1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ወታደሮች ዳግም በሶማሊያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2009

የሶማሊያው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አልሸባብን ለመዋጋት ዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ብትጠቀምም ውጤቱ እምብዛም ነው እየተባለ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት ወታደሮቿን  ወደ ሶማሊያ መላኳን አስታውቃለች።

https://p.dw.com/p/2bWqi
US-Drohnen in Afghanistan
ምስል picture alliance/Pacific Press/A. Ronchini

Ber. DC. (US military in Somalia) - MP3-Stereo

ዩናይትድ ስቴትስ 101ኛው አየር ወለድ ብርጌድ አባል የኾኑ አርባ ወታደሮቿን  ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ ሶማሊያ መላኳን አስታውቃለች።  የአሜሪካ ወታደሮች የሶማሊያ ተልዕኮ የሶማሊያ መንግስት ወታደሮችን በማሠልጠን ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል። 101ኛው አየር ወለድ ብርጌድ ቀደም ሲል በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ተልዕኮ በስፋት መሳተፉ ይነገራል። ከሁለት ዐሥርተ ዓመት በፊት «ብላክ ሐውክ» የተሰኙ ሁለት ተዋጊ ሄሊኮፕተሮቿ ሞቃዲሾ ከተማ ውስጥ ተመተው ከወደቁ እና 18 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች  ከተገደሉ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮቿን  ከሶማሊያ ምድር ለማስወጣት ተገዳ ነበር። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሜሪካ ጥቂት የልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ ኃይላት እና ጸረ-ሽብር አማካሪዎችን ስትልክ ቆይታለች። የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተልዕኮውን ማስፋፋት እንደሚፈልግ ቀደም ሲል አስታውቋል። አሜሪካ የሶማሊያው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አልሸባብን ለመዋጋት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ብትጠቀምም ውጤቱ እምብዛም ነው እየተባለ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት  ነው 101ኛው አየር ወለድ ብርጌድ  አባላትን የላከችው።

ነዋሪነታቸው በዩናይትድ ስቴትስ የኾነ አንድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ለዶይቸ ቬለ በሰጡት አስተያየት፦ ሶማሌያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ እና አካባቢያዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርባቸው መፈለጋቸውን ተናግረዋል። አሜሪካ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሠላም ለማስፈን ከአካባቢው ሃገራት ጋር ሳይሆን  በቀጥታ ከሶማሊያ ሕዝብ  እና መንግሥት ጋር  መነጋገር እንዳለባት የሶማሊያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ይወተውቱ እንደነበርም ገልጠዋል።  

መክብብ ሸዋ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ