1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፤ የተቃዉሞ ሰልፎችና አስተያየት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 27 2008

በኢትዮጵያ ከተሞች የተቃዉሞ ሰልፎች መካሄድ ከጀመረ ሰነባበተ። በኦሮምያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከወራት በፊት የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ እየበረደ ዳግምም እያገረሸ ቀጥሏል። በአማራ ክልል በተለይ ጎንደር ላይ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት መያዝ ጋር በተገናኘ የተነሳዉ ተቃዉሞ ቀጥሎ ባለፈዉ እሁድ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/1Jaym
Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

[No title]

ጎንደር ባለፈዉ እሁድ በታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ብትጥለቀለቅም አጀማመሩም አፈፃጸሙም ሰላማዊ እንደነበር ተነግሮላታል። በሰልፉ ላይ የተነሱ አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም ሁኔታዉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ የፀጥታ ኃይሉ የበኩሉን አስተዋፆኦ ማድረጉን አቶ መኳንንት መልካሙ የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

በጎንደርም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚታየዉ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ሕዝቡ ለሚያቀርባቸዉ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመንግሥት በማጣቱ ምክንያት የመጡ መሆናቸዉን ነዉ የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ አዲሱ ጌታነህ እና የኦሮሞ ፌደራዊ ኮንግረስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ በተከታታይ የሚናገሩት።

Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ በጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከሕዝቡ ከቀረቡ ጥያቄዎች በፍጥነት መልስ ሊያገኙ የሚገባቸዉ መኖራቸዉን ተናግረዋል።

በዴሳ፤ ቆቦ እና አወዳይን በመሳሰሉ በተለያዩ የምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎች የቀጠሉ ሲሆን ሰዎች በጥይት እንደተመቱ፤ የሞቱም እንዳሉ የሚያሳዩ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንደሚሰራጩ ጠቅሰን እዉነታዉን የጠየቅናቸዉ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ ጉዳዩን ለመንግሥትም ሆነ ለዓለም ማሕበረሰብ በማሳወቅ የኃይል ርምጃዉ እንዲቆም ጥሪ ማድረጋቸዉን አመልክተዋል።

አክለዉም በማንኛዉም ክልል የሚገኙ ሕዝቦች ሕጋዊ እና ሰላማዊ ጥያቄ በያቀርቡበት ጊዜ ተገቢ መልስ መስጠት እንጂ የመንግሥት ኃይሎች ሊተኩሱባቸዉ አይገባም የሚለዉ የፓርቲያቸዉ አቋም እንደሆነ ያመለከቱት የኦሮሞ ፌደራዊ ኮንግረስ ባለሥልጣን አቶ ጥሩነህ፤ በጎንደርም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከሕዝቡ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እንደሚደግፉም ገልጸዋል። የፊታችን እሁድ ባህር ዳር ከተማ ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ያረጋገጡት አቶ አዲሱ በበኩላቸዉ የሰልፉን አላማ ዘርዝረዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ