1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የደነገገዉን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሚያጠናክሩ ማብራሪያዎችን ይፋ ከተደረጉ ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸዉን መግለጽ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/2RROo
Ethiopia State of Emergency Merkel (picture alliance / AP Photo)
ምስል picture-alliance/AP Photo

Ulrich Delius on State of Emergency - MP3-Stereo

 

 የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፤ ይደረጋሉ የተባሉት መሻሻሎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትንታኔ ይፋ ሲደረግ በተቃራኒዉ መንገድ የሚጓዝ ነገር መኖር እንደሚያመላክት ነዉ የተጠቀሰዉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከዉጭ የሚሰራጩ የሽብርተኛ ድርጅቶች ልሳን ያላቸዉን መገናኛ ብዙሃን ማዳመጥ ያግዳል፤ የዉጭ ሃገራት ዲፕሎማቶችም ከዋና ከተማ አዲስ አበባ ዉጪ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ሳያሳዉቁ እንዳይወጡም ገድቧል።

ባልተጠበቀዉ የተቃዉሞ ማዕበል ምክንያት የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንድ ወገን የሲቪሉን ኅብረተሰብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ወንጀል ለማድረግ የሚሞክር መሆኑን የተጨቆኑ ሕዝቦች መብት የሚሟገተዉ የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድህሮተ ፎልከር ባልደረባ ዑልሪሽ ዴሊዩስ ይናገራሉ።

«በአንድ ወገን በኦሮሚያ የሚገኘዉን ሲቪል ሕዝብ ማንኛዉንም ዓይነት ተቃዉሞ ወንጀል ለማድረግ የሚሞክር ሲሆን ይህ ደግሞ የፖለቲካ ቀዉስን የሚፈታ ጥሩ መንገድ አይደለም። በዚያም ላይ ለምንድ ነዉ ተቃዉሞዎቹ የቀጠሉት፤ በቅርቡስ የተፈጠረዉ ምንድነዉ፣ እነዚህ ሰዎችስ እስካሁን ለምን በቁጣቸዉ ቀጠሉ፤ ለምንስ በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኙ ኩባንያዎችን አቃጠሉ ለሚለዉም ተገቢ ትንታኔ አይሰጥም። አሁን የምናየዉ ባለስልጣናት በገጠሩ አካባቢ የሚደረገዉን ነገር ለመደበቅም በዋና ዋና ጎዳናዎች አካባቢ የ25 ኪሎ ሜትር አደገኛ ቀጠና ተደንግጓል፤ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች በየአካባቢዉ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ለጋዜጠኞች ረዥም ጊዜናት ተቆጥረዋል ተንቀሳቅሰዉ መመርመር እንዳይችሉ ከተገደበ። ስለዚህ እራሳችንን ምንድነዉ የሚደብቁት ብለን እንጠይቃለን። ጋዜጠኞችም ሆኑ የመብት ተቆርቋሪዎች በገጠሩ አካባቢ ምን እንደተፈጠረ መነሻዉን እንዳይመረምሩ እንዲህ ያለ ጠንካራ ገደብስ ማድረግስ ያስፈልጋል ወይ እንላለን።»

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱን ሰላም እና ፀጥታ ስጋት ላይ የጣሉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመቆጣጠር የታለመ መሆኑን ይናገራል። በተቃዉሞ እንቅስቃሴዉ ወቅት የንፁሐን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ የግል ንብረቶችም በተቃዉሞ አድራጊዎቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለመሆኑ ፀረ መንግሥት ተቃዉሞዉ ምን ያህል ሀገሪቱን ወደ ትርምስ ይከታታል ብሎ መገመት ይቻላል? እንደገና ዴሊዩስ

«ቢያንስ የእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ናት የሚል ስሜት አለን ። ነገር ግን መንግሥት  የተደራጀ አሸባሪ ቡድን የሚያካሂደዉ እንቅስቃሴ ነዉ፤ ወይም ደግሞ የዉጭ ኃይሎ እንደ ኤርትራ ወይም ግብፅ ከጀርባዉ አሉ እንደሚለዉ ነዉ ብዬ አላስብም። ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ ግጭትነት ይሻገራል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ብሔራዊ ግጭት፤ ብሔራዊ ችግር ነዉ። ለምን እነዚህ ሰዎች ጎዳና ላይ ወጥተዉ ይቃወማሉ የሚለዉን ማሰብ አለባቸዉ። ከመንግሥት በኩል ለምን እነዚህ ሰዎች እንደተቆጡ የሚያስረዳ ተቸባጭ ትንታኔ ያለ አይመስለኝም። እናም ይህ ሀገሪቱን በቀጣይ ወራት እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ ሁኔታ ላይ ሊጥል የሚችል በብሔራዊ ደረጃ የመጣ ጥፋት ነዉ።»

Ulrich Delius
ምስል Gesellschaft für bedrohte Völker

ዑልሪሽ ዴሊዩስ እንደሚሉት ይህን መፃኢ ችግር ከወዲሁ ለማስቀረት አስፈላጊ የመፍትሄ መንገዶችን መፈለግ፤ የተመድም ሆነ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ምን እየተካሄደ እንደሆነ ጉዳዩን እንዲመረምሩ ማድረግ ወሳኝ ነዉ። ለምድነዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዉሞን ፈፅሞ የሚጠላዉ፤ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች የሚያካሂዱትን? ለሚለዉ ጥያቄ የዑልሪሽ ዴሊዩስ ምላሽ እንዲህ የሚል ነዉ፤

«ባለፉት ቀናት በተለይ በዋና ዋና የአማራ አካባቢዎች ኦሮሚያ ዉስጥ የተከሰተዉን በተመለከተ የመተባበር እንቅስቃሴዎች አይተናል። እናም ከዚህ ጠንካራ ገደብ ጀርባ ያለዉ ስጋት በእነዚህ አካባቢ የተነሳዉ ተቃዉሞ ወደሌላዉም የአማራ ክፍል ሊስፋፋ ይችላል የሚል ይመስለኛል። አሁን እኛ በምንነጋገርበት ሰዓት በአማራ ክልል ተፈላጊ በሆነችዉ ጎንደር ከተማ ላይ የሶስት ቀናት የስራ ማቆም አድማ መኖሩ ተሰምቷል። እናም ለዚህ መንግሥት በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ምክንያቱም በየጊዜዉ ለዓለም ፀጥታችን የተረጋጋ ነዉ እያለ ባለወረቶችን ለሚጋብዘዉ ለዚህ መንግሥት አስቸጋሪ ነዉ። አሁን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በተጠንቀቅ ላይ ናቸዉ፤ ከኢትዮጵያ ስለመዉጣትም እየተናገሩ ነዉ፤  እናም መንግሥት እጠብቀዋለሁ ብሎ በሚሞክረዉ ኤኮኖሚዉ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ