1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መክረዋል።

ሰኞ፣ ጥቅምት 13 2010

በአል-ሸባብ ላይ "ብሔራዊ ጦርነት" ያወጁት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በአፍሪቃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር ወታደሮቻቸውን ያሰማሩ አገሮችን እየጎበኙ ነው።"ከኢትዮጵያ ድጋፍ እና ወንድማማችነት ፍለጋ" ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በአል-ሸባብ ላይ ለከፈቱት ዘመቻ ተመሳሳይ ጥምረት ለመፍጠር ወደ ጅቡቲ እንደሚጓዙም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2mMcI
Äthiopien Mohamed Abdullahi Mohamed, Präsident Somalia
ምስል DW/Y. G/Egziabhare

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ጉብኝት

"አል-ሸባብ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ተጨባጭ ሥጋት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድ "ስንተባበር በፍጥነት ድል ልንነሳው እንችላለን። አለበለዚያ እንዲህ አይነት አስከፊ ጥቃት መድረሱ ይቀጥላል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል። 

ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድ ዛሬ ኢትዮጵያ ደርሰው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር መክረዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ አለም በአሸባብ ላይ አዲስ ዘመቻ የከፈተው የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን ድጋፍ በመፈለጉ ፕሬዚደንቱ ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውንም ገልጠዋል።  

በሞቅዲሹ ባለፈው ሳምንት በደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 358 ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም የሶማሊያ የጸጥታ መሥሪያ ቤቶች በተሽከርካሪው ላይ  ከ600-800 ኪ.ግ. የሚመዝን ተቀጣጣይ ቁስ ተጭኖ ነበር ብለዋል። ከጥቃቱ በኋላ መድሐኒት እና የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ሞቅዲሹ ከላኩ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ