1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር ኢትዮጵያዊውን ይሸልማል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 2009

የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር የህዋ እና ምድር ሳይንስ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በዓለም ትልቁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ማህበሩ ባለፈው ሳምንት ለሽልማት ከመረጣቸው 29 ሳይንቲስቶች እና ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር መልሰው ንጉሴ ይባላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2hCN0
Symbolbild | gravitational waves are ripples in the curvature
ምስል imago/Science Photo Library

ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፉ።

ዋና መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር በ139 ሀገራት ያሉ 60 ሺህ አባላት ያሉት ግዙፍ የሙያ ተቋም ነው፡፡ የህዋ እና ምድር ሳይንስን ማሳደግ ዓላማው ያደረገው ማህበሩ በሚያሳትማቸው የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) እና በሚያካሄዳቸው ስብሰባዎቹ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ በዓመት እስከ 10 የሚደርሱ ስብሰባዎች ቢያዘጋጅም በዘርፉ ባለሙያዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ግን በየዓመቱ በታህሳስ ወር መጀመሪያ የሚካሄደው ነው፡፡ 

ከማህበሩ የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ 24 ሺህ ገደማ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ ይህን ስብሰባ ማህበሩ ለባለሙያዎች ሽልማት ለማበርከትም ይጠቀምበታል፡፡ ማህበሩ የጎርጎሮሳዊው 2017 ተሸላሚዎችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገዉ ግን ባለፈው ሳምንት ነዉ።፡

Wirtschaftstagesreportage DWi Antenne Symbolbild
ምስል DW

“በህዋ እና ምድር ሳይንስ ስኬት አስመዝግበዋል፣ ሳይንስን ለሰው ልጅ ጠቀሜታ በማዋል አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ከተባሉት 29 ተሸላሚዎች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር መልሰው ንጉሴ ናቸው፡፡ ዶ/ር መልሰው ተመራማሪ እና መምህር ናቸው፡፡ እያስተማሩበት በሚገኘው የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር ያለ የምርምር እና ጥናት ተቋምንም ይመራሉ፡፡ 

የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር አባል እና በቦስተን ኮሌጅ ስር ባለው የሳይንሳዊ ምርምር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ስለተመረጡበት ሽልማት ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

“የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ሽልማቶች አሉት፡፡ ነገር ግን አፍሪካ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ፡፡ በህዋ ሳይንስ እና በጂአሎጂ በየዓመቱ ሁለት ሽልማት ይሰጣል፡፡ ሽልማቱ መካሄድ ከጀመረ አሁን ሁለተኛ ዓመቱ ነው፡፡ ዶ/ር መልሰው ለዚህ ሽልማት ሁለተኛ አሸናፊ ነው፡፡ 

በጎርጎሮሳዊው 1919 የተቋቋመው የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር በተለያየ ደረጃዎች ከፋፍሎ ሽልማት እንደሚሰጥ የሚናገሩት ዶ/ር እንዳወቀ ዶ/ር መልሰው ያገኙት ግን በማህበር ደረጃ የሚሰጥ በመሆኑ “የተከበረ” እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ መምረጫ መስፈርቶች በተመለከተ ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡

“ሽልማቱ የሚሰጠው በአፍሪካ ውስጥ ተምረው አፍሪካ ውስጥ ዶክትሬታቸውን አግኝተው እዚያው አፍሪካ ውስጥ ምርምር የሰሩ፣ ጥሩ ውጤት ላመጡ እና ለሳይንስ ማህበረሰቡ የሰሩት ስራ ጥራቱ ተገምግሞ ያሳተሙት የምርምር ውጤት፣ እንደገና የሚያማክሯቸው ተማሪዎች ካሉ ይታያል፡፡ ሀገራቸው ውስጥ ሆነው ሳይንስ እንዲያድግ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ፣ እንደገና ዋናው እና ጠቃሚው ደግሞ ለምርምር የሚሆናቸውን ገንዘብ ማግኘት መቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ዓመት ካመለከቱት አመልካቾች ውስጥ ዶ/ር መልሰው በእነዚህ ነጥቦች ልቆ በመገኘቱ አሸናፊ ሆኗል፡፡”

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲው ዶ/ር መልሰው ለሽልማት ካበቋቸው ውስጥ አንዱ የምርምር ስራቸው ነው፡፡ በሽልማቱ እውቅና ያገኘውን ምርምር የጀመሩት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ እያሉ ነበር፡፡ አምስት ዓመት ግድም ስለወሰደው ምርምር ዶ/ር መልሰው እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

Gravitationswellen
ምስል picture-alliance/dpa/CALTECH-JPL

“በዋናነት እኔ እየሰራሁት ያለሁት ስራ አንደኛው በላይኛው የመሬት የአየር ክልል ላይ የሚገኙ ኤልክትሮን የምንላቸው ወይም ቅንጣት አካላት አሉ፡፡ በተፈጥሮ እዚያ የሚገኙ ማለት ነው፡፡ እና የእነዚህ ቅንጣት አካላት በቦታ እና በጊዜ መቀያየር በዚያ አየር ክልል ውስጥ ቆርጦ የሚሄደውን ወይም የሚያልፈውን ሬድዮ ሞገድ ወይም ሬድዮ የምንለውን ያደናቅፉታል፡፡ የሚያደናቅፉት ከሆነ ያንን የሬድዮ ሞገድ ተጠቅመን የምንሰራውን ስራ በትክክል ልንሰራ አንችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን አደናቃፊ አካል ማደናቀፉን ለመግታት የእነዚህን ቅንጣት አካላት በጊዜ እና በቦታ መቀያየር ማወቅ መቻል አለብን፡፡ የእኔ ስራ ምንድንነው የነበረው? የእነዚህን አካላት ብዛታቸውን፣ በጊዜ እና በቦታ እና ይሄ ነው ብሎ መተንበይ የሚያስችል ሞዴል ነው የሰራሁት፡፡”

ዶ/ር መልሰው ይህን ጥናት ጨምሮ ሶስት የምርምር ስራዎቻቸውን የአሜሪካ የጂኦፊዚካል ማህበር በሚያሳትማቸው የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር መልሰው ከምርምር ስራቸው ሌላ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር ባለው የዋሸራ የጂኦስፔስ እና የራዳር ሳይንስ የምርምር ቤተ-ሙከራ ዳይሬክተር ናቸዉ፡፡  የምርምር ተቋሙ የተመሰረተው ከ 10 ዓመት በፊት ነው፡፡ ቤተ-ሙከራው አሁን የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ በሚገኙት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ አነሳሽነት እና በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ፍላጎት ባላቸው ባለሙያዎች የተመሰረተ ነው፡፡ ስለ ተቋሙ ስራ ዶ/ር መልሰው ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

“አጠቃላይ ጥናቱ ምንድነው? የህዋ ሳይንስ ላይ ምርምር ማካሄድ ነው፡፡ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መጥቷል፡፡ ከምርምሩ በተጨማሪ በማስተርስ እና በፒ.ኤች.ዲ ፕሮግራም ተማሪዎችን ያስተምራል፡፡ በዋናነት አተኩረን እየሰራን ያለነው የላይኛው የመሬት የአየር ክልል በቴክኖሎጂ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ ወደፊት ጥሩ ለማድረግ የሚያስችል ምርምር እያደረግን ነው ያለነው፡፡”  

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ መነቃቃት ያለ ይመስላል፡፡ እንደዋሽራ አይነት ተቋማት ብቅ ብቅ ማለታቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ የህዋ ሳይንስ ዘርፉ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር “የቅንጦት” ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የእነ ዶ/ር መልሰውን አይነት ጥናትን ፋይዳም ያጠይቃሉ፤፤ ዶ/ር መልሰው ዘርፉ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ የምርምር ዘርፍ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ሆኖም በጣም ብዙ ወጪ የማያስወጡ ዘዴዎችን በመጠቀም በዘርፉ ላይ ጥናት ማካሄድ ይቻላል ይላሉ፡፡ ዘዴዎቹን ይዘረዝራሉም፡፡  

Installation Teleskope in Addis Abeba
ምስል DW/Getachew Tedla Hailegiorgis

“አንደኛ ይህ ጥናት እንደምታየው ዓለም አቀፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ፣ የአሜሪካ ወይም የጀርመን ብቻ የምትለው አይደለም፡፡ ስለዚህ እዚህ አካባቢ የሚጠናው ጥናት ለአሜሪካ ወይም ለጀርመን የሚጠቅም ስለሆነ ሰዎቹ በቀላሉ ከእኛ ጋር በትብብር ይሰራሉ፡፡ በዚያም እኛ ጋር ብዙ መሳሪያዎች አሉ፡፡ ራዳራ፣ ጂ.ፒ.ኤስ ሪሲቨር አለን፡፡ እነዚህን መሳሪያዎች የእኛን አየር ለማጥናት ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪ ይህንን ጥናት ለማጥናት ሲባል የአሜሪካ መንግስት ወይም ጀርመን ሳተላይት ሊያመጥቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የእነርሱን መረጃ እኛ በነጻ ማግኘት እንችላለን፡፡ እዚሁ እኔ ባህር ዳር ቁጭ ብዬ የእነርሱን መረጃ ወደ ኮምፒውተር በመገልበጥ ጥናቱን ማድረግ እችላለሁ፡፡ ስለዚህ የእኛን መሳሪያዎች መጠቀም እችላለሁ ካስፈለገም የሌላ ሀገር መሳሪያን መረጃ በመጠቀምም ስራ መስራት እችላለሁ፡፡”

የዶ/ር መልሰው ስም ከተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ባለፈው ሳምንት ይገለጽ እንጂ የሽልማት ስነስርዓቱ የሚካሄደው ከአምስት ወር በኋላ በአሜሪካው ኒው ኦርሊያንስ ከተማ በሚካሄደው የማህበሩ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ዶ/ር መልሰው ሽልማቱ የፈጠረባቸውን ስሜት እንዲህ አጋርተዋል፡፡ 

“ለእኔ በጣም ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ትርጉም የሚኖረውም አንደኛ እኔ በምስራበት የምርምር ዘርፍ ላይ የመጨረሻው ዘርፍ ላይ ያሉበት ማህበር ነው፡፡ እና እነዚያ ሰዎች የእኔን ስራ ዋጋ ሰጥተውት ለዚህ ሽልማት ሲያበቁኝ ለእኔ ትልቅ የሆነ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡” 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ