1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብልጽግናና የህወሓት ባለሥልጣናት ዉይይት

ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2016

ከጦርነቱ መቆም 17 ወራት በኃላ የቀድሞ ተዋጊዎቹ ትግራይን የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ትላንት በመቐለ ቀጣይ ፖለቲካዊ ውይይት በሚያደርጉበት ጉዳይ ዙርያ በከፍተኛ አመራሮቻቸው በኩል ንግግር አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/4eOh5
የብልፅግናና የሕወሓት ፓርቲዎች ባለስልጣናት ፖለቲካዊ ወይይት ለማድረግ ተስማምተዋል
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ገዢ የብልፅግና ፓርቲና የትግራይ ገዢ ፓርቲo ህወሓት አርማዎች

የብልጽግናና የህወሓት ባለስልጣናት ዉይይት

                   

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራሕ የመሩት የመልዕክተኞች ጓድ ትናንት መቀሌ ዉስጥ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይቷል።ህወሓት በፅሑፍ ባወጣዉ መግለጫ ሁለቱ የቀድሞ ባላንጣ ፓርቲዎችየፖለቲካ ንግግር ለማድረግ መስማማታቸዉን አስታዉቋል።የሁለቱ ደም የተቃቡ ፓርቲዎች ባለሥልጣናት ውይይት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ገቢራዊነት ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ተነግሯልም።የትናንቱ ዉይይት «የፖለቲካ» የተባለዉ ንግግር መጀመሪያ መሆን አለመሆኑ ግን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።

 

ከጦርነቱ መቆም 17 ወራት በኃላ የቀድሞ ተዋጊዎቹ ትግራይን የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይእና የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ትላንት በመቐለ ቀጣይ ፖለቲካዊ ውይይት በሚያደርጉበት ጉዳይ ዙርያ በከፍተኛ አመራሮቻቸው በኩል ንግግር አድርገዋል። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ አጭር የፅሑፍ ማብራርያ የሰጠው ህወሓት፥ በፕሪቶርያው ውል መሰረት ህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ፖለቲካዊ ውይይት ሊያደርጉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልክቷል።

 

እንደ ህወሓት ገለፃ በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ የገዢው ፓርቲ ልኡክ፥ ትላንት በመቐለ ከህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት የዘገየው የሁለቱ አካላት ፖለቲካዊ ውይይት በአጭር ግዜ እንዲጀመር ተግባብተዋል ብሏል። በዚህ የትላንቱ የህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ ውይይት ዙርያ ከገዢው ብልፅግና ፓርቲ እስካሁን የተባለ ነገር የሌላ ሲሆን ወደ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም። ህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ ከጦርነቱ መቆም በኃላ በይፋ ፓለቲካዊ ንግግር መጀመራቸው ሲገለፅ ይህ የመጀመርያ ነው። የሕግ ምሁሩ ሙስጠፋ ዓብዱ በሁለቱ ሐይሎች መካከል ያለው ፓለቲካዊ ልዩነት ሊፈጥረው የሚችል አደጋ እንደቀላል የማይታይ ነው የሚሉ ሲሆን፥ ከጦርነት መልስ ባሉ ሁሉም አጀንዳዎች ዙርያ ተነጋግረው ችግሮች ሊፈቱ እንደሚጠበቅ ያነሳሉ።

ሁለት ዓመታት ባስቆጠረዉ በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ከወደሙ የጦር መሳሪያዎች አንዱ
የብልፅግናና የህወሓት ፓርቲዎች ባለሥልጣናት የጫሩት ጦርነት ለሁለት ዓመት ሰሜን ኢትዮጵያን አንድዷልምስል Amanuel Sileshi/AFP

 

እንደ የሕግ ምሁሩ አስተያየት ህወሓት እና የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግናበስልጣን ክፍፍል ጨምሮ በሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ዙርያ በቀጣይ ሊወያዩ እንደሚጠበቅ ያነሳሉ።የፕሪቶሮያው የሰላም ስምምነት በህወሓት እና የፌደራል መንግስቱ መካከል ተደርጎ እያለ፥ ህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ በስምምነቱ መሰረት ፓለቲካዊ ውይይት ሊያደርጉ መሆኑ መገለፁ ለምንድነው ለሚልና ሌሎች ጥያቄዎች ከህወሓት ወገን ዝርዝር ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልሰመረም።

 ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ