1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ በረከትሥልጣን መልቀቅና የመንግሥት ተቃውሞ

ዓርብ፣ ጥቅምት 10 2010

የአቶ በረከት ስምዖን የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ እና በኢትዮጵያ የኦሮሚያ አካባቢዎች የቀጠለው ተቃውሞ ዋነኞቹ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ርእሰ-ጉዳዮች ናቸው። የአቶ በረከት ስምዖን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ የተሰማው የአፈጉባኤው የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ ቀለም ሳይደርቅ ነበር። ዜናውን ወዲያው ነበር የመነጋገሪያ ርእስ የኾነው።

https://p.dw.com/p/2mCst
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የአቶ በረከት ስምዖን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ የተሰማው የአፈጉባኤው የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ ቀለም ሳይደርቅ ነበር። የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዜናውን ወዲያው ነበር የመነጋገሪያ ርእስ ያደረጉት። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ጋብ ብሎ የቆየው የመንግሥት ተቃውሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ እና በተለይ በኢትዮጵያ ምዕራባዊ አካባቢዎች እንደ አዲስ ተባብሷል።

የባለሥልጣናቱ መልቀቂያ

ሳምንቱ የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት የተነገረው የአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ጉዳይ ሳይደበዝዝ ሌላ ተጨማሪ አስደማሚ ነገር ይዞ ብቅ በማለት ነበር። ከመንግሥት ሥልጣናቸው ለመነሳት ጥያቄ ያቀረቡት የዚህ ሳምንት ባለተራ አቶ በረከት ስምዖን ኾነዋል። 

ብሩክ ተስፋዬ በትዊተር ገፁ፦ «አባዱላ እና በረከት ስምዖን በጥቂት ቀናት ልዩነት ሥልጣን መልቀቃቸው በጠቅላይ ሚንሥትር ደሳለኝ እና በዙሪያቸው የምር ውሳጣዊ ቀውስ እንዳለ አመላካች ነው» ሲል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፏል። 

አቶ በረከት ቀድሞ ከነበራቸው ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን እየተንሸራተቱ በስተመጨረሻ በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚንሥትር ተብለው ነበር። ከዚህ ሥልጣናቸው ለመነሳት ጥያቄ ከማቅረባቸው ቀደም ሲል «ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ኃላፊነት ተነሱ» የሚለው ዜናም በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቶ ነበር። 

ተስፋዬ ወልደየስ በትዊተር ገጹ፦ «እረ ባባጃሌዉ! 'ፖሊሲ ምርምር' በባንዲራዉ ቀን ይለቀቃል እንዴ?  ሲያልቅ አያምር» ሲል ተሳልቋል።  አቶ በረከት ስልጣን ለመልቀቅ የጠየቁበት ጊዜ «9ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን» በሚል መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ቀኑን እያከበረ ነበር። 

Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የአቶ በረከት የሥልጣን መልቀቂያ

«አቶ በረከት ስምኦን የከፍታ ዘመን ብሎ ሳይጨርስ ወርዶ ተፈጠፈጠ ምነው እንደዚህ ባቡሩ ፈጠነ ጎበዝ?» ሲል ያጠየቀው ደግሞ ስቲቨን ሉዊ ነው በዛው በትዊተር ማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፍ። አቶ በረከት ሥልጣን ለመልቀቅ ለምን ጥያቄ እንዳቀረቡ ዝርዝር ማብራሪያ አልተሰጠም። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚንሥትሩ አቶ ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው የአቶ በረከት ስምዖን ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን በተመለከተ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦ «እኛም ከሚዲያ ነው የሰማነው» ብለዋል። የአቶ ነገሪ ሌንጮ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኾነው በኢሕአዴግ አመራር ጉልህ ስፍራ ስለነበራቸው አቶ በረከት ሥልጣን መልቀቅ አለማወቅ በኢሕአዴግ ዘንድ መናበብ ለመጥፋቱ ማረጋገጫ ነው የሚል አስተያየት በማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተነስቷል።

ድምጸወያኒ በትዊተር ገጹ፦«አንጋፋው የነጻነት ታጋይ በረከት ስምዖን በሚንሥትር ደረጃ ከነበረው ሥልጣን መልቀቁን መንግሥት አረጋገጠ» ሲል በመጻፍ ውሳኔውን «ለብዙዎች ያልተጠበቀ» ብሎታል። 

በእርግጥ በሚያዝያ ወር ላይ አዲስ ፎርቹን የተባለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ጋዜጣ አቶ በረከት ስምዖን «ቅሬታ» እንዳላቸው የሚያመለክት ጽሑፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር። ጽሑፉ፦ አቶ በረከት የምርጫ ማሻሺያን በተመለከተ ያቀረቡት ሐሳብ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱ እንዳስከፋቸው ይገልጣል። ከዚህ ጥቆማ ባሻገር አቶ በረከት ከሥልጣናቸው ለምን ለመነሳት ጥያቄ እንዳቀረቡ የሚገልጥ ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልተገኘም።  

ብዙዓየሁ ብዙአየሁ፦«ጥቂት ካልተንበረከኩት ጓዶች አንዱ ስለነበረው ታጋይ ጓድ በረከት ስምኦን!» ሲል የውዳሴ ጽሑፉን ይጀምራል። «በረከት ስምኦን እኮ ማንም ስለ ኢትዮጵያ ህዘቦች መሰረታዊ መብት መከበርና ስለ አማራ ህዘቦች ነፃነትና ክብር የሞቀና የተደላደለ መቀመጫ ላይ ሆኖ ለሆዱ፤ ሆዱ ያስፈለገውንና የጠየቀውን ሁሉ እያቀረበ አይደለም ስለ ህዝብ ተጠቃሚነትና ነፃነት የሞገተው የታገለው» በማለት የሚተነትነው ብዙዓየሁ በስተመጨረሻም፦«በረከት ራሱ የገነባውን ቤት ራሱ የሚያፈርስ ስላልሆነ ጠላትም መርዶህን ስማ፤ ወዳጅም ተረጋጋ። ጀግናው በረከትም መልካም የእረፍት ጊዜ ይሁንልህ» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል።

ብሩክ የሽወርቅ አሰፋ፦ «እኔ ከነዚህ ሰዎች ጀርባ የሆነ የተደበቀ ሴራ ይሸተኛል!!» ብሏል። መልካሙ ተሾመ በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ አቶ በረከት ስምዖን ከሥልጣን የተነሱበትን ምክንያት ገምቶ እንዲህ ጽፏል። «ኢህአፓ ፣ህወሃት ፣ኢህዴን ፣ብአዴን ቤቶቹ ነበሩ። የጆሴፍ ጎብልስ አድናቂና ደቀመዝሙር ነው» ሲል ይንደረደራል መልካሙ። ጆሴፍ ጉብልስ በጀርመን ናዚ አገዛዝ ወቅት የሒትለር የፕሮፖጋንዳ ሚንሥትር ኾኖ የሰራ ሌላ የናዚ አባል ነው።  

Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

መልካሙ ስለ አቶ በረከት የጀመረውን ጽሑፍ ማብራራት ይቀጥላል። «አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ድቅል ቲዬሪ አለ ብለው ለማስረዳት ከሞከሩት ወይም ሳይኖር ሊያስኖሩት ከደከሙት ጥቂቶች አንዱ ነው። የዘር ሀረጉን ከናቅፋ ተራሮች የሚመዝዘው በረከት ስምኦን የማይቀረውን በመቀበል ስሌት ስልጣኑን መልቀቁ ተሰምቷል። ማረፊያው የት ይሆናል? የመልቀቂያ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? የመልቀቁ አንድምታዎችስ ምን ይነግሩናል? ፍንጭ፦ የስምኦን ልጅ በረከት በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ አደራዳሪ፣ ተንታኝ፣ ሸምጋይ፣ ጣፊ ሆኖ ሊከሰት ይችላል» ሲል ጽሑፉን አጠናቋል። 

እንደ አዲስ የተቀጣጠለው የመንግሥት ተቃውሞ

ሌላው በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከኾኑ ርእሰ ጉዳዮች መካከል በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል እንደ አዲስ የተቀጣጠለው የመንግሥት ተቃውሞ ይገኝበታል። ተቃውሞው በአዲስ አበባ ዙሪያ እና አቅራቢያ በሚገኙ ሱሉልታ እና ጫንጮን በመሰሉ ከተሞችም ታይቷል።

በዋትስአፕ ከደረሰን የጽሑፍ መልእክቶች መካከል፦ «በኦሮሚያ የተከሰተውን ሠላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ሰሞኑን በሁሉም ቀበሌዎች ምንም ችግር አልተፈጠረም እየተባለ ውይይት ላይ ነው ህዝቡ»  እንዲሁም «ሁሉን ለፈጣሪ ትተን ዝም ነው፤ ደሀው አለቀ በከንቱ» የሚሉ አስተያየቶች ይገኙበታል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ግጭትና ግድያ ማስተናገዳቸው «እንዳሳዘነው» በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በድረ-ገጹ ባወጣው ጽሑፉ ገልጧል። የኤምባሲውን መግለጫ በርካቶች «አስመሳይ» ሲሉ ተችተውታል።  ተስፋዬ ደሳለኝ በፌስቡክ ገጹ እንዲህ ሲል ትችት ሰንዝሯል። 

«ሰውን ያለ አገሩና ጭራሽ ያለ አሕጉሩም ሄዶ የሚገድለው የአሜርካ መንግሥት ለእኛ በተለየ ሁኔታ አዝኖ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ቬንዝዌላ ላይ ለተካሄደና እነርሱ "የተጭበረበረ" ለሚሉት ምርጫ ምላሽ አሜሪካና ጭፍራዎቹ የአውሮጳ ኀብረት ማዕቀብ እንጥላለን ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የኬንያም ምርጫን በተመለከተ ሂደቱ ጥሩና ተአማኒ እንደነበር» የአውሮፓ ኀብረት መግለጡን ያተተው ተስፋዬ «በኋላ የኬንያ የፍትሕ ስርዓት በተቃራኒው ከሀቅ ጎን ቆሞ አሳፍሯቸዋል» በማለት ትችቱን አጠናቋል።

Äthiopien US Botschaft in Addis Abeba
ምስል U.S. Embassy/S. Dumelie

አንቱ ጥላሁን ደግሞ፦ «ስልቷን ቀይራ ምታስገድለንና ምትገለን ራሷ አሜሪካ ናት! በጭቁኑ ህዝባችን ላይ ለፈፀምሽዉ አረመኔያዊ ተግባርሽ ከፈጣሪ ዘንድ ዋጋሽን ትቀበያለሽ!» ሲል ምሬት አዘል ጽሑፉን አስፍሯል። 
ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ በበኩሉ፦ «አሜሪካ በጓዳ በር መግደያ ታቀብላለች። ፊት ለፊት ደግሞ አዛኝ መስላ ይጣራ ትላለች። እኩይ!» ብሏል። የተቃውሞ ሰልፉን ማን እንደጠራው እና እንደመራው ግን ግልጽ አይደለም።

ባለባጃጁ ወላድ እናቶችን ረጂ አሽከርካሪ

የዛሬውን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅንት መሰናዶ የምናበቃው ሰሞኑን አነጋጋሪ ጉዳይ ኾኖ በሰነበተውስ አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ ሰናይ ምግባርን የሚያንጸባርቅ መልእክት እናገኛለን። «ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም በነፃ አደርሳለሁ» የሚል መልእክት የባጃጅ ተሽከርካሪው ላይ ለጥፎ ስለሚንቀሳቀስ አሽከርካሪ ነው የሚያወሳው መልእክቱ። 

ጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው የባጃጅ አሽከርካሪ አቶ ማስረሻ አስተዋለ ይባላል። በተጠራ ጊዜ ከተፍ ብሎ ወላድ እናቶችን 24 ሰአት ለማገልገል ዝግጁ መኾኑን የተናገረውን ግለሰብ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በስልክ እንዳነጋገረው በመግለጥ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስተዋውቆታል። 

ይኽ ጽሑፍ ከባጃጅ ተሽከርካሪ እና አሽከርካሪው ፎቶግራፍ ጋር ተያይዞ በፌስቡክ እና በትዊተር ተሰራጭቷል። በርካቶች የግለሰቡን ደግነት እና ቅንነት በማወደስ ለብዙዎች አርዓያ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጽፈዋል። ሐገሬ ኢትዮ «እንደ ወንድማችን አይነት ቅን ሰዎችን ያብዛልን»  ሲል፤ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ይኽን የባጃጅ አሽከርካሪ ተግባር «ደግነት በተግባር ሲገለጥ» ሲል አወድሶታል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ