1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት

እሑድ፣ ነሐሴ 7 2009

ተቃዋሚዎች አዋጁ መነሳቱን ቢደግፉም የሐገሪቱን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት በቂ እርምጃ አይደለም ይላሉ። በሌላ በኩል አዋጁ ከተነሳ በኋላ እዚህም እዚያም የተለያዩ አድማዎች እየተካሄዱ ነው።

https://p.dw.com/p/2i62C
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ኢትዮጵያ ላለፉት 10 ወራት የደነገገችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ አንስታለች። የተነሳውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው የኮማንድ ፖስት ወይም የእዝ ጣቢያ ሃላፊ የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓም ለኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ ሀገሪቱ አሁን መረጋጋትዋን ካሳወቁ በኋላ ነበር። በኦሮምያ እና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሲካሄዱ የቆዩ ፣የ700 ያህል ሰዎች ህይወት የጠፋባቸው ተቃውሞዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ በኋላ በርካታ ክልከላዎችን ባካተተው በዚህ አዋጅ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። መንግሥት የአገሪቱን ህልውና እና የህዝቡን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ አወጣሁት ያለው አዋጅ የሕዝብን መብት የሚያፍን ከዓለም አቀፍ ህግጋትም ጋር የሚፃርር ነው የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል። አሁንም ተቃዋሚዎች አዋጁ መነሳቱን ቢደግፉም የሐገሪቱን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት በቂ እርምጃ አይደለም ይላሉ። በሌላ በኩል አዋጁ ከተነሳ በኋላ እዚህም እዚያም የተለያዩ አድማዎች እየተካሄዱ ነው። የአዋጁ መነሳት እና ፋይዳው የዛሬው እንወያይ ትኩረት ነው። በዚህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ አራት እንግዶችን ጋብዘናል እነርሱም አቶ ሙላቱ ገመቹ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምህፃሩ ኦፌኮ ሊቀመንበር ፣ዶክተር መሐሪ ረዳኤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምሕርት ቤት ተመራማሪ፣ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ የሰብዓዊ መብቶች ህግ ምሁር እና የዞን ዘጠኝ ድረ ገጽ አምደኛ እንዲሁም ዳንኤል ብርሀኔ የህግ ባለሞያ እና ሆርን አፌርስ የተባለew ድረ ገጽ አዘጋጅ ናቸው። በዚህ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ለማሳተፍ ሞክረን ነበር። ስልካቸውን ስለማያነሱ ልናገኛቸው አልቻልንም። ሙሉውን ውይይት የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ማዳመጥ ይችላሉ።

ኂሩት መለሰ

ልደት አበበ