1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሸንገን እጣ ፈንታ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 26 2008

በአውሮፓ የድንበር ቁጥጥርን ካስቀረው የሸንገን ስምምነት ፈራሚ አባል ሃገራት የተወሰኑት ፣የድንበር ቁጥጥር መጀመራቸው በሰፊው እያነጋገረ ነው ።አነዚህ ሃገራት ቁጥጥሩን ተግባራዊ ያደረጉት ያልተመዘገቡ ስደተኞችን ዝውውር ለመግታት መሆኑን አስታውቀዋል ።ይህ አሠራር ወዴት ያመራል ? የሸንገን ስምምነት እጣ ፈንታስ ምን ይሆናል?

https://p.dw.com/p/1HYTP
Dänisch-Schwedischer Grenzübergang Kontrolle in Lernacken
ምስል picture-alliance/dpa/N. Meilvang

የሸንገን እጣ ፈንታ

ፈረንሳይ ፣ምዕራብ ጀርመን፣ ቤልጂግ ኔዘርላንድስ እና ሉክሰምቡርግ ፣ደቡብ ምሥራቅ ሉክስምቡርግ ውስጥ በምትገኘው በሸንገን ከተማ በጎርጎሮሳዊው 1985 ነበር የድንበር ቁጥጥርን የሚያስቀረውን የሸንገን ስምምነት የተፈራረሙት። የ5 ቱ መንግሥታት የያኔው ራዕይ ሰዎችና እቃ ያለ አንዳች መሰናክል ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው እንዲዘዋወሩ ማብቃት ነበር ። ስምምነቱ በተግባር ከተተረጎመበት ከ1995 ጀምሮ ያ ራዕያቸው በአመዛኙ ገቢራዊ ሆኗል ። ይሁንና የዛሬ 7 ዓመት ግድም አውሮፓን በመታው የኤኮኖሚ ቀውስ ሰበብ በክፍለ ዓለሙ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ማንሰራራታቸውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አውሮፓ የሚገባው ተገን ጠያቂ ቁጥር መጨመር በሸንገን ስምምነት ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ ነው ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስምምነቱ እንዲሻሻል የሚጠይቁ በአንዳንድ ሁኔታዎችም እንዲቀየር የሚወተውቱ መንግሥታትና የፖለቲካ ቡድኖች ተነስተዋል ። በተለይ ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2015 ስምምነቱ በሚፈቅደው ነፃ ዝውውር ፣ ያልተመዘገቡ ስደተኞች የሜዲቴራንያንን ባህር በሚዋሰኑ ሃገራት በኩል ወደ ሰሜን አውሮፓ መጉረፋቸው ሲያወዛግብ ነው የከረመው ።የሰሜን አውሮፓ ሃገራት በስተደቡብ የህብረቱ ድንበር የሆኑትን ሃገራት ተገን ጠያቂዎችን ሳይመዘግቡ በመልቀቅ ሲወቅሱ ፣ስደተኞች በብዛት የሚገቡባቸው ኢጣልያና ግሪክን የመሰሳሉ የደቡባዊ አውሮፓ ሃገራት ደግሞ ከአቅማቸውበላይ የሆነውን ስደተኛ የመቆጣጠርም ሆነ የማስተናገድ አቅም የለንም ሲሉ ይከራከራሉ ። ሃንጋሪን የመሳሰሉት ሃገራት ድንበራቸውን አጥረዋል ። ስደተኞች በብዛት ከሚገቡባቸው ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ስዊድን ቀደም ሲል ባስጠነቀቀችው መሠረት የሸንገን ስምምነት ያስቀረውን የድንበር ቁጥጥር ትናንት ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች ።ዴንማርክም ከሰዓታት በኋላ በደቡባዊ ድንበሯ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች ። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ የሸንገን ስምምነት ፈራሚ የሆኑት እነዚህ ሃገራት የድንበር ቁጥጥር ማድረግ የጀመሩበት ምክንያት ግልፅና የሚጠበቅም ነበር ይላል ።
የስደተኞችን ዝውውር ለመግታት ታስቦ የተጀመረው ይህ አሠራር የሸንገን ስምምነት ባስተሳሰራቸው ሃገራት ውስጥ አሉታዊ ተጽእኖ ማስከተሉ እንደማይቀር ከወዲሁ አስግቷል ። ለምሳሌ ከዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፕንሃገን ወደ ደቡባዊቷ የስዊድን ሦስተኛ ትልቅ ከተማ ማልሞ ሁለቱን ሃገራት በሚያገናኘው በኦርዙንድ ድልድይ በኩል በየቀኑ 15 ሺህ ሰዎች እየተመላለሱ ይሠራሉ ።ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው አሠራር ከዴንማርክ ወደ ስዊድን የሚሄድ ባቡር ተሳፋሪዎች በሙሉ ኮፕንሃገን አየር ማረፊያ እንዲወርዱ ተደርጎ ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች የጉዞ ሰነዶቻቸው በድንበር ጠባቂዎች ይመረመራሉ ። 30 ደቂቃ ለሚወስደው ለዚህ ጉዞ እስከ 45 ደቂቃ የሚፈጅ የድንበር ቁጥጥር ይካሄዳል ። ጊዜ ገንዘብ በሆነበት በአውሮፓ ቁጥጥሩ በተሳፋሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ሳይሆን በባቡር ኩባንያዎች ገቢ ላይም ተፅእኖ አሳድሯል ። ለቁጥጥሩ የሚወጣው ገንዘብም ቀላል የሚባል አይደለም ።የዴንማርክ ባቡሮች ህጋዊ ያልሆኑ መንገደኞችን ይዘው ድንበር ቢሻገሩ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ስዊድን አስጠንቅቃለች ።በገበያው አስተያየት የድንበር ቁጥጥሩ ከዚህም በላይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ተፅእኖዎችም አሉት ።
ስዊድንና ዴንማርክ እንዲሁም ኖርዌይን የመሳሰሉት ሃገራት በአውሮፓ የተጠቀሱትን ተፅእኖዎች ሊያሳድር ይችላል የተባለውን የድንበር ቁጥጥር ተግባራዊ ማድረጋቸው ህጋዊ ነው።በሸንገን ደንብ መሠረት ለፀጥታ ጥበቃ ሲባል ያልተጠበቀና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስደተኞች እንቅስቃሴን ለመገደብ ሃገራት ሁኔታውን ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አሳውቀው ቁጥጥሩን ለ30 ቀናት ተግባራዊ ሊያደርጉ ይችላሉ ። አሠራሩ እንደ ሁኔታው እስከ 6 ወራት ሊቀጥልም ይችላል ። በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ውሳኔ ላይ የሚደርሱት ሃገራት ደግሞ ዴንማርክ ትናንት እንዳደረገችው ለመጀመሪያ ጊዜ ለ10 ቀናት ሥራ ላይ እንዲውል አድርገው ከዚያ በኋላም በየ20 ቀኑ ለሁለት ወራት ሊያራዝሙት ይችላሉ ። በገበያው አስተያየት ስዊድንና ዴንማርክ የድንበር ቁጥጥር እንዲጀምሩ ያስገደዳቸው የጋራ ችግር እስካልተወገደ ድረስ ችግሩ የሚያሰጋቸው ሌሎች የሸንገን ስምምነት ፈራሚዎችም የነርሱን ፈለግ መከተላቸው አይቀርም ። ቁጥጥሩም በጊዜያዊነት ብቻ ላይገደብም ይችላል ።
የሸንገን ስምምነት ይህን መሰል ፈተና ውስጥ ቢገኝም ፣ የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት ግን የስምምነቱ ደንቦች ተግባራዊ እየሆኑ መሆኑን ነው የሚናገሩት ። ተችዎች እንደሚሉት ግን የሸንገን ስርዓት ችግር ውስጥ ወድቋል ። ስምምነቱን ለመታደግ ትክክለኛው መፍትሄ በአውሮፓ ድንበሮች ተገቢውን የፀጥታ ጥበቃ ማካሄድ ነው እንደ አስተያየት ሰጭዎች። ገበያውም በዚህ ሃሳብ ይስማማል።ይህ ካልሆነ ግን ሁሉም የአውሮፓ ሃገራት ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም። ድንበር ቁጥጥሩ በአጠቃላዩ የአውሮፓ ኤኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ ሳይታለም የተፈታ ነው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሸንገን ደንቦች ላይ ይደረጋሉ የተባሉ ማሻሻያዎችን በመጋቢት ወር ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ማሻሻያዎቹ የአውሮፓ የውጭ ድንበሮች ላይጥብቅ ቁጥጥር ማድረግንና የአውሮፓ የተገን አሰጣጥ ሕግን ማሻሻልን ይጨምራሉ።

Metallgatter mit Schild Schengen
ምስል picture alliance/Romain Fellens
Grenzkontrollen in Dänemark
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ