1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምንስቲ ዓመታዊ ዘገባና ኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2009

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገዉ ዓመታዊ ዘገባ በመላዉ ዓለም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየጨመረ መሆኑን አመለከተ። ድርጅቱ በዓለም ላይ እየተለመደ መጣ ያለዉ ጥላቻን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ ሰብዓዊ መብት ላይ ያለዉን አሉታዊ ጫና ከፍ እንዳደረገዉም ዘርዝሯል።

https://p.dw.com/p/2Y9hm
Deutschland PK Amnesty International Report 2016/2017
ምስል DW/N. Jolkver

Amnesty Jahresbericht & Äthiopien /MMT - MP3-Stereo

 

በኬንያ የሚገኘዉ የምስራቅ አፍሪቃ ቢሮ፤ ባለፈዉ ዓመት በኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በኦሮምያ ክልል ለወራት በዘለቀዉ ተቃዉሞ የታየዉ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዳሳሰበዉ ገልጾአል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የድርጅቱ ዘገባ መንግሥትንና ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኝ ሕዝብን አስተያየት ያላማከል ነዉ ብሎታል።  

ባሳለፍነዉ ጎርጎረሳዊ ዓመት 2016 በበርካታ ሃገራት ከፍተኛ የመብት ጥሰት መታየቱን የሚያትተዉ የዘንድሮዉ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ዘገባ በተለይ በተለያዩ መንግሥታት ዘንድ ጥላቻ ላይ መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እየተስፋፋ መምጣቱን በግንባር ቀደምትነት አመልክቷል። ለዚህ ማሳያም በአሜሪካም ሆነ በአዉሮጳ ሃገራት መንግስታት ላይ የሚታየዉን የፖለቲካ አካሄድና የሥደተኞች ጉዳይ ጠቅሶአል። ከዚህም ሌላ አምነስቲ ተቃዉሞና ትችትን ያለመታገስ አዝማሚያዉ እየጨመረ መሄዱን የገለጠዉ የኢትዮጵያ መንግሥት በፀረ ሽብር ሕግ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲከኞችና በተለይ ደግሞ ለተቃዉሞ የወጡ ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀም መቀጠሉንም ዘርዝሯል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ እንደተናገሩት ባለፈዉ ዓመት ኢትዮጵያ ዉስጥ ረዘም ላለጊዜ በታየዉ ተቃዉሞ የተካሄደዉ የመብት ጥሰት ጉዳይ በዘገባዉ ተቀምጦአል።     

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣዉን ዘገባ ያጣጣሉት ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሰኢድ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቅድሚያ የሚሰጠዉ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነዉ ብለዋል።  የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሰኢድ የአምነስቲ ዘገባ የተሟላ አይደለምም ብለዋል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ በበኩላቸዉ የሰብዓዊ መብቶች ይከበራል በሚባልባቸዉ አገሮች ጥሰቶች እየጎሉ በመታየታቸዉ ጊዜዉ ለሰብዓዊ መብቶች የጨለመ መስሎአል፤ እንድያም ሆኖ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ