1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግጭቱ ሰዎች ሞተዋል፤ ቆስለዋልም

ዓርብ፣ ኅዳር 8 2010

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ከተማ ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት ፍርሃት የገባቸው ነዋሪዎች ከተማይቱን ለቅቀው እንዳይወጡ ከንቲባው ጠየቁ፡፡ በባቱ ያለው ሁኔታ መረጋጋቱን ለዶይቼ ቬለ የተናገሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች ግን ስጋት ያለባቸው የደቡብ ክልል ተወላጆች ከከተማይቱ እየወጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2nq1z
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በግጭቱ ሰዎች ሞተዋል፤ ቆስለዋል

ዝዋይ በተሰኘ የቀድሞ መጠሪያዋ ይበልጡኑ በምትታወቀው በባቱ ከተማ ያሉ የደቡብ ክልል ተወላጆች ከሰሞኑ ከነበረ ግጭት ጋር በተያያዘ ከተማውን እየለቀቁ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ከተማውን ለቅቀው ሊሄዱ የነበሩ ነዋሪዎችም ከከተማይቱ ከንቲባ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ስማቸው እንዳይነገር የጠየቁ አንድ የባቱ የከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ትላንት ሐሙስ ምሽት በግጭቱ ምክንያት ከከተማይቱ ለመልቀቅ ሲዘጋጁ የነበሩ ነዋሪዎች ተመልክተዋል፡፡

እኔ ራሴ ማታ በከተማ ውስጥ በመኪና ውር ውር ስል ዕቃቸውን ሲጭኑ ደርሼባቸዋለሁ፡፡ የሆኑ ጥበቃዎች ነበሩ በየቦታው ቁሳቁስ እንዳይነሳ፣ ምንም ችግር እንዳይኖር የሚጠብቁት ፖሊሶች ነበሩ፡፡ አንድ ሁለት ሰዎች ይዤ በመኪና ደረስኩባቸው፡፡ ‘እነዚህን ሰዎች አስታግሷቸው፣ እንዳይሄዱ፤ አሁን ሰላም ነው’ ብዬ ሰዎችን አጠገባቸው ወሰድኩኝ፡፡ ሰዎቹ ለመኑ፤ ፖሊሶችም ሲለምኑ ‘አይ! እኔ በቂ ስራ እዚህ አለኝ፡፡ ልጆቼችን ብቻ እሸኛለሁ’ አለኝ በአይሱዙ ዕቃውን የሚጭነው ባለቤቱ፡፡ በቃ አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም ደስ የማይል ነው፡፡ የእነርሱ መነሳት በጣም አሳዝኖናል፡፡ በብዛት እየሄዱ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ፈርተው ነው፡፡”

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የከተማው ነዋሪ ትላንት ሐሙስ ከባቱ ለቅቀው ወደ ሌላ ቦታ ሊሄዱ ተዘጋጅተው የነበሩ የደቡብ ተወላጆች ከባቱ ከንቲባ አቶ ኦሾ ከዲር እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ያስረዳሉ፡፡ መኖሪያቸውን በፍርሃት የለቀቁ ሰዎች በአንድ ቦታ አለመጠለላቸውንም ይገልጻሉ፡፡  “እነርሱ እንሄዳለን ብለው ዕቃቸውን ጭነው ሲሄዱ የከተማው ከንቲባ፣ የከተማው አስተዳደር ‘እንዳትሄዱ፣ ሀገር ሰላም ነው፣ ወደ ስራችሁ ትመለሳላችሁ፣ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን’ በሚል ትላንት እንዳይሄዱ ተደርገዋል፡፡ ትላንትናም ይሄዳሉ የተባሉት የወጣቶች ማዕከል ተብሎ ይገነባ የነበረው ቦታ ላይ ነው ለተወሰኑ ሰዓታት ስብሰባ አይነት ነገር ተደርጎላቸው የወጡት እንጂ ተጠልለው የተቀመጡበት ሁኔታ የለም፡፡ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡”

የባቱ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ አለማየሁ ታደለ በሰሞኑ ግጭት ከተማውን ለቅቀው ለመውጣት ተዘጋጅተው የነበሩት ጥቂት ሰዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ትላንት ከደቡብ ክልል ተወላጆች ጋር በወጣቶች እና ስፖርት ጽህፍት ቤት ግቢ በነበረ ውይይትም ነዋሪው እንዲረጋጋ መልዕክት እንደተላለፈ ተናግረዋል፡፡ “ሶስት ቤተሰቦች ናቸው እንሄዳለን ብለው ተነስተው የነበረው፡፡ እነኛን ቤተሰቦች ‘አትሂዱ፣ እዚሁ ከህብረተሰቡ ጋራ ተዋልዳችሁ ኖራችኋል፡፡ ዛሬም ደግሞ ወደዚያ ብትሄዱ ለእናንተም ላይጠቅም ይችላል፡፡ እዚሁ የነበረውን እንቅስቃሴያችሁን ብትቀጥሉ ጥሩ ከሚል አንጻር ነበር፡፡”  

በባቱ ግጭት የተቀሰቀሰው ባለፈው እሁድ ህዳር 3 ነበር፡፡ በዕለቱ በነበረው ግጭት  ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸው ቢታወቅም በብዛታቸው ላይ ግን የተለያዩ ቁጥሮች ይቀርባሉ፡፡ በግጭቱ የሞቱትን ሰዎች ከአራት እስከ ሰባት የሚያደርሱት አሉ፡፡ የባቱ ከተማ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሰራተኛ ግን ሟቾቹ ሁለት ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ በግጭቱ የንግድ ቤቶች መቃጠላቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ሁሉም የሚስማሙበት ግን የግጭቱ መንስኤ የሁለት ግለሰቦች ጠብ መሆኑን ነው፡፡ 

ከወር በፊት በሁለት ወጣቶች መካከል በነበረ ጠብ የእግር መሰበር ጉዳት የደረሰበት ወጣት ህይወቱ ማለፉ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡  “ልጁ እግሩ ተሰበረ እና ወደ ወላይታ የአጥንት ሀኪም ወዳለበት ሆስፒታል ተወሰደ፡፡ ልጁ በወሩ ሞቶ [አስክሬኑ] መጣ፡፡ ጠቡ ከዚያ ነው የተነሳው፡፡ የልጁ ሬሳ እሁድ መጣ፡፡ ከዚያ እነዚህ ምንም የማያውቁ ልጆች፣ ወዲህና ወዲያ የሚሮጡ ልጆች ናቸው በልጁ ምክንያት ረብሻ ያመጡት” ብለዋል፡፡ 

ሰሞኑን በከተማው በነበረው አለመረጋጋት ከወጣቱ ሞት ሌላ በከተማይቱ ዳርቻ ያለው የሼር የአበባ እርሻ ሠራተኞች የደመወዝ ይጨመርልን ጥያቄም ሰበብ እንደሆነ ሌላኛው የከተማይቱ ነዋሪ ይገልጻሉ፡፡ ግጭቱን ለመቆጣጠር ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ አባላት በከተማይቱ እንደተሰማሩ ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡ በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች አሁን በከተማይቱ መረጋጋት ይታያል ብለዋል፡፡ በባቱ ሰላም መስፈኑን የሚናገሩት የከተማዋ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሠራተኛም በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችም ከሆስፒታል መውጣት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ