1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢሊየን ዛፍ ተከላ ዘመቻ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2007

የቢሊዮን ዛፍ ተከላ ዘመቻ ይፋ ከሆነ 9 ዓመቱን የፊታችን ኅዳር ወር ይደፍናል። በተለያዩ ሃገራት የችግኝ ተከላዉ በተጀመረ በሶስት ዓመቱ ነዉ ሰባት ቢሊዮን መድረሱ የተሰማዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በዘንድሮዉ የክረምት ወቅት ብቻ ሶስት ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ የሰሞኑ ዜና ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GHQ9
Wiederaufforstung in Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/Maxppp Ef Afrimages

የቢሊየን ዛፍ ተከላ ዘመቻ

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2006ዓ,ም በናይሮቢ ኬንያ በተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ነበር የዛፍ ችግኝ ተከላ በዘመቻ እንዲከናወን የተወሰነዉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመቻዉን እንዲጀመር ያስተባበረዉ የዓለም እርሻ እና ኢንዱስትሪ ማዕከል ሲሆን ለዘመቻዉ የበላይ ጠባቂነትም ኬንያዊቱ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ዋንጋሪ ማታይ እና የሞናኮዉ ልዑል አልበርት ተሰይመዉ ነበር። ዋንጋሪ ማታይ በተመሳሳይ የዘመን ቀመር በ2011 ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም። ማታይ በሕይወት ዘመናቸዉም የአረንጓዴ ቀለበት ንቅናቄ የተሰኘ ሌላ ተመሳሳይ ዓላማ ያለዉ እንቅስቃሴ መሥርተዉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸዉም ይነገርላቸዉ። የቢሊዮን ዛፍ ተከላዉ ዘመቻ እንቅስቃሴዉ በተጀመረ በሶስት ዓመቱ ገደማ ነዉ ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ዛፎችን በላይ በመትከል ከተወደሱት ሃገራት አንዷ መሆኗ የተሰማዉ። ያኔም 1,4 ቢሊዮን ዛፎች እንደተተከሉ ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ቱርክ 711 ሚሊዮን፤ ሜክሲኮ ደግሞ 537 ሚሊዮን ዛፎችን መትከላቸዉ በወቅቱ ተመዝግቧል። ኬንያ፣ ኩባ እና ኢንዶኔዢያም ስማቸዉ በበጎ ተጠርቷል። ቻይናን ግን የቀደማት የለም፤ መንግሥት 260 ዓይነት የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን በ11 የቻይና ክፍለ ሃገራት አስተክሏል። ያኔ በተመዘገበዉ መሠረት በስምንት ወራት ዉስጥ 6,1 ቢሊዮን ዛፎች የተከለችዉ ቻይናም፤ 2,6 ቢሊዮኑ በዓለም አቀፉ ዘመቻ ስም እንዲያዝላት አድርጋለች። ያም በቢሊዮን ዛፍ ዘመቻዉ በመላዉ ዓለም የተተከሉትን ዛፎች ቁጥር 7,3 ቢሊዮን አድርሶታል።

Symbolbild Abholzung Holzhandel CAR Zentralafrikanische Republik
ደኑ የተራቆተዉ የአፍሪቃ ገጽታምስል picture-alliance/dpa/T. Koene

የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሃግብር በመዘገበዉ መሠረትም እስከአሁን አስራ አራት ቢሊየን፤ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሚሊዮን፤ አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሺህ፤ ዘጠኝ መቶ ሰባ አራት ዛፎች በመላዉ ዓለም ተተክለዋል። ለዚሁ የችግኝ ዘመቻ ከተዘጋጀዉ ከድርጅቱ ድረ ገጽ ላይም እያንዳንዱ ሀገር በየዘርፉ እና ዓመቱ ተከልኩ ያላቸዉን ችግኞች ብዛት ዝርዝርም ማየት ይቻላል። የኢትዮጵያም የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ተቋማትን የወከሉ ስሞች እንተክላለን ብለዉ ቃል የገቡት እና የተከሏቸዉ ችግኞች ብዛትም ተዘርዝሯል። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2007 እስከ 2013 ድረስም በዚህ ሰንጠረዥ መሠረት አንድ ቢሊየን፤ መቶ ሃምሳ ስምንት ሚሊየን፤ ስምንት መቶ ሃያ ሺህ፤ ስድስት መቶ አርባ ስምንት ችግኞች መተከላቸዉ ተመዝግቧል። በያዝነዉ ዓመት የክረምት ወቅት ሶስት ቢሊየን ችግኝ መተከሉ ደግሞ የሰሞኑ ዜና ነዉ። የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የደን ዘርፍ ሚኒስትር ዴታ አማካሪ ዶክተር ተፈራ መንግሥቱ እንደዉም ዘንድሮ ቁጥሩ አንሷል ነዉ የሚሉት።

Papua-Neuguinea Dschungel Luftaufnahme Symbolbild Suche nach Flugzeug
ምስል Imago

እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ለመከታተል ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ሚኒስቴርን ካቋቋመች ሁለት ዓመት ሆናት። ችግኞች መተከላቸዉ ብቻ ሳይሆን ተከታትሎ ለማፅደቅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ዓመት አስቀድሞ የወሰዳቸዉ ርምጃዎች አሉ ይላሉ ዶክተር ተፈራ።

ችግኞች እንደሚተከሉት ብዛት አለመጽደቃቸዉ የሚያሳስባቸዉ በርካቶች ናቸዉ። ዛፎች ከተተከሉ ጸድቀዉ ለዉጤት መብቃት እንዳለባቸዉ እናምናለን ያለን ጤና ግፍሌና ቀበናን እናጽዳ የተሰኘዉ ማኅበር ኃላፊ ደሳለኝ ፍሬዉ ዘንድሮ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ችግኞችን የተከሉት በተመረጡና የተወሰኑ ቦታዎች እንዲሁም በግለሰቦች ኃላፊነት መሆኑን ገልጸሎናል።

እንደተባለዉ ችግኞቹን መትከሉ አንድ ነገር ሆኖ መጽደቃቸዉን መከታተሉ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚጠይቅ ሥራ ይሆናል። ስለሶስት ቢሊዮን ችግኞች መተከል ያነጋገርኳቸዉ የደን ባለሙያ ቁጥሩ መበርከቱ ትንሽ የተጋነነ እንደሚመስል ጠቁመዉ፤ በሙያቸዉ ሲያሰሉትም 1,2 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን መሬት እንደሚሸፍን ነዉ የገለፁልኝ። ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን ከልብ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ