1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ ሕግ መዘዝ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥር 22 2009

በትራምፕ ሕግ መሠረት ከ134 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ስደተኛ ይሁን ነጋዴ፤ ታካሚ ይሁን ተማሪ፤ የአሜሪካ ሰላይ ይሁን አስተርጓሚ፤የመኖሪያ ፍቃድ ይኑረዉ-አይኑረዉ ቢያንስ ለዘጠና ቀናት ዩናይትድ ስቴትስ መግባት አይችልም።

https://p.dw.com/p/2Wg4x
New York City Women's March Trump Proteste
ምስል Reuters/S. Keith

የትራምፕ ሕግ

ኢራኖች፤ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትን እርምጃ በአፀፋ-እርምጃ እንደሚበቀሉ ይዝታሉ።አዉሮጶች የዤኔቭ ስምምነት ይከበር ይላሉ።የመብት ተሟጋቾች ያወግዛሉ።አሜሪካዉያን ባደባባይ ይጮሐሉ።ዩናይትድ ስቴትስ የስደተኞች ሐገር ናት።አዲሱ መሪዋ ደግሞ ከአብዛኞቹ ስደተኞች ዘግይቶ የተሰደደ ቤተሰብ  የልጅ ልጅ፤ ወይም ልጅ ናቸዉ።የስደተኛች ዉልድ-ዉላጁ ሕዝብ፤ ዘግይቶ የተሰደደዉን ቤተ-ሰብ የልጅ ልጅ ወይም ልጅ መርጦ የሾመዉ፤ ተሿሚዉ ስደተኞች፤ ከስደተኞቹ ሐገር እንዳይገቡ ለማገድ ቃል በመግባታቸዉ ነበር።የስደተኞቹ የልጅ-ልጅ ከስደተኞቹ ሐገር ስደተኛ እንዳይገባ አገዱ።ቃልቸዉን አከበሩ።አርብ።ቃል በማክበራቸዉ መወገዝ፤ መወቀስ፤መተቸታቸዉ ለእሳቸዉና ለደጋፊዎቻቸዉ በርግጥ አይገባቸዉም።የገባዉ አለ ይሆን?ላፍታ አብረን እንጠይቅ

ታሕሳስ 7 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ከያኔዉ ፕሬዝደንታዊ ተፎካካሪ ዶናልድ ጆን ትራምፕ አምደ-መረብ የተለጠፈዉ መልዕክት ካንድ ቀን በኋላ ተሰርዟል።የሰራዡ ማንነት እና የተሠረዘበት ምክንያት በዉል አልታወቀም።መልዕክቱ ግን ተሰራጭቷል።

                     

«የሐገራችን ተወካዮች የሚሆነዉን መአት እስኪያዉቁት ድረስ ሙስሊሞች በሙሉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ (እንዲዘጋባቸዉ) ዶናልድ ጄ ትራምፕ ጥሪ ያቀርባል።----ምርጫ የለንም፤ ም---ር---ጫ----የ-ለ-ን-ም።»እና  ቃል ነበረ።የሚሊዮን አሜሪካዉያን ድጋፍ የተንቆረቆረለት ግልፅ ቃል።ቃል ገቢር ሆነ።አርብ።« ወደዚች ሐገር የሚገባዉ ሰዉ ማንነትን ለማወቅ ተጨማሪ ማጣራት እስከሚደረግ ድረስ ለዘጠና ቀናት የሚፀና እገዳ ነዉ።የአሜሪካ ዜጎች ደሕንነት፤ የሐገራችን ደሕነት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ ነዉ።ፕሬዝደንቱ ትናንት ያደረጉት ይሕንን ነዉ።ወደ ሐገራችን እንደገቡ የምንፈቅድላቸዉ ሰዎች ወደዚሕ የሚመጡት ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸዉን እና ሰላማዊ ዓላማ ያላቸዉ መሆንቸዉን ማረጋገች ነዉ።»

Deutschland Anti-Trump Protest in Berlin
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

አፈ ቀላጤ ሼን ስፒሰር።ቅዳሜ።

ትራምፕ ከነጋዴነት ወደ ፖለቲከኝነት መቀየራቸዉን ካስታወቁበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ጋዜጠኞች፤ፖለቲከኞች እና  ተንታኞች «ሰዉዬዉ ሙስሊም አይወዱም» ይላሉ።ባለፈዉ አርብ የሰባት የሙስሊም ሐገራት ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸዉን ደግሞ ለአባባላቸዉ ማረጋገጪያ ያደርጉታል።ዘገባ፤ ትንታኔዉ እዉነም-ሐሰትም ሊሆን፤ ላይሆንም ይችላል።ግን የሚወዱት ማንን ይሆን? «አሜሪካን» ይላሉ እሳቸዉ።

አሜሪካን ስለሚወዱ አሜሪካን ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነዉን ድንበር በግንብ አጥር ለመዝጋት ቃል ገብተዉ፤ ቃላቸዉን ገቢር አደረጉ።ወሰኑ።አስራ-አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቀዉን የማስገንቢያ ወጪ ሜክሲኮን እንደሚያስከፍሉ አስታወቁም።ሜክሲኮዎች ባብዛኛዉ ካቶሊኮች ናቸዉ።ሰዉዬዉ ካቶሊክም ይጠላሉ እንበል? አይታወቅም።

የሚታወቀዉ የሜክሲኮዉ ፕሬዝደንት ኤንሪኮ ፔና ኒቶ  ዉሳኔዉን በመቃወም  ዋይት ሐዉስን ለመጎብኘት የነበራቸዉን ዕቅድ መሰረዛቸዉ ነዉ።የእስልማናዉ ታሪክ እንደሚነግረን ከመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ዮርዳኖስን የሚገዙት ነገስታት ከነብዩ መሐመድ የዘር-ሐረግ የሚመመዘዙ ናቸዉ።ሐሺማይት።

የዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላሕ ዳግማዊ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምን ለማነጋገር ዛሬ ዋሽግተን ይገባሉ።ንጉሱ ባለቀ ሰዓት ሐሳባቸዉን ካልቀየሩ በስተቀር ትራምፕን እንደ ሐገር መሪ በገፅ በማነጋገር ሁለተኛዉ የሐገር መሪ ይሆናሉ።ቀዳሚዋ የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሪዛ ሜይ ናቸዉ። የሜክሲኮዉ መሪ ሐገር-ወገኔ ተነካ ብለዉ ሌላ ማድረግ ቢያቅታቸዉ ጉብኝታቸዉን ሰረዙ።እስልምናን ከእምነት ባለፍ በደም የወረሱት የሐሺማይቷ ንጉሳዊ ግዛት ገዢ ግን ወገኖቻቸዉ መታገዳቸዉ በታወጀ ሳልስት ከትራምፕ ጋር የወዳጅነት «ፅዋ» ሊያጋጩ ነዉ።«አጃኢብ» እንዲል አረብ።

አለም አላለ ንጉስ አብደላሕ ዳግማዊ ከትራምፕ ጋር ለመምከር ዋሽግተን የሚገቡት ትልቂቱ ከተማ የትልቁን ሰዉዬ ዉሳኔ በሚቃወም ታላቅ ሰልፍ እንደተጥለቀለቀች ነዉ።አሜሪካን የሚወዱት መሪን ዉሳኔ በመቃወም  አደባባይ የወጡት አሜሪካዊት እንደሚሉት የፕሬዝደንቱ እርምጃ የአሜሪካ ፀር እንጂ የሚወዳት ሊሆን አይችልም።«ዶናልድ ትራምፕ ያደረጉት አሳፋሪ ነዉ።ክብርነክ ነዉ።ፍፁም አሜሪካን የሚቃረን ነዉ።እቃወመዋለሁ።እንዴት ቢደፍሩ ነዉ።እንዴት ቢደፍሩ ነዉ፤ ሰዎች እንዳይገቡ የሚያግደዉን ሰነድ ብቻቸዉን የሚፈርሙት።»

Infografik Karte Trump: Einreisestopp für Bürger aus sieben Ländern  Deutsch

በርግጥም ደፋር ናቸዉ።በድፍረት ይገዛሉ፤ይገነባሉ-ይሸጣሉ።ያተርፋሉ።ይከብራሉ።በድፍረት ይናገራሉ።ሲሻቸዉ ይሳደባሉ።ሲያሰኛዉ ክሊንተንን እንዳሉት ለማሰር ያስፈራራሉ።ይመረጣሉ።እንደገና ይወስናሉ።ማንናቸዉ? ያንዲት ቃል ጥያቄ።ረጅም መልስ--------

የያኔዉ ወጣት ጀርመናዊ እስከ 17ኛ መቶዎቹ አጋማሽ ድረስ ድሩምፕፍ የነበረዉን የቤተ-ሰብ ስም ቅምቅም-ቅድመ አያቶቹ የቀየሩበትን ምክንያት ለማወቅ የሚያስብ፤የሚመራመርበት ዕዉቀት፤አቅም፤ ጊዜ ፍላጎትም አልነበረዉም።

ድሕነትን ለመሸሽ ግን ዘየደ።ወሰነም።ስደት።ተወልዶ ያደገባትን የካልሽታትን ከተማ ጥሎ ወደ ካዲሲቱ ሐገር ገባ።ዩናይትድ ስቴትስ።1885።አስራ-ስድስት ዓመቱ ነበር።ፍሬድሪሽ ትሩምፕፍ የሚለዉ ስሙ አዲስ ከተቀየጠዉ ማሕበረሰብ ባሕልና ቋንቋ ጋር እንደማይጣጠም ሲረዳ  እሱም በተራዉ ሙሉ ስሙን ቀየረ።ፍሪድሪሽን-ፍሬድሪክን አለዉ።ትራምፍን-ትራምፕ።

ለሰራ-የልፋቱን፤ ለተመራመረ የጥረቱን፤ ላጭበረበረ-የብልጠቱን፤ለቀማ የጉልበቱን የማትነፍገዉ ሐገር ካሰችዉ ።ከበረ።አገሩ ሔዶ የመንደሩን ልጅ አግብቶ ሁለት ሆኖ ተመለሰ።1902።በሰወስተኛ ዓመታቸዉ እሱ-እናት-እሷ አባት ሆኑ።

ልጁንም ፍሬድርክ-ክሪስት ትራምፕ አሉት። እንደ ማቆላመጥ ፍሬድ ።ፍሬድ 13ኛ ልደቱን ሲያከብር አባቱ አረፉ።1918።ለቤተሰቡ በርግጥ ታላቅ ሐዘን ነበር።ሰዉዬዉ ለሚስት ልጆቻቸዉ ከሐብታቸዉ እኩል-ታታሪነትን፤ ከስማቸዉ ጋር ጥንካሬን በማዉረሳቸዉ  ቤተሰቡ በሐብት-ላይ ይጨምር ገባ እንጂ አልተቸገረም።

 

ስኮትላንዳዊቷ ኮረዳ ሜሪ አነ ማክሎይድ ችግር አስመረሯት እንደ ፍሬድ አባት ሁሉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስትሰደድ ወጣቱ ፍሬድ ባባት-እናቱ ሐብት ላይ ሐብት ከምሮ ዶላር-እያፈሰ-ዶላር ይረጭ ነበር።1930።50 ዶላር ቋጥራ አሜሪካ የገባችዉ ሜሪ አነ ማክሎይድ ለአምስት ዓመት ያክል በግርድና ፈጋች።ድሕነትን ማሸነፍ ግን አልቻለችም።አምስተኛ ዓመቷን ስታጋምስ ቱጃሩን አወቀችዉ ወይም እሱ አወቃት። ፌሬድን። ተጋቡ።1936።በአስረኛ አመቱ ሰዉዬዉ ተወለዱ።ዶናልድ ጆን ትራምፕ።

                              

የስደተኞች ልጅ ግን አሜሪካዊ ናቸዉ።አሜሪካም የስደተኞች ሐገር።«እኛ አሜሪካዉያን ነን።የስደተኞች ሐገር ነን።ስደተኞች ወደየሐገራቸዉ መሔድ አለባቸዉ የሚል ሰዉ፤ ይሕን መርሳት አለበት።እኛ በክፍለ-ዓለሚቱ የሰፍረን የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አይደለንም።»

እዉነታዉ ግን ተቃራኒዉ ነዉ።እንደያዉም የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማድሊን ኦልብራይት በቀደም እንዳሉት በዘመናችን ለስደተኛ ከሚደረገዉ ድጋፍ እና እንክብካቤ ይልቅ ለአሜሪካ ዉሻ የሚደረገዉ  ይበልጣል።

                                       

«እንዲያዉ የሚያሳዝነኝ እኒያ ልጆቻቸዉን አዝለዉ፤ በረሐ አቋርጠዉ ሊሰምጥ ከሚችል  ጀልባ የሚሳፈሩትን ሰዎች ሳይ ነዉ።ይሕን ካለፉ በኋላ ደግሞ በየሚደርሱበት ሥፍራ እንደዉሻ መታየታቸዉ ነዉ።በነገራች ላይ ከስደተኞች ይልቅ ለአሜሪካ ዉሾች የተሻለ እንክብካቤ ይደረጋል ብያለሁ።»

ኦልብራይት የቀድሞዋ ቼኮዝላቪኪያ ስደኛ ናቸዉ።በትራምፕ ሕግ መሠረት ከ134 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ስደተኛ ይሁን ነጋዴ፤ ታካሚ ይሁን ተማሪ፤ የአሜሪካ ሰላይ ይሁን አስተርጓሚ፤የመኖሪያ ፍቃድ ይኑረዉ-አይኑረዉ ቢያንስ ለዘጠና ቀናት ዩናይትድ ስቴትስ መግባት አይችልም።

Deutschland Demonstration gegen die Wahl von Donald Trump
ምስል picture alliance/dpa/L. Mirgeler

የአሜሪካ ጦር የቀድሞዉ የኢራቅ ፕሬዝደንት ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን ያስወገደዉ ኋላም ያስገደለዉ ከኢራቃዉያን ተባባሪዎቹ በተደገለት ድጋፍና ባገኘዉ መረጃ ነዉ።ጦሩ የሳዳምን መንግሥት ወይም ከሳዳም መገደል በኋላ የተደረጁትን አሸባሪዎች በሚወጋበት ወቅት በአስተርጓሚና በመረጃ አቀባይነት በሺ የሚቆጠሩ ኢራቃዉያን አሜሪካኖችን አገልግለዋል።አንዱ በቀደም እንዳሉት ያደረጉትን ሁሉ ያደረጉት አሜሪካ እየኖሩ የሰላም፤ ዴሞክራሲን የፍትሕ-እኩልነትን ትሩፋት ለማጣጣም ነበር።በቀደም ኒዮርክ ላይ ተያዙ።ከብዙ ሙግት በኋላ ተለቀቁ።

                                   

«ይሕ ሰብአዊነት ነዉ።ይሕ የአሜሪካ ልዩ መለያ ነዉ።ሐገሬን ጥዬ እዚሕ እንደመጣ ያደረገኝም እሱዉ ነዉ።»

ከእንግዲሕ ግን ቢያንስ ለሰባቱ ሐገራት ዜጎች አሜሪካ-የሚወራ የሚባልላት ሐገር አይደለችም።ትራምፕ በተደጋጋሚ እንዳሉት የሰባቱ ሐገራት ዜጎችን ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ያገዱት «አሸባሪዎችን ለመከላከል» ነዉ።

በ1970ዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ ቬትናምን በምትወጋበት ወቅት የሐገሪቱ ባለሥልጣናት ከአስከፊዉ ጦርነት ለመዘፈቃቸዉ የሚሰጡት ምክንያት ኮሚንስቶችን «ለማጥፋት» የሚል ነበር።እዉነታዉ ከሐሰቱ ምክንያት መቃረኑን ያወቁ «አላማችሁ ኮሚንስቶችን ማጥፋት ከሆነ ቀንደኞቹ ኮሚንስቶች ሞስኮ ላይ እያሉላችሁ እስያ ድረስ ምንአዘመታችሁ» እያሉ ያፌዙባቸዉ ነበር።

ዘገቦች እንደጠቆሙት ባለፉት አርባ ዓመታት ትራምፕ በአርቡ አዋጃቸዉ ከጠቀሷቸዉ የሰባቱ ሐገራት አንድም ዜጋ ዩናይትድ ስቴትስን አሸብሮ አያዉቅም።አሜሪካን ማሸበራቸዉ የተነገረዉ የሳዑዲ አረቢያ፤ የግብፅ እና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ናቸዉ።

Donald Trump
ምስል picture-alliance/Olivier Douliery/CNP/AdMedia

እርግጥ ነዉ ሰዉዬዉ እንደ ሰዉ የፈለጉትን መዉደድ የፈለጉትን መጥላት ይችላሉ።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ግን የተገን ጠያቂዎችን መብት ለማስከበር ዤኔቭ ላይ የተፈረመዉ ዓለም አቀፍ ዉል መጣስ የለበትን።እንደ ሜርክል ሁሉ የፈረንሳይ፤ የብሪታንያ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና የሌሎችም የምዕራባዉያን መንግሥታት እና ድርጅቶች መሪዎች የትራምፕን ዉሳኔ ተቃዉመዋል።ማብራሪያ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋልም።የአፍሪቃ ሕብረትም ዉሳኔዉን ተቃዉሟል።

ሐምሳ ሰባት አባል ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የእስልምና ትብብር ማሕበር በፋንታዉ ዉሳኔዉን ለአሸባሪዎች መጠናከር ጥሩ ምክንያት ብሎታል።ዜጎቻቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ከታገዱባቸዉ መካከል እስከ ዛሬ ቀጥተኛ መልስ የሰጠችዉ ኢራን ናት።የኢራን መንግሥት ለትራም ዉሳኔ አፀፋ-አሜሪካዉያን ኢራን እንዳይገቡ አግዷል።

የኢራን ምክንትል ፕሬዝደንት ኢሻቅ ጃሐንግሪ  መንግሥታቸዉ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚያቀርብ አስታዉቀዋልም።ትራምፕ ብሪታንያን በይፋ እንዳይጎበኙ የሚጠይቁ ወገኖች ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የድጋፍ ፊርማ አሰባስበዋል።ትራምፕ በተደጋጋሚ እንዳሉት አሜሪካን ይወዳሉ እንበል ወይስ ይጎዳሉ? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ