1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥርጭቱ እና መከላከያዎቹ

ዓርብ፣ የካቲት 13 2007

ኢቦላ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍባቸው መንገዶች እንደ ደም፣ ምራቅ፣ ላብ ወይንም የወንድ የዘር ፈሳሽ ባሉ ከሰውነት ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር ንክኪ በመፍጠር ነው።

https://p.dw.com/p/1Eelt
Infografik Ebola Ansteckungswege amharisch

በአሁኑ የምዕራብ አፍሪቃ የኢቦላ ወረርሽኝ በርካታ ሰዎች በተሐዋሲው የተጠቁት ከተጠቀሱት መንገዶች በአንደኛው ነው። ሐኪሞች እና ከኅመምተኞች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በተለይ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው።

የተሐዋሲው ተጨማሪ የመሠራጪያ መንገዶች የሚከተሉትንም ያካትታል:

  • የግብረ-ሥጋ ግንኙነት
  • በሥርዓተ-ቀብር ወቅት ወቅት አስክሬንን መንካት
  • በተሐዋሲው የተበከሉ ቁሳቁሶችን እና አካባቢዎችን በመንካት፤ ለምሳሌ፥ አንድ ሰው ቀደም ሲል በኢቦላ ኅመምተኛ የተነካ የበር እጀታን ቢነካ እና በነካ እጁ መልሶ አይኑን አለያም አይኗን ቢያሹ ተሐዋሲው ይዛመታል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ፍራፍሬ በሊታ የሌሊት ወፎች የተሐዋሲው ተፈጥሯዊ አመላላሾች ናቸው። በሌላ አነጋገር ያ ማለት የተሐዋሲው ተፈጥሯዊ ተሸካሚዎች ናቸው። ጦጣዎች፤ ሰዎች በተሐዋሲው የተጠቁ ጦጣዎችን አለያም ተሐዋሲው ያለባቸው የዱር አውሬዎችን ሥጋ ሲመገቡ ተሐዋሲውን ሊያስተላልፉ የሚችሉ «የአጋጣሚ» አስተናጋጆች የሆኑ ይመስላል። እንደ አይጠ-መጎጥ ያሉ ትንንሽ እንስሳትም የተሐዋሲው ተሸካሚዎች ናቸው ተብሎ ይታሰባል። የመጀመሪያው የኢቦላ ስርጭት ምልክት የታየው ሰዎች የእነዚህን እንስሳት ሥጋ ሲመገቡ የተከሰተ ነው ተብሎ ይታመናል። .

የኢቦላ ተሐዋሲ መከላከያ አልባሳቶች ለሐኪሞች እና ኅሙማን ተንከባካቢዎች
የኢቦላ ተሐዋሲ መከላከያ አልባሳቶች ለሐኪሞች እና ኅሙማን ተንከባካቢዎች
  • አንድ ወሳኝ እውነታ፤ አንድ ኅመምተኛ የመጀመሪያዎቹ የተሐዋሲው ምልክቶች ካልታዩበት አስተላላፊ አለመሆኑ ነው።
  • የወባ ትንኝ ወይንም ሌሎች ነፍሣቶች የኢቦላ ተሐዋሲን ማስተላለፍ ስለመቻላቸው ምንም አይነት ማስረጃ የለም።

ጥብቅ የሆነ የንፅህና አጠባበቅ የተሐዋሲውን ሥርጭት ለመከላከል ወደር የማይገኝለት አማራጭ ነው። ተሐዋሲው በተለይ ወረርሽኝ በሆነባቸው አካባቢዎች እጆችን በክሎራይድ ውኃ፣ በሣሙና እና በሽታ አምጪ ተሐዋሣትን ገዳይ በሆነ ንጥር በመደበኛነት መታጠብ ያስፈልጋል። ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን እና ጊኒ ውስጥ በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች አቅራቢያ በክሎራይድ ውኃ የተሞሉ በርሜሎች ተዘጋጅተዋል። በእነዚህ ሃገራት በርካታ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች እጅ ለእጅ መጨባበጥ ትተው «እጅን የማያካትት» ሠላምታ ጀምረዋል።

የላይቤሪያ ፕሬዝዳንቲት ኤለን ጆንሶን ሲርሊፍ «እጅን የማያካትት» ሠላምታ ለአሜሪካዊቷ ሳማንታ ፓወር ሲያሳዩ
የላይቤሪያ ፕሬዝዳንቲት ኤለን ጆንሶን ሲርሊፍ «እጅን የማያካትት» ሠላምታ ለአሜሪካዊቷ ሳማንታ ፓወር ሲያሳዩምስል picture-alliance/AP Photo /Abbas Dulleh

የላስቲክ ጓንቶች እና የፊት ጭምብሎች ተሐዋሲውን ለመከላከል መቶ በመቶ አስተማማኝ ናቸው ማለት አይቻልም። የመከላከያ ቱታም ቢሆን አስተማማኝ ጋሻ የሚሆነው በትክክለኛ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ ብቻ ነው። ይኽ ደግሞ የተለየ ስልጠና ያስፈልገዋል። ከኅመምተኛው ጋር ንክኪ ከተፈጠረ በኋላ መከላከያ አልባሳቱን ማውለቁ ውስብስብ እና ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ ነው። የላስቲክ ቱታው ሊለበስ የሚችለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ወዲያውኑ ሊወገድ ይገባል።

ኢቦላ በተዛመተባቸው ቦታዎች የሚከተሉት መሠረታዊ መመሪያዎች መተግበር አለባቸው

  • እቃዎችን እና ሌሎች ሰዎችን አለመንካት
  • የገዛ ፊትን አለመንካት
  • መደበኛ በሆነ መልኩ እጆችን መታጠብ!

የኢቦላ ተሐዋሲ ወደ ሰውነት ሊገባ የሚችለው ክፍት በሆኑ ቁስሎች፣ በዓይኖች፣ በአፍንጫዎች፣ በአፎች ወይንም በሌሎች የሰውነት ቀዳዳዎች ብቻ ነው።