1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም እና አስተያየት

ረቡዕ፣ የካቲት 14 2010

የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር አንድን ማዉጣቱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አመለከቱ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በአዋጁ አፈጻጸም መመሪያ እቅድ ላይ በአዲስ አበባ ከፌደራል እና ከክልሎች የተዉጣጡ ከፍተኛ የጸጥታ አካላት ጋር ዉይይት ማድረጉም ተገልጿል። 

https://p.dw.com/p/2t6Ef
Äthiopien Siraj Fegesa
ምስል DW/Y.G.Egiziabher

የአዋጁ ዝርዝር መመሪያ ቁጥር አንድ ወጥቷል፤

30 አንቀፆች እንዳሉት የተገለፀው መመሪያ፣ እርምጃ የሚያስወስዱ ተግባራት፣ ክልከላዎች፣ የመተባበር ግዴታዎች እና ይህን ተላልፎ ሲገኝ የሚወሰድ እርምጃን እና እርምጃ የመውሰድ ስልጣን ስላለው አካል የያዘ ስለመሆኑ በመከላከያ ሚኒስትር  እና የኮማድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ መገለፁን ነዉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ያመለከቱት።  በአዋጁ ክልከላ ከተደረገባቸው መካከልም የማንነት ጥቃት መፈፀም፤ ከሽብርተኛ እና ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነቶችን ማድረግ፤ የመጓጓዣ እንቅስቃሴን ማወክ፣ የሕዝብ አገልግሎትም ሆነ የንግድ ተቋማትን መዝጋት፤ በትምህርት ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ማድረስ እንዲሁም የሕግ አስከባሪዎችን ማወክ፤ ያልተፈቀደ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባዎችን ማድረግ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጣረሱ» የተባሉ ተግባራትን በጥቅሉ እንደሚያግድ በተገለፀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነትም የሽብር እና የነውጥ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እና ሕገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሣሪያ ዝዉዉርን ባሉ ኬላዎች  ቁጥጥሩን ማጠናከሩ አስፈላጊ እንደሚሆንም ተጠቅሷል። እንዲያም ሆኖ ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፋፊ ዉይይቶች እንደሚደረጉ ተገልጿል።  መመሪያ ቁጥር አንድ በአመዛኙ ባለፈዉ ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ገደማ ተግባራዊ ተደርጎ ከነበረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ጋር ተመሳሳይነት አለው።  በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና  የድረገጽ ፀሐፊ አቶ ስዩም ተሾመ የአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ተደንግገው የነበሩ እገዳዎችን መልሶ ከማንሳቱ ዉጭ ምንም የተለየ ነገር ይዞ አልመጣም ይላሉ።

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

እንዲህ ያለዉ አዋጅም በሕዝብ መብት እና የሀገር ኤኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ በዋናነት በመንግሥት ላይ የሚያደርሰው አፍራሽ ተፅዕኖ እንደሚበረታም አመልክተዋል። የሕግ ባለሙያዉ አቶ ተማም አባ ቡልጉ በበኩላቸዉ የሕጉ ባለ 30 አንቀጽ መሆን በራሱ ያልተለመደ እንደሆነ አብራርተዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፈፃጸም መመሪያ መሠረት መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ ማዳረስን በተመለከተም ኮማንድ ፖስቱ በሚያቋቁመው የመረጃ ማዕከል አማካኝነት መዋቅሮች መዘጋጀታቸውም ተመልክቷል። ከፀጥታ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ከኮማንድ ፖስቱ ዉጭ መግለጫ መስጠት መከልከሉ አቶ ስዩም የክልሎችን ስልጣን እንደሚጋፋ ነው ያስረዱት።

ጠበቃ ተማምም እንዲሁ ለሕዝብ ምንም አይነት መብት የማይተው ነው ብለውታል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ የሰዓት ዕላፊ ገደብን ያደረገ ሲሆን በዚህ ረገድም የመሰረት ልማት፣ የኢንቨስትመንት አውታሮች እና መሰል ተቋማት አካባቢ ኮማንድ ፖስቱ ከፈቀደው ሰዓት እና ገደብ በስተቀር ማንኛውም ሌላ ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ አፅንኦት ሰጥቷል። የአዋጁ ዝርዝር አፈፃጸምም በቀጣይ እንደሚብራራ ነው የተጠቆመው። ስለ አዋጁ መግለጫ ያወጡ  የውጭ መንግሥታት አፅንኦት የሰጡት  አዋጁ ሀገሪቱ በሕገ መንግሥት ያጸደቀቻቸውን መሠረታዊ መብቶች እንዳይጥስ የሚለዉን ማሳሰቢያ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ