1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል «ግድያ »ይቁም መግለጫ

ዓርብ፣ ግንቦት 24 2010

የኢትዮጵያ መንግስት የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ በሰላማዊ ዜጎች  ላይ የሚፈፅመዉን  ግድያ ሊያስቆም ይገባል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት፣ አምነስቲ አንተርናሽናል ጠየቀ። ድርጅቱ  ትናንት  ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፓሊስ  በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን እየፈጸመ በመሆኑ

https://p.dw.com/p/2yoln
Logo von Amnesty International

Ethiopian government must disband the Liyu police unit of the Somali - MP3-Stereo

ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግ ተገዥ በሆነ የፖሊስ ሀይል መተካት አለበት ብሏል።ተገቢ ማጣራት ተደርጎም ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ድርጅቱ  አሳስቧል።
ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናል  በዘገባው እንዳመለከተዉ «ልዩ ሀይል»  እየተባለ የሚጠራዉ የሶማሌ ክልል ፖሊስ በሶማሌ ክልልም ይሁን በአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል «ሰዎችን ያለፍርድ በማሰቃየትና በመግደል ላይ ነዉ» በሚል  ድርጊቱን ኮንኗል።
የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ ሽብርተኝነትን በክልሉ ለመዋጋት በልዩ ሁኔታ የተቋቋመ ቢሆንም ከተመሰረተበት ዓላማ በተቃራኒ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ  እየፈፀመ መሆኑን የድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ልዩ ፖሊስ በተለይም በዚህ ሶማሌ ክልል ከአስር አመት በላይ ሆኖታል ከተቋቋመ።በዋነኛነት ሽብርን ለመዋጋት የተቋቋመ ነበር።እና ከዚያ ታሪኩ በሙሉ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል በማሰቃየት አስከፊ የሆኑ ወንጀሎችን በመፈፀም የሚታወቅ ነዉ።አሁን በቅርቡ ራሱ የኦሮሚያን ድንበር በማለፍ ጭክሰን ዉስጥ የነበሩ አምስት አርብቶ አደሮችን ረቡዕና ሀሙስ ገድሏል።ብዙ ቤቶችንም አቃጥሏል።»
ከዚህ በተጨማሪም የልዩ ሀይል  ፖሊስ  አባላት በዚህ ሳምንት ዉስጥም በሶማሌ ክልል የሚገኙ  48 የኦሮምያ ተወላጆችን ቤት ማቃጠላቸዉን ድርጅቱ  አመልክቷል። ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላም የአካባቢዉ ነዋሪዎች  ለደህንነታቸዉ በመስጋት አካባቢዉን ጥለዉ መሰደዳቸዉን ገልጿል።ስለሆነም  ይህንን  የጭካኔ ድርጊት የሀገሪቱ ባላስልጣናት ያስያቆሙት ዘንድ ድርጅቱ ጠይቋል።  እንደ ድርጅቱ  የሚደርሰዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የልዩ ሀይል ፖሊስ የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ህግ በሚያከብር የፖሊስ ሀይል መተካት አለበት።ይህ ሀይል የሰብዓዊ መብትጥሰቶችን እየፈፀመ  በመሆኑ ከስራ ዉጭ መደረግ አለበት ሲሉ አቶ ፍስሃ ተክሌ አብራርተዋል። 
«ይህ እንግዲህ ያዉ በቅርቡ መሆኑ ነዉ እንጅ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲፈጸም ነዉ የኖረዉ።የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል እስካሁን ድረስ ሀይ የሚለዉ አካል አልተገኘም።ግን በሶማሌ ክልልም ይሁን በአጎራባች ክልሎች ላይ የሚፈፀመዉ በደል አልቆመም።ስለዚህ ይህ ሀይል ለሰብዓዊ መብት ያለዉ አመለካከትና ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የሚያከብር ሳይሆን የሚጥስ በመሆኑ፤ከታሪኩ አንጻር መበተን ያለበት ሀይል ነዉ ብለን እናስባለን።» 
ፖሊስ የሰብዓዊ መብትን እንዲያከብር ማድረግ የመጀመሪያዉ የመንግስት ርምጃ መሆኑን  አመልክተዉ፤ የልዩ ሀይል የፖሊስ አባላት ፈፅመዉታል የተባለዉን  ወንጀልም  በነጻና ገለልተኛ ወገን ተገቢ ማጣራት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።በዚህም መሰረት መንግስት  ወንጀለኞቹን በህግ ተጠያቂ  ማደረግና ተጎጅዎችንም ይቅርታ መጠየቅ  አለበት  ሲሉ ተመራማሪዉ ገልጸዋል።
«በተለያዩ ጊዜያት የምንሰማቸዉ በሶማሌ ክልልም ይሁን በአጎራባች ክልሎች ላይ የሚፈፅማቸዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስፈላጊዉ ምርመራ ተካሂዶ ነፃና ገለልተኛ ታማኝ የሆነ ምርመራተካሂዶ ለዚያም ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ መቻል አለባቸዉ።ይህ ካልሆነ እንግዲህ ድርጊቱ እየቀጠለ ነዉ የሚሄደዉ።ምክንያቱም ሰዎች ወንጀል ፈፅመዉ ነፃ ሆነዉ የሚቀጥሉ ከሆነ በአንድም ይሁን በሌላ መልክ አያቆሙም። ስለዚህ ለድርጊቱ ሰለባዎችም መፍትሄና ካሳ ከመስጠት አንፃር ፍትህ ከመስጠት አንፃር፤ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸዉ።አስፈላጊዉ ካሳ ሊከፈል ይገባል።ለሰብዓዊ መብት ጥሰቱም «ኦፊሻላዊ» የሆነዕዉቅና ተሰጥቶት ይቅርታ እንዲጠየቅበት የሚገባ ነዉ።»በማለት ነበር አቶ ፍስሀ ያብራሩት።
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል  በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር 2017  ዓም በተከሰተዉ የድንበር ግጭት ሳቢያ  በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉን መፈናቀላቸዉን ድርጅቱ አስታዉሶ ፤ለሁለቱ ክልሎች ግጭት መንስኤ የሆነዉን የድንበር ዉዝግብ ለመፍታትም በጎርጎሮሳዊዉ  በ2004 ዓም የተካሄደዉን  የድንበር ማካለል ህዝበ ዉሳኔ የሀገሪቱ መንግስት ተግባራዊ እንዲያደርግ አምነስቲ ጥሪ አቅርቧል።
በጉዳዩ ላይ የመንግስት የኮምኒኬሽን ፅ/ቤት ሀላፊዎችን  ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም መልስ ልናገኝ አልቻልንም።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ