1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የተገን ጠያቂዎች ሥራ እና ትምህርት በጀርመን

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 2009

በአገራቸው ኹከት እስር እና እንግልት የሸሹ 890,000 ተገን ጠያቂዎች በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ወደ ጀርመን ገብተዋል። እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ቀደም ሲል እንደተገመተው ሳይሆን የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ያገኙ መሆናቸውን አንድ ጥናት ጠቆሟል። 

https://p.dw.com/p/2SnaF
Deutschland Wirtschaft will Flüchtlinge leichter in Jobs bringen (Symbolbild)
ምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul

የተገን ጠያቂዎች ሥራ እና ትምህርት በጀርመን

ከሶሪያዋ ደማስቆ ከተማ ተሰዳ በጀርመን በፍራንክፈርት ከተማ ተገን የጠየቀችው እዝራ ተወልዳ ባደገችባት ከተማ የልብስ ቅድ ሙያ ትማር ነበር። የ20 አመቷ ወጣት አንድ ቀን  የልብስ ቅድ ባለሙያ የመሆን ሕልም አላት። «በሶርያ የልብስ ቅድ ሙያን ለሁለት አመታት ተምሪያለሁ። እዚህም ይኽንኑ ሙያ መማር እፈልጋለሁ።» የምትለው እዝራ ጀርመንኛ ቋንቋ በጣም እንደሆነባት ገልጣለች።  «ይመስለኛል ቀስበቀስ በትጋት መማር ይፈልጋል። ወደ ፊት ቋንቋውን ጥሩ አድርጌ መናገር እችላለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ቋንቋውን ካጠናቀቅኩ በኋላ የልብስ ቅድ ሙያን ተምሬ በኢንደስትሪው ውስጥ መስራት እሻለሁ።»እስከዚያው ግን እዝራ በፍራንክፈርት ከተማ ስቲች ባይ ስቲች በተሰኘ ጀማሪ ኩባንያ ውስጥ አጫጭር ሥልጠናዎች በመውሰድ ላይ ነች። 
ክላውዲያ ፍሪክ፦ ከስቲች ባይ ስቲች መስራቾች መካከል አንዷ ናት። በልብስ ቅድ ባለሙያዋ ራሷ የነደፈቻቸውን ልብሶች በፍራንክፈርት ለገበያ ታቀርባለች። «ከአገራቸው ከተሰደዱ ከፕሮፌሽናል ልብስ ሰፊዎች ጋር በጥምረት እየሰራን ነው። ዋና አላማው እነዚህ ተገን ጠያቂዎች በፍጥነት እና በቀላሉ ከማሕበረቡ ጋር እንዲቀላቀሉ እገዛ ማቅረብ ነው።» ስትል ሐሳባቸውን ታስረዳለች። 

ኒክ እና ክላውዲያ በጀርመን የልብስ ገበያ ውስጥ እዝራን የመሳሰሉ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ይዘው እንዲቀርቡም እቅድ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ የጀርመንን ቋንቋ፤ባሕል እና ሥራ የሚለማመዱበት መንገድም አድርገውላቸዋል። 

እንደ እዝራ ሁሉ በአገራቸው ኹከት እስር እና እንግልት የሸሹ 890,000 ተገን ጠያቂዎች በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ወደ ጀርመን ገብተዋል። እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ቀደም ሲል እንደተገመተው ሳይሆን የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ያገኙ መሆናቸውን አንድ ጥናት ጠቆሟል። 
የጀርመን የስደት እና ተገን ጠያቂዎች ቢሮ ከስራ ቅጥር ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገው ዘገባ በአይነቱ የመጀመሪያው ሲሆን ተገን ጠያቂዎች ያላቸውን የትምህርት ዝግጅት እና ተነሳሽነት ይፈትሻል። 
በዚህ ጥናት መሰረት ከሁሉም እንስቶች አንድ ሶስተኛው ከወንዶች ደግሞ ሁለት አምስተኛው በጉዞ ወቅት አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። በጥናቱ ከተካተቱ እንስቶች 15 በመቶው ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። 

እስከ 50,000 የሚሆኑ ተገን ጠያቂዎች ከመስከረም 20115 እስከ መስከረም 2016 ባለው አንድ ዓመት ሥራ አግኝተዋል። በግብርናው ዘርፍ እና የማከማቻ መጋዘኖች ውስጥ ሥራ ያገኙ  30,000 ተገን ጠያቂዎች ለማሕበራዊ ዋስትና መክፈል የሚያስችላቸው በቂ ደሞዝ ያገኛሉ። በግል የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ የመኖራቸውን ያክል 100,000 ተገን ጠያቂዎች አሁንም እንደ ስራ አጥ የተለያዩ ድጋፎች ከመንግስት እንደሚደረግላቸው ይኸው ጥናት ጠቁሟል። ጥናቱን በኃላፊነት የመሩት ፕሮፌሰር ጀርገን ሹፕ እንደሚሉት ጥናቱን ሶስት ተቋማት በትብብር ሰርተውታል። 
«ተገን ጠያቂዎቹን የሚወክል የዳሰሳ ጥናት ሲደረግ የመጀመሪያው በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ከ2013 ጀምሮ ወደ ጀርመን የደረሱ ተገን ጠያቂዎች ያሉበትን ሁኔታ መናገር የሚያስችል ጥናት ነው።  በዚህ ጥናት በጀርመን የሚኖሩ 2300 ተገን ጠያቂዎችን አነጋግረናል። ይህ የሶስት ተቋማት የጥምረት ውጤት ነው። ተቋማቱ በኑረምበርግ የሚገኘው የሥራ ቅጥር ጥናት ተቋም፤ የፌዴራል ስደት እና ተገን ጠያቂዎች ቢሮ የጥናት ተቋም እና በጀርመን የኤኮኖሚ ጥናት ተቋም የማህበራዊ እና ኤኮኖሚ ጥናት መድረክ ናቸው።»

Deutschland Job für Flüchtlinge
ምስል picture alliance/dpa/S. Hoppe

በዚህ ጥናት መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2015 እና 2016 ወደ ጀርመን ከደረሱ ተገን ጠያቂዎች ከስምንቱ አንዱ ብቻ ስራ አግኝቷል። አብዛኞቹ የተገን ማመልከቻቸው በሚመዘንበት ደረጃ ላይ በመሆናቸው ተቀጥሮ የመስራት እድላቸው የተገደበ ነው። በጥናቱ ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል 50% የሚሆኑት በጀርመን ለአምስት አመታት ከኖሩ በኋላ ሥራ ያገኙ ሲሆን ከአስር እስከ 15 ዓመታት ለመጠበቅ የተገደዱ መኖራቸውም ተገልጧል። ሥራ ካልጀመሩት መካከል 75 በመቶው በእርግጠኝነት ሥራ እንደሚፈልጉ የገለጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ምናልባት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

«በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ለምን ወደ ጀርመን እንደመጡ መገንዘብ ያሻል። አብዛኞቹ ኹከት፤ግጭት እና ጦርነት ሸሽተው ከትውልድ አገራቸው መውጣታቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ከተገን ጠያቂዎቹ መካከል 70 በመቶ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ተገን ጠያቂዎቹ በግድ ወደ ጀርመን የጎረፉባቸው ሰብዓዊ ምክንያቶች አሉ። በርካታ የአችር ጊዜ ፈተናዎችም አሉ። የቋንቋ ክህሎት እና ለሥራ ብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያሻል። በረጅም ጊዜ ሒደት ግን ፈተናዎቹ ስለሚቀረፉ ለአገሪቱ መልካም አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት አላቸው። ራሳቸውን ለማሳደግ እና አዳዲስ የጀርመን ክህሎቶች ለመማር ዝግጁ ናቸው። አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ35 አመት በታች በመሆኑ ከጀርመን ማሕበረሰብ አኳያ በአንፃራዊነት ወጣት ናቸው። በረጅም ጊዜ ሒደት ባላቸው ተነሳሽነት እና ዝግጁነት ለጀርመን ኤኮኖሚ አዎንታዊ ሚና ይኖራቸዋል።» ይላሉ ፕሮፌሰር ጀርገን ሹፕ

Deutschland Zuwanderer oft gebildet
ምስል picture-alliance/dpa

እድሜያቸው ከ18-65 የሚደርሱት እና በዚህ ጥናት ከተካተቱት ተገን ጠያቂዎች ሶስት አራተኛው ወደ ጀርመን ከመጓዛቸው በፊት የሥራ ልምድ አላቸው። 13 በመቶው ደግሞ በአስተዳዳሪነት የሚሰሩ ነበሩ። በጥናቱ መሰረት በጀርመን የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች ወርሐዊ ደሞዝ በጎርጎሮሳዊው 2015 በአማካኝ 3,600 ዩሮ ነው። ተገን ጠያቂዎች በሶስተኛ አገር አቋርጠው ወደ ጀርመን ለመጓዝ የዚህን ሁለት እጥፍ ከፍለዋል። ጉዞው ከ35 እስከ 49 ቀናት ወስዶባቸዋል። 
በዚህ ጥናት ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው ተገን ጠያቂዎች 43 በመቶው የጀርመን የትምህርት ሥርዓት ወደ አገሪቱ ለመምጣት መነሾ እንደሆናቸው ተናግረዋል። 58 በመቶው ከአስር ዓመት በላይ በትምህርት ገበታ ላይ ያሳለፉ ሲሆን 37 በመቶው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ምንም የትምህርት እድል ያላገኙት ዘጠኝ በመቶ ብቻ ናቸው። 
እዝራ ከጀርመን ጋር የተጣጣመ የትምህርት ሥርዓት በነበራት ሶርያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች። ወጣቷ አዲስ ለሚመጡ ሶርያውያን በማስተርጎም ጭምር ትሰራለች። እነ ክላውዲያ እዝራን ጨምሮ ጀርመን የተቀበለቻቸውን ተገን ጠያቂዎች በማገዙ ረገድ ከፖለቲከኞች ባሻገር እያንዳንዱ ኩባንያ እና ግለሰብ ጥረት ማድረግ አለበት የሚል እምነት አላቸው።
«አንዳች ጥረት ካደረክ ከማሕበረሰቡ ጋር መቀላቀል ውጤታማም መሆን አይቸግርም ብዬ አምናለሁ። እንዲህ አይነት የማሕበራዊ ግብይት ስራዎች ደግሞ ጥሩ አማራጮች ናቸው። ማሕበራዊ ችግርን ለማቅለል የንግድ ሥራዎች ጥሩ መሳሪያ ይሆናሉ።  ይህ ነው የእኛ እቅድ። ጥያቄው አንጌላ ሜርክል ምን እያደረጉ ነው አሊያም ሌሎች ሰዎች ምን አደረጉ የሚለው አይደለም። እኛ ምን ምን ማድረግ እንችላለን? የራሳቸውን እድል እንዲያገኙ የሆነ ነገር ለመስራት የራሳቸውን መንገድ እንዲያበጁ እሻለሁ። ምን አልባት ከሶስት አመታት በኋላ የራሳቸው ወርክሾፕ ይኖራቸው ይሆናል።

ባለፈው ዓመት አገሪቱ የተቀበለቻቸው አብዛኞቹ ሥደተኞች በጀርመን የሰው ኃይል ገበያ ውስጥ በቀላሉ ሊዋሐዱ የሚችሉ መሆናቸውን የጀርመን ፌዴራል የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ቢሮ ኃላፊ ገልጠዋል። ኃላፊው ፍራንክ ጀርገን ቬይዝ ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ማሕበራዊ አንድነት(CSU)  ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ጀርመን ባለፈው ዓመት የተቀበለቻቸውን ተገን ጠያቂዎች ለማዋሐድ እምብዛም አትቸገርም ሲሉ ተናግረዋል። 


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ