1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኒኩሊየር የኃይል ምንጭነት ተቃርኖ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 2010

ለኃይል ምንጭነት ከሚዉሉ መካከል ኒኩሊየርን ለዚህ ማዋልን በተለያዩ ምክንያቶች የሚቃወሙት ይበረክታሉ። በተቃራኒዉ ኒኩሊየርን ለኃይል ምንጭነት መጠቀሙ ከባቢ አየርን ከብክለት በመታደግ ዘላቂነት ያለዉ የኃይል አቅርቦትን ሊያሳካ ይችላል በሚል የሚከራከሩለትም አሉ። ኒኩሊየርን በኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙ ጥቂት የማይባሉ የበለፀጉ ሃገራት አሉ።

https://p.dw.com/p/2pEtF
Belgien Atomreaktor Tihange 2
ምስል Getty Images/AFP/J. Thys

ደጋፊዎቹ ከብክለት ነፃ ሲሉት ተቺዎቹ አሳሳቢ ይሉታል፤

ፈረንሳይ አብዛኛዉን የኃይል ፍጆታዋን የምታመነጨዉ ከኒኩሊየር የኃይል ምንጭ ሲሆን ከ40 በመቶ ያላነሰ ከዚህ ዘርፍ እንደምታገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ፈረንሳይ ከራሷ ፍጆታ አልፋ ለጎረቤቶቿም በዚህ ዘርፍ ከምታመነጨዉ ኃይል እስከመሸጥ መድረሷም ይነገርላታል። ጀርመን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም 22,4 በመቶ ከኒኩሊየር ዘርፏ ኃይል ማመንጨት መቻሏ ቢመዘገብም፤ ፉኩሺማ ጃፓን ላይ የኑኩሊየር ኃይል ማመንጫዉ በተከሰተዉ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጉዳት ሲያስከትል ወዲያዉ ካሏት 17 የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫዎች ስምንት ያህሉን በቋሚነት ዘግታለች። ቀሪዎቹንም እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2036ዓ,ም ቀስ በቀስ እንደምትዘጋ አሳዉቃለች።  

ኒኩሊየር ፎር ክላይሜት መንግሥታዊ ያልሆነ ዋና መቀመጫዉን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ ድርጅት ነዉ። ድርጅቱ የፀሐይ ብርሃን እንደልብ ለማይገኝባቸዉ ሃገራት ኒኩሊየር ዋነኛዉ እና አስተማማኙ የኃይል ምንጭ ነዉ በሚል ኒኩሊየር ለከባቢ አየር ጥበቃ ወሳኝ ነዉ በሚል ይሟገታል። ጀርመን የፉኩሺማዉን አደጋ ተመልክታ የወሰደችዉን እርምጃም አጥብቆ ይተቻል። መከራከሪያዉ የድንጋይ ከሰልን ለኃይል ምንጭነት ከመጠቀም፤ ኒኩሊየር ኃይል ምንጭ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀዉ የብክለት መጠን አነስተኛ እና ዘላቂነቱ አስተማማኝ በመሆኑ እሱ ላይ ማተኮር ይገባል የሚል ነዉ። ስኮትላንዳዊዉ ኔተን ፓተርሰን የዚህ ድርጅት ባልደረባ እና ስለኒኩሊየር የኃይል ምንጭነት አዎንታዊ ጎኖች ሳይታክት የሚሟገት ወጣት ነዉ።

Japan, Premierminister, Shinzo Abe
ምስል picture-alliance

«የምለዉ ከባቢ አየሩን ከካርቦን በፍጥነት ለማጽዳት የሚያስፈልጉን ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት የሚያስከትሉ የኃይል ምንጮች ናቸዉ ነዉ። ለዚህ ደግሞ የሚመረጡት የንፋስ፣ የፀሐይ፣ የዉኃ እና የኒኩሊየር የኃይል ምንጮች ናቸዉ። ከጋዝንም ሆነ ከከሰል የኃይል ምንጭነት ለመላቀቅ ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ በበኩሌ አይታየኝም። ኒኩሊየር እጅግ አነስተኛ አሻራ በመተዉ ኃይልን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ቴክኒዎሎጂ መሆኑ ተረጋግጧል።»

ምንም እንኳን የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ወደከባቢ አየር በካይ ጋዞችን ይለቃል ተብሎ ባይወቀስም ያለዉ ጨረርም ሆነ የዝቃጭ አወጋገድ በጤና ላይ የሚያስከትለዉ አደጋ በየጊዜዉ መነጋገሪያ እንደሆነ ነዉ። ፓተርሰን ግን ስለጨረር ከተነሳ ፓይለቶች በዕለት ተዕለት ሥራቸዉ የሚያጋጥማቸዉ ከኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ከሚወጣዉ የከፋ ነዉ ባይ ነዉ።

«ምናልባት ያልተስተዋለዉ ጉዳይ ፉኩሺማ ላይ ከባድ አደጋ ደርሶ በነበረበት ወቅት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሲነገር ነበር ሆኖም ለኒኩሊየር የኃይል ማመንጫዉ ተጋልጦ በካንሰር ምክንያት የሞተ ሰዉ ግን የለም። በዚያ ላይ ደረጃዉን በጠበቀ መልኩ በሚንቀሳቀስ የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ላይ የሚሠሩ ሰዎች የመጋለጣቸዉ ሁኑታ አዉሮፕላን አብራሪዎች በየዕለቱ ከሚያገኛቸዉ የጨረር መጠን ያነሰ ነዉ።»

የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቀልበስ ለሚደረገዉ ጥረት መንግሥታት ከሁለት ዓመታት በፊት ፓሪስ ላይ የተስማሙበትን የብክለት መጠን የመቀነስ ርምጃ ለማሳካትም ይህን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግም ይናገራል።

Frankreich Atomkraftwerk Cattenom Besetzung durch Greenpeace Aktivisten
ምስል Getty Images/AFP/P. Hertzog

«የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫን ስለመዝጋት ስናወራ ጀርመን በርከት ያሉትን መዝጋቷን እናያለን፤ ግን ፈረንሳይን፤ ቤልጂየምን፣ ዩናይትድ ኪንግደምን ስንመለከት የመዝጋት ዕቅድ የላቸዉም። ምክንያቱም ሃገራቱ የፓሪሱን ስምምነት ግባቸዉን ለማሳካት ይህ እንደሚያፋጥንላቸዉ ያምናሉ። የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ካለ ድንጋይ ከሰል ማቃጠል አይኖርም በዚህ ደግሞ ወደከባቢ አየር የሚገባዉ ካርቦን ዳይይኦክሳይድ ይቀነሳል።»

የኒኩሊየር የኃይል ምንጭ ከባቢ አየር ላይ የሚያስከትለዉ የብክለት ተፅዕኖ ይቀንሳል ቢባልለትም የዝቃጭ አወጋገዱ ግን ማነጋገሩ አልቀረም።  ኔተን ፓተርሰን የዓለም አቀፉን የአቶም ኃይል ተከታታይ ተቋምን መመሪያ ተከትሎ እስከሁለት መቶ ዓመት ድረስ ተቀብሮ የሚኖርበትን ስልት መቀየስ እንደሚቻል ያስረዳል።

የኒኩሊየር የኃይል ምንጭነት የመቃወሙ እንቅስቃሴ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ አለዉ።በጎርጎሪዮሳዊዉ 1970ዎቹ መጀመሪያ ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ በምትገኘዉ ቪይል በተባለች ስፍራ የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ለመትከል የነበረዉ ዕቅድ በሕዝብ ተቃዉሞ መሰረዙ በመላዉ አዉሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ ተመሳሳይ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ብርታት ሰጥቷል።

Ukraine Duga-1 Radar-System
ምስል picture alliance/abaca/F. Pauletto

ተቃዉሞ እና ድጋፉ እስከዛሬ ዘልቆም የአዉሮጳ እና አሜሪካን ሃገራት ከዚህ ዘርፍ ኃይል ማመንጨታቸዉ መቀጠሉ አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራትንም ቀልብ መሳቡ እየታየ ነዉ። ደቡብ አፍሪቃ ተጨማሪ የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ለመገንባት አቅዳለች። ግብፅ እና ናይጀሪያም ዓይናቸዉን ጥለዉበታል። የደቡብ አፍሪቃ ዕቅድ ግን ከወዲሁ ተቃዉሞ እየቀረበበት ነዉ። ግሪንፒስ የተሰኘዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ ተቋም የደቡብ አፍሪቃ ቢሮዉ ኒኩለርን አስቁሙ የሚል ዘመቻዉን ጀምሯል። ሚሊታ ስኪል የግሪንፒስ አፍሪቃ የአየር ንብረት እና የኃይል ጉዳይ ዘመቻ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ ናቸዉ። ለድርጅታቸዉ ኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ደህንነቱ አስተማማኝ አይደለም።

«የደቡብ አፍሪቃ ኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ ለመገንባት መወሰኗ ከሚዛናዊ ዉሳኔ የሚቃረን ነዉ። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ተቋማት ተከታታይ ምርምር አካሂደዉ ከኒኩሊየር ማመንጫ ኤሌክትሪክ የማግኘቱ ሂደት ከየትኛዉም ዘርፍ የበለጠ ዉድ ዋጋ የሚጠይቅ መሆኑ ታዉቋል። ታዳሽ የኃይል ምንጮች ግን ርካሽ ናቸዉ። መንግሥት ምንም ቢሆን አዲስ የኒኩሊየር የኃይል ማመንጫ እንዲገነባ የታቀደዉ እንዲቀጥል ማዘዙ ጤናማ የወደፊት ሕይወትን በተመለከተ ከአካባቢ ተፈጥሮ መብታችን ጋር በግልፅ የሚጋጭ ነዉ ብለን  እናምናለን። ምክንያቱም ኒኩሊየር መቼም ቢሆን ደህንነቱ አስተማማኝ ሆኖ አያዉቅም።»

Schweiz Greenpeace-Protest gegen Atomkraftwerk
ምስል picture-alliance/dpa/U. Flueeler

ከዚህም ሌላ ደቡብ አፍሪቃ በዘርፉ ላይ አደጋ ቢፈጠር በሕዝቡ ላይ የከፋ ችግር እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል በቂ አቅምም ሆነ ዝግጅት አላት ብሎ ግሪንፒስ እንደማያምንም አክለዉ አመልክተዋል። አቶ ያለምሰዉ አደላ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ እና የዘርፉ ምሁር ናቸዉ።  አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል የኃይል ምንጭ ባይኖርም አንፃሪነቱ መታየት እንዳለበት ያስረዳሉ።

በአሁኑ ጊዜ በመላዉ ዓለም በ30 ሃገራት ዉስጥ 430 የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል 24ቱ የአዉሮጳ ሃገራት ናቸዉ። ከአፍሪቃ ሃገራት ብቸኛዋ የኑኪሊየር ኃይል ማመንጫ ባለቤት ደቡብ አፍሪቃ እስካሁን ሁለት ማመንጫዎች አሏት። ከሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይልም 5 በመቶዉን ይሸፍናሉ። ሙሉ ዝግጅቱን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ