የንቅሳት ጌጥ በአፍሪቃዉ ቀንድ
የጥርሷ ንቅሳት ያንገቷ ሙስና ረቡዕ ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና። እንደ ፎገራ ላም አንገተ ዝንጉርጉር፣ መንገዱን አስታ ሰደደችን በዱር። አንገተ ንቅሳት መልከ ዉዳዉድ፣ ምን ትጠቀሚያለሽ አንቺን ብዪ ባብድ። የአንገቷ ንቅሳት ይመስላል ዝናር፣ እስዋን ያገኘ ወንድ ጀግና ነዉ የምር።
ንቅሳቷ ነዉ ዉበቷ
በተራራ ፍየል ይመስላል ሰርገኛ፣ የእገትዋ ንቅሳት አለዉ አማረኛ፤ ንቅሳትሽማ ልብ ያስደነግጣል፣ ከጀግናዉ ባለቤት ከተዋበች በልጦአል! ይባል ነበር። አሁን አሁን ንቅሳት ባህል ፤ በገጠሩ አካባቢ ካልሆነ እንደቀድሞ ጊዜ የሚነቀስ አለ ማለት ይከብዳል። ተነቅሳ የታየችም ሴት ከዘመናዮቹ አትቆጠርም። በገጠሩ አካባቢ አዳጊ የስምንት ዓመት ሕጻናት ሁሉ ተነቅሰዉ ይታያሉ። ተነቀሽ ተነቀሽ ተነቀሽ በሾክ፣ ትሆኝ እንደሆን የናትሽ ምትክ። ንቅሳትሽማ መቁጠርያ የሚመስለዉ፣ ያን ዉበትሽን አስበለጠዉ ከሰዉ። የግንባርሽ መስቀል የአንገትሽ ድርድር፣ ያኑራት ዘላለም ነቃሽን በምድር።
ገላን ማስዋብ
በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ንቅሳት የተለመደ ነዉ ። በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል ብዙ ሴቶች ግንባራቸዉን ጉንጫቸዉን አንገታቸዉን ድዳቸዉን ተነቅሰዉ እናገኛለን። የመንቀሻ መሳርያቸዉም ከትዉልድ ትዉልድ የሚተላለፈዉ ባህላዊ የመንቀሻ መሳርያ አጋም እሾህ፣ መርፊ፣ አልያም ወስፊ ይሆናል። ታድያ በባህላዊዉ ንቅሳት አምራ አጊጣ የባህላዊ ቀሚስዋን አጥልቃ ያየ ሰዉ ነቃሽዋንም ተነቃሽዋንም ያሞካሻል፤ በግጥም! ፎቶዉ ላይ የምትታየዉ ባለንቅሳት ሃና ትባላለች። ባህር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ግቢዉስጥ የተነሳችዉ ፎቶግራፍ ነዉ። የቤተ- እስራኤላዉያን ባህላዊ መስቀል ግንባርዋ ላይ ተነቅሳለች።
የሰዉነት ማስዋቢያ
ድሪዳዋ ከተማ ላይ ባለንቅሳትዋ ሴት ጫት በመሸጥ ላይ ናቸዉ። ሴቲቱ አገጫቸዉና ግንባራቸዉ ላይ በነጠብጣብ አይነት ነዉ የተነቀሱት። እንሶስላ የተባለዉ ተክል ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሰዉነት ማስዋቢያ በስፋት ይዉላል። በተለይ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ልጃገረዶችና ሴቶች እጅና እግራቸዉን እንሶስላ ይሞቃሉ። ለቁርጥማት ጥሩ ነዉ የሚሉም አይጠፉም። ንቅሳት ከአንድ የእድገት ደረጃ ወደ ሌላ መሸጋገርን፣ መአረግን ሃይማኖታዊ እና መንፈስነትን፣ ጀግንነትን ወሲባዊ መስብዕን፣ ወላድነትን ፍቅርን ቅጣትን እንዲሁም ከለላን አመላካች ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ማገልገሉ ይገለጻል፣ ንቅሳት የባሮች የእስረኞች መለያ ሆኖ ማገልገሉም አንዳንድ ጽሁፎች ያሳያሉ።
ሰዉነትን በእንሶስላና ሂና ማሳመር
እንደ እንሶስላ ሁሉ ሂናም ከጊዜ በኋላ የሚለቅ ከቅጠላ ቅጠል የሚሰራ የሰዉነት ቆዳ ማስጌጫ ነዉ። በኢትዮጵያ በጎረቤት ሶማልያና ጅቡቲ ዉስጥም እንሶስላና ሂና በስፋት ለቆዳ ማስጌጫ ይጠቀሙበታል። በፎቶ ላይ የምትታየዉ ወጣት በርበራ ከተማ ዉስጥ አንዲት ጠና ያሉት ሴት የእጅ ቆዳ በሂና ታሳምራለች። ለባለንቅሳትዋ ኢትዮጵያ እንዲህ ይገጠም ነበር ።« አየሁት ዉበትሽን ከእገትሽ በላይ፣ የዛ የጀግና ዘር የበላይ ነሽ ወይ። ድንቅ ነዉ ዉበትሽ ሲያዩት በትኩረት፣ ነቃሽ ነች እና ጠቢብ በእዉነት።»
የእጅና የእግር ጥፍርን በሂና ማሳመር
እግርና እጅን በሂና ማስዋብ በአፍሪቃ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በሰሜን አፍሪቃ ዉስጥ በሚገኙ ሃገራትና በአረብ ባህረ ሰላጤዉ ሃገራት እንዲሁም በቅርብ ምስራቅ ሃገራትና እስያ ዉስጥም የተለመደ ነዉ። ሴቶች በሂና እጅና እግራቸዉን፤ ብሎም የእጅና የእግር ጥፍራቸዉን ያሳምራሉ፤ ያስዉባሉ። ሰዉነትን በንቅሳት ማሸለም ከሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ወዲህ በዘመናዊ መልኩ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች እንደተስፋፋ ጽሁፎች ያመለክታሉ። በተለይ በሰሜን አሜሪካ በጃፓን በአዉሮጻ ዉስጥ ተወዳጅነቱ ጎልቶ ይታያል። የንቅሳት ባህል ሊስፋፋ የቻለዉ የቴክኒክ እና የሥነ-ጥበብ ስልጠና ያላቸዉ አዳዲስ ባለሞያዎች ወደ ዘርፉ በመግባታቸዉም እንደሆነ ተመልክቶአል።
ሂጃብ
የሶማሌላንድ መዲና በሆነዉ በሃርጌሳ ሃገሪቱ 25ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ባከበረችበት ወቅት በተለይ በሴቶች እና ልጃገረዶች ዘንድ ይታይ የነበረዉ ደማቅ የተለያዩ ቀለሞች ያልዋቸዉ ድርያ ያደረጉ ሴቶች በሂና የተሸለመ እጅ ላይ የተለያዩ ጌጦችን አድርገዉ ነዉ፤ ቆንጆ ሂጃብን አጥልቀዉ ነበር
በረመዳን ወቅት
በቅዱስ ረመዳን ጾም ወቅት ሴቶች የኢድ በዓልን ለማክበር ሲዘጋጁ በሰዉነታቸዉን በሂና ያሳምራሉ። ፎቶዉ ላይ የምትታየዉ ሃሚራ በሃርጌሳ በሚገኝ አንድ ባህላዊ ሆቴል ዉስጥ ትሰራለች። ሃሚራ በሂና ቆዳዋን ለማሳመር የፈጀባት 20 ደቂቃ ነዉ የከፈለችዉም ወደ አራት ይሮ ግድም ነዉ ። ሃሚራ በምትኖርበት አካባቢ ሴቶች በሰርግ እንዲሁም በበዓላት ወቅት ሰዉነታቸዉን በሂና ያስዉባሉ።
አወዛጋቢዉ ዘመናዊነት
በሃርጌሳ የ16 ዓመትዋ ናጂማ የቆዳ ማስዋብያ የተሰራዉ ከጥቁር «አባያ» ነዉ ። በሶማሌ ላንድ ሴቶች ሂጃብ ይለበሳሉ፤ እጅጌ ሙሉ ልብስም ነዉ የሚያደርጉት። ግን በርካታ ሕዝብ በማይገኝበት ቦታ ላይ ሴቶች አለባበሳቸዉ ፤ ብዙ ሕዝብ እንደተሰበሰበበት ሁሉ ወግ አጥባቂ አይነት አይደለም። እንደዉም «ሰዉ ራሱ ላይ የሚያስረዉ ነገር ሳይሆን ፤ራሱ ዉስጥ ባለዉ ይለካል» የሚል አነጋገርም አላቸዉ።
የጅቡቲዉ ንቅሳት
በጅቢቲና፤ በሰሜናዊ ሶማሌላንድ በሂና የሰዉነትን ቆዳ ማስዋብ የተለመደ ነዉ። በእነዚህ ሁለት አገራት የሚገኙ ማኅበረሰቦች ዘንድ ተመሳሳይ የሆኑ ባህልና ልማዶች ሲተገበሩ ይታያል። ይህች የጅቡቲ ተወላጅ ታዳጊ ሕጻን ከጓደኞችዋ ጋር ሆና 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሪድ ሙቀት በሚለካበት እለት ጅቡቲ ባህር ዳርቻ ላይ ተቀምጣለች።