1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተቃዉሞ ሰልፍ እና ተኩስ በነቀምቴ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ የካቲት 19 2010

ሁለተኛዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስራ ላይ ከዋለ ዛሬ 11ኛ ቀኑን አስቆጥሯል ። መንግስት የፖለቲካ አለመረጋጋትን ለመቆጣጠር ደነገኩ ያለዉ ይህ አዋጅ  በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሃይማኖት ተቋማትና በማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ላይ ተፅኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ነዋሪዎች በተለያዩ መንገዶች እየገለፁ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2tMn7
Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

በምዕራብ ኦሮሚያ በነቀምቴ ከተማ ዛሬ የተቃዉሞ ድምፃቸዉን ለማሰማት መንገድ ላይ በወጡ ሰዎች ላይ የመከላክያ ሰራዊት አባላቶች ቱክስ እንደከፈቱባቸዉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ለተቃዉሞዉ መነሻ ምክንያት ምንድን ነዉ? በነቀምቴ የሚታየዉ ድባብስ ምን ይመስላል? ስማቸዉን መግለፅ ያልፈለጉት የከተማዋ ነዋሪ ያስረዳሉ፤  «የማህበረሰቡ ጥያቄ ፣ ያዉ መጀመርያ ተነስቶ እንደነበር፣ አቶ በቀለና ዶክተር መራራ ወደ ከተማዋ እየመጡ ነበረ። ግን ጉቴ ተብላ በምትታወቀዋ  አከባቢ ላይ  የመከላክያ ሰራዊት አባሎች እንዳይገቡ መንገድ ዘግተዉባቸዉ ነበር። ማህበረሰቡ መከላክያ እንድያሳልፋቸዉ ብጠይቅም መልስ ስላላገኙ መንገድ መዝጋት ጀመሩ። እዚህ ባኬ ጃማ በሚባል ቦታ ሰፍሮ የሚገኙ የመከላክያ ሰራዊት አባላቶች ሰዎች ላይ ቱክስ ከፍተዋል። አሁንም ሁኔታዉ አልረገበም። አሁንም እየተከሱ ናቸዉ። መህበረሰቡም እየሸሸ አይደለም። መከላከያ ከተማዋን ለቆ እንዚወጣ እየጠየቁ ናቸዉ። እስካሁን ባለን መረጃ ግን የቆሰለም የሞተም የለም።»

አቶ በቀለ ገርባ፤ ዶክተር መረራ ጉዲናና ሌሎች የኦሮሞ ፌዴራልስት ኮንግሬስ አባላቶች ከእስር ከተፈቱ በዋላ ሕዝብ እንk/ን ከእስር ወጣችሁ እያለ አቀባበል እያደረገላቸዉ ይገኛል። በተመሳሳይም የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ለፖለቲካ አመራሮቹ ጥሪ ባደረገላቸዉ መሰረት ቅዳሜ ወደ ከተማዋ እንዳቀኑ አቶ በቀለ ጋርባ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። ነቀምቴ  ለመድረስ ወደ 12 ኪሎሜትር ስቀር የመከላክያ ሰራዊት፣ የአድማ በታኝና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ መታዘዛቸዉ፣ ጉዳዩንም ለማጣራት እስከ ሌሊቱ 10 ሰዓት ድረስ ቦታዉ ላይ እንደቆዩ፣ እዛዉ ያለ ምግብና ያለ ዉኃ በብርድ ዉስጥ ዉጭ ካደሩ በዋላ መፍትሄ  ሳያገኙ ትላንት ወደ መኖርያ ቤታቸዉ መመላሳቸዉን አቶ በቀለ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በምዕራብ ኦሮሚያ በደንቢ ዶሎ ከተማ ቅዳሜ እለት ከእኩለ ቀን በኋላ  የመከላከያ ሰራዊት አባላቶቹ ወሰዱ በተባለዉ የቱክስ ርምጃ ሰዎች እንደቆሰሉና እንደሞቱም ዘገባዎች ያመለክታሉ። ሁኔታዉን አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የገለፁ የአከባቢዉ ተከታዩን  አጋርቶናል፣ «እስራኤል ዳንሳ የተበለዉ የወንጌላዊት ቤተክርስትያን ሰባኪ ደንቢዶሎ ለሰበካ እንደሚመጣ  ዝግጅት ነበረ። ይህን በተመለከተ ሰዎች በድምፅ ማጉያ ማስታወቅያ ስያደርጉም ነበረ። መከላክያ እነዚህን ሰዎች ለምን ማስታወቅያ ታደርጋላችሁ በሚል ይዞዋቸዉ መደብደብ ጀመሩ። ቄሮዎቹ ደግሞ ለምን ሰዎቹን ትመታላችሁ፣ ልቀቋቸዉ በምል ግጭት ተፈጠረ። መከላክያም በቀጥታ ወደ ሰዎቹና ለገበያ የወጡት ሰዎች ላይ መቶከስ ጀመሩ። ከቆሰሉት ዉስጥ ሁለት ሰዎች በሞት አፋፍ ላይ ይገኛሉ። አሁንም ይሄን ሁለት ቀን መንገድም፣ ሱቆችም፣ ባንኮችም ሁሉ ዝግ ናቸዉ።»

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም  ባወጣዉ መግለጫ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ «ሥር እንድትተዳደር መደረጉ የፈነጠቀውን የሠላምና የመግባባት ተስፋ አደብዝዞ ሀገሪቱን ይበልጥ አሳሳቢ በሆነ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊያስገባት ይችል ይሆን የሚል ሥጋት»፣ እንዳሳደረባት «መንግስት ያሉትን ሁኔታዎች በጥልቀት አጢኖ ቢቻል አዋጁን ማንሳት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደገና እንዲመክር፤ አዋጁ ሥራ ላይ ይዋል ከተባለ ደግሞ በአፈጻጸሙ ወቅት የዜጎች መሰረታዊ መብትና ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ» ጥሪዋን አስተላልፋለች። ይሄን ጉዳይ አስመልክቶ በድምፅ አስተያየት እንዲሰጡን ብንጠይቅም የወጣዉ መግለጫ በቂ ነዉ የሚል መልስን አግኝተናል።

ሙሉ ዘገባዉን ለማዳመጥ ከላይ ያለዉን የድምፅ ዘገባ ይጫኑ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ