1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦንብ ፍንዳታ በባሕር ዳር ከተማ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2009

ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የሙዚቃ ድግስ ከሚቀርብበት አዳራሽ ውጪ በተከሰተ የቦንብ ፍንዳታ ሁለት የፀጥታ ጥበቃዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/2cFQh
Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል Tesfaye Shiferaw

ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ ሁለት የጸጥታ ሠራተኞች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ተገለጠ። ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የዐይን እማኞች ባላገሩ ቢራን ለማስተዋወቅ ከተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ አካባቢ የነበሩ ሌሎች ሰዎችም የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ብለዋል። የአማራ ብሔራዊ ክልልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የቦንብ ፍንዳታው መከሰቱን ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል። እንደ እሳቸዉ ግን የተጎዱት ሁለት የፀጥታ ሠራተኞች ብቻ ናቸው።

«እንደተባለው የሙዚቃ ድግስ ነበረ፤ በሙዚቃ ድግሱ አካባቢ  ከውጭ በኩል የቦንብ ፍንዳታ ተከስቷል። ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት የፀጥታ አባላት ወደ ሕክምና መስጫ ተወስደው ከታከሙ በኋላ  ተመልሰዋል። ጤንነታቸውም በጥሩ ኹኔታ ላይ ነው ያለው።  እና ክስተቱ እውነት ነው። በቦታው ላይ  በጥበቃ ላይ የነበሩ ናቸው። ሌላ የደረሰ ጉዳት የለም። የፀጥታ መዋቅሩ በቦታው ያረጋገጠልን ምንም አንዳችም ጉዳት እንዳልደረሰ ነው።»

ፍንዳታው የተከሰተው ሚሌኒየም አደባባይ በሚባለው ሥፍራ የሙዚቃ ድግስ እየተካሄደ እንደኾነ ኃላፊው አክለው ተናግረዋል። የሙዚቃ ድግሱ የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ባላገሩ የተሰኘ ቢራን ለማስተዋወቅ  ያሰናዳዉ ነበር። የዳሸን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ዘሪሁን ፍንዳታ ስለመከሰቱ ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «እኛ ስለ እሱ መረጃ የለንም» ብለዋል።

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

«የምናቀው ስለ ሙዚቃ ዝግጅቱ ብቻ ነው» ያሉት አቶ አብርሃም «እንደዚህ አይነት ነገር ተከስቶም ከኾነ የፀጥታ ኃይላት እንጂ እኛ መረጃ የመስጠት ኃላፊነቱ የለንም። እንደሚያውቁት እኛ ዝግጅት ነበረን። ዝግጅታችንን አጠናቀን ነው የተለያየነው።  ያው እናንተም እንደምታውቁት እንደዚህ አይነት መረጃ ለመስጠት  የእኛ ሥራ አይደለም፤ ሥልጣንም አይደለም» ሲሉ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ የኾኑ የዐይን እማኞች ፍንዳታው የደረሰው ከባጃጅ ታክሲ ላይ በተወረወረ ቦንብ ነው ይላሉ። በበነጋታው እሁድም እዛው ባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 ማደያው አካባቢ ሌላ ፍንዳታ መድረሱንም ተናግረዋል። አቶ ንጉሡ አሉባልታ ብለውታል። 

«አካባቢው በአጠቃላይ በቀውስ ውስጥ ያለ መስሎ  እንዲታይ እና ሠላም የታወከ  እንዲመስል ነገሮችን ለማግዘፍ የሚደረግ አሉባልታ ካልሆነ በስተቀር ይኼ የተከሰተው ቅዳሜ ዕለት ነው። ከቅዳሜ ወዲህ ባሉት በእሁድ እና በትናንትናው ቀን ዛሬን ጨምሮ የተከሰተ አንዳችም ነገር የለም።»

አቶ ንጉሡ ፍንዳታውን በማድረስ የተጠረጠሩ ሰዎች ተይዘው እንደኾን ተጠይቀው ሲመልሱ ዝርዝሩ በፀጥታ መዋቅሩ እጅ ያለ መኾኑን ተናግረዋል። ከባሕር ዳሩ ፍንዳታ ቀደም ብሎ በጎንደር ከተማ በተደጋጋሚ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ የተነሳ አዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ከተማዪቱ በዚህ ወቅት የመጓዛቸውን አስፈላጊነት በጥንቃቄ እንዲያጤኑ መምከሩ የሚታወስ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ