የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ወደ እስር ቤት ሊላኩ ነው
ሐሙስ፣ መጋቢት 27 2010ማስታወቂያ
የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ወደ እስር ቤት ሊላኩ ነው። ዳኞች የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ያቀረቡትን ይግባኝ ዛሬ ማለዳ ውድቅ አድርገዋል። ሉላ ዳ ሲልቫ በቀረበባቸው የሙስና ክስ የ12 አመታት ተፈርዶባቸዋል። ዳ ሲልቫ ለብራዚል ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ጉዳያቸውን ሳይታሰሩ ለመከራከር ጠይቀው ነበር። የ72 አመቱ ግራ ዘመም ፖለቲከኛ ከጎርጎሮሳዊው 2003-2011 ዓ.ም. ባሉት አመታት በብራዚል ፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሔደው የአገሪቱ ምርጫ ዳግም ሊወዳደሩም እቅድ ነበራቸው። ሉላ በሚል የቁልምጫ ስማቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ የቀረበባቸው ክስ እርሳቸውን ከምርጫ ውድድሩ ለማግለል ሆን ተብሎ የተቀነባበረ እና ፖለቲካዊ ግብ ያለው ነው ሲሉ ያጣጥላሉ። በርካታ ብራዚላውያን ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ለደሆች የወገኑ ፖለቲከኛ አድርገው ያደንቋቸዋል።
ይልማ ኃይለሚካኤል
አርያም ተክሌ