የሾንኮራ አገዳ መሬት ግጭት
ሐሙስ፣ የካቲት 2 2009የየአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ የእርሻ መሬቶች ላይ የደረሱት የቃጠሎዎቹ መንስኤ በልማት ስም መሬት ከገበሬዎች ያለ በቂ ካሳ መወሰዱ መሆኑን ይገልፃሉ። በተቃዉሞዉ ወቅት ቃጠሉ ከደረሰባቸው መካከል የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካን ለመመገብ የተተከሉት የሾንኮራ አገዳ እርሻዎች ይገኙበታል። የሾንኮራ ተክሎቹ በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳማና በቦሰት ወረዳዎች እንድሁም በአርስ ዞን ዉስጥ ደግሞ ዶዶታ ወረዳ ዉስጥ እንደምገኝ የፋብሪካዉ ስራ አስኪያጅ አቶ ቱሉ ለማ ጠቅሰው በአከባቢዉ መንግስት በኒልዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘቦችን አፍስሶ የመስኖ መሰረተ ልማት እንደሰራ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።
የ25 ዓመት ወጣት የሆነዉ ይህ የአዳማ ነዋሪ የሾንኮራ እርሻዉ የተቃጠለዉ መሬቱ ከገበሬዉ በጉለበት ስለተወሰደበት ነዉ ይላል።
ይሁን እንጅ የፋብርካዉ ስራ አስካያጅ አቶ ቱሉ ከገበሬዉ «የተወሰደ መሬትም የለም፣ የሚከፈልም ካሳ የለም፣ አሁንም መሬቱ የገበሬዉ ነዉ፣ ግብርም እየከፈለበት ያለዉ ገበሬዉ ነዉ» ይላሉ። ይልቁንስ አከባብዉ ዝናብ አጠር አከባቢ ስለሆነ አርሶ አደሩ ራሱ በመስኖ ቢያለማው የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ህሳቤ ነበረ ይላሉ። በሶስቱም ወረዳዎች 32 የገበሬ ማሃብራት እንዳሉና እነዚህ ማህበራትም አንድ የሾንኮራ አገዳ አምራቾች ህብረት ስራ ማህበር እንዳላቸው ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነዉ፣ ገበሬዎቹንም ሆነ ልጆቻቸዉን አነጋግሬያለሁ የሚሉት እኝህ የአዳማ ነዋሪ ግን ስራ አስኪያጁ አለ ያሉት ስምምነት ቢኖርም ገበሪዎቹ የሚያገኙት ገቢ ግን በጣም ጥንሽ ነዉ ይላሉ።
ይህ የተቃጠለ የሾንኮራ እርሻ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ለሚለዉ አቶ ቱሉ ሲመሊሱ፣ አርሶ አደሩ ራሱ ዳግም ወደ ተከላ እንደገባና ወደ ፊትም ለሚፈጠሩት ችግሮች ፋብሪካዉና የአምራቾቹ ማህበር እየተገናኙ አብረው ይሰራሉ ሲሉ ተናግረዋል ። የአከባቢዉ ነዋሪዎች ደግሞ አርሶ አደሩ ዳግም ተከላው ላይ የተሳተፈው ተገዶ እንጅ ወዶ አይደለም ይላሉ።
የወንጅ ሾዋ ስኳር ፋብርካ የሾንኮራ አገዳ ፍላጎቱ በመጨመሩ የእርሻ መሬቱን ወደ 6000 ሄክታር ለማሳደግ ማቀዱ ተዘግቦ ነበር። ከዚህም ዉስጥ 75 በመቶዉ በገበሬዎች እንደሚለማም ተጠቅሷል። የሾንኮራ አገዳዉ ቆረጣ ሲደርስም አንድ ኩንታል በ50 ብር ለመቀበል እቅድ እንደነበረዉ ተዘግቧል።
መርጋ ዮናስ
ሂሩት መለሰ