነች በኋላ የተቀሩት የሕብረቱ አባል መንግሥታት የሕብረቱን አንድነት ጠብቀዉ የሚቀጥሉበት ሥልት የየሃገሩን ፖለቲከኛ እያነጋገረ ነዉ። የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጉባኤዉ ከመጀመሩ በፊት እንዳሉት ሕብረቱ አንድነቱን ከማጠናከር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች አሉበት። ይሁንና ሜርክል አክለዉ እንዳሉት የዛሬዉ ጉባዔ ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሔ መስጠት አይችልም። «አዉሮጳ ያለባትን ችግሮች በሙሉ በአንድ ጉባዔ ማስወገድ አይቻልም። አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ነን። የዉጪና የዉስጥ ፀጥታ ጥበቃ ያሳስበናል።አሸባሪነትን በመዋጋትና በመከላከያ መስክ መተባበር፤ የኤኮኖሚ እድገትና የስራ ዕድል ፈጠራ ይበልጥ በማጠናከሩ መስክ ብዙ መስራት አለብን።»
የፈረንረንሳዩ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድም የሜርክልን ሐሳብ ተጋርተዋል።ኦሎንድ እንደሚሉት የብሪታንያ ከአባልነት መዉጣት ከባድ ፈተና ቢሆንም ሕብረቱ ሌሎች ፈተናዎችን እንደተወጣ ሁሉ ይኸኛዉንም መወጣቱ አይቀርም።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ