1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለዉ የዩኒቨርስቲዎች ተቃዉሞ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 5 2010

አዲሱ የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ወዲህ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በሚነሱ ግጭቶችና ተቃዉሞዎች ሳቢያ ትምህርት በአግባቡ እየተሰጠ አለመሆኑ አሳስቦናል ሲሉ የተለያዩ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለፁ። በአምቦና በመቱ ዩኒቨርስቲዎችም ተቃዉሞዎች መቀጠላቸዉን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2ndDa
Äthiopien Oromiya MBO Universität
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

MMT university studentas protest - MP3-Stereo

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደገለፁት የዘንድሮዉ የትምህርት ዘመን በአግባቡ አልተጀመረም። በአምቦ ዩኒቨርስቲ የ3ተኛ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኝ ተማሪ እንደሚለዉ አዲሱ የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ወዲህ ከአንድ ሳምንት ያለፈ ትምህርት አልተማሩም። ችግሩን ለመፍታት ከፌደራልና ከክልል ከመጡ ባለስልጣናት ጋር ዉይይት ተደርጎ ትምህርት ለጊዜዉ ተጀምሮ እንደነበር አስታዉሶ በትናንትናዉ ዕለት ግን ተማሪዎች ከፓሊሶች ጋር በመጋጨታቸዉ ተመልሶ ትምህርት መቋረጡን  ይናገራል።

ተቃዉሞ ከተካሄደባቸዉ ዩንቨርሲቲዎች አንዱ  በሆነዉ  በወለጋ ዩኒቨርሲቲ  አንድ የ5ተኛ  ዓመት የጤና ሳይንስ ተማሪ  እንደሚያስረዳዉ የአካባቢዉ ህብረተሰብ በያዝነዉ ዓመት መጀመሪያ  በመንግስት ላይ ያነሳዉን ተቃዉሞ በመደገፍ የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች ቀደም ሲል ሰልፍ አካሂደዉ ነበር። በተቃዉሞዉ ወቅትም ሰዎች መጎዳታቸዉን ገልጿል። ያም ሆኖ ግን ተማሪዎች ትምህርታችን መቋረጥ የለበትም በሚል ዉሳኔ ከ21 ቀናት በኋላ ትምህርት ቀጥለዋል። እንደ ተማሪዉ ገለጻ ትምህርቱ ቢቀጥልም አሁንም ድረስ ተረጋግቶ የመማር ችግር በአንዳድ ተማሪዎች ላይ ይታያል።

Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ሌላዉ ዶይቼቬለ ያነጋገረዉ የጅማ ዩንቨርሲቲ ተማሪ በበኩሉ የኦሮሚያ ክልል ተማሪወች ሶማሌ ክልል ከሚገኘዉ ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሊማሩ አይገባም በሚል ተቃዉሞ ከ20 ቀን በላይ ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጿል። በተማሪዎቹ የተነሳዉ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ባለለፈዉ ሳምንት ትምህርት መጀመራቸዉን አመልክቷል። ይሁን እንጅ የባከነዉ የትምህርት ጊዜ ሊካካስ ይገባዋል ይላል።

ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመቱ  ዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች እንደሚገልጹት ደግሞ በተያዘዉ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተማሪዎች በግቢዉ ዉስጥ መንግስትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዉ ነበር። በኋላ ላይ ግን በተማሪዎች መካከል ማንነት ላይ ያተኮረ ግጭት መፈጠሩን አመልክተዋል። በግጭቱም 3 ያህል ተማሪዎች ተጎድተዋል ይላሉ። ይህንን ተከትሎ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ችግሩን ሊፈቱ የሞከሩበት መንገድ አድሏዊ ነዉ በሚል ተቃዉሞ መቀጠሉንና አሁንም ድረስ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ  መቋረጡን የሌላዉ የዩኒቨርሲቲዉ የ3ተኛ ዓመት ተማሪ ተናግሯል።

እንደ ተማሪዉ ገለጻ ማንነት ላይ ያነጣጠረዉ ግጭት የጥቂት ተማሪዎች ችግር ነዉ። የአብዛኛዉ ተማሪ ፍላጎት ግን ግጭቱ  በአግባቡ ተፈትቶ ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ ነዉ ሲልም ያስረዳል። ጉዳዩን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊዎችንና የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስተያየት ለማካተት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ