1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደት ጉዞ ወደ አዉሮጳ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 28 2007

ወደአዉሮጳ በሕገወጥ መንገድ ለመጓዝ የሚነሱ አፍሪቃዉያን በመንገድ ምን እንደሚጠብቃቸዉ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። እጅግ ዉድ በሆነ ክፍያ ሕይወትን ለአደጋ ባጋለጠ መልኩ በግልጥ የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ በረሃዉን ማቋረጥ ግድ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GQgs
Migranten in Agadez
ምስል DW/K. Gänsler

[No title]

ሊቢያ ዉስጥ መሰቃየት እና መዋረድ፤ ከዚያም ጣሊያን ለመግባት የሚደረገዉ አደገኛ የጀልባ ጉዞ። እንዲህም ሆኖ ግን በየዓመቱ በአስር ሺህ የሚገመቱ የምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃ አካባቢ ወጣቶች በዚሁ መንገድ ይሰደዳሉ። አጋድዝ በተባለችዉ የኒዠር ግዛትም ሁሉም ማለት ይቻላል ማረፍ ግድ ነዉ።

ማማን ካንታ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ይኖርበታል። በአካባቢዉ የሚያሰራጨዉ የ ኦልተርኔቲቭ FM ራዲዮ ዳይሬክተር ቀጣዩን እንደወትሮዉ ሁሉ ዛሬም የስደተኞች ጉዳይ ዋና ርዕሡ ነዉ። የማያቋርጠዉ የስደተኞች ጎርፍ በሰሜን አፍሪቃ አድርጎ ወደአዉሮጳ ለመሻገር የሰሃራ በረሃን ሲሻገር ይህችን ከተማ መርገጡ የማይቀር ነዉ። ጋዜጠኛ ካንታ በረኃዉን በማቋረጥ ሂደት ስላለዉ አደገኛና አስቸጋሪ ጉዞ ያስጠነቅቃል። ይህን አልፈዉ ለሚሄዱትም የሜዲትራኒያንን ባህር በአደገኛ ጀልባዎች ተሻግረዉ አዉሮጳ ቢገባም አስቸጋሪ ስለሆነዉ የመኖሪያ ፈቃድ ጉዳይም ያስረዳል። ይህም ሁሉ ሆኖ በየሳምንቱ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች የየእድላቸዉን ለመሞከር ጉዞዉን ቀጥለዋል ይላል ካንታ።

Niger Agadez Sahara Flüchtlinge Wasser
ምስል Reuters/Akintunde Akinleye

«በመሠረቱ ለእነሱ ሁኔታዉ በጣም መጥፎ ነዉ። ሥራ ቢኖራቸዉ እንኳ ክፍያቸዉ ጥሩ አይደለም፤ በዚያም ህይወታቸዉን መምራት አይችሉም። ለምሳሌ ለልጆች የትምህርት ቤት መክፈል አይችሉም። ወይም ራሳቸዉም ቢሆኑ መማር እየፈለጉ ወይም አትሌት የመሆን ሕልም እንኳ ቢኖራቸዉ ማሳካት አይችሉም።»

ለብዙዎች አጋድዝ ላይ የሚደረገዉ እረፍት የግዳጅ ያህል ነዉ። ከስንት አንድ ነዉ የጀመረዉን ጉዞ ሳያርፍ የሚጨርሰዉ። በዚህ ስፍራ ስደተኞቹ የሚቆዩት አንድም ከቤተሰብ ለመማከር አንዳንዴም ለጉዟቸዉ የሚያስፈልጋን ገንዘብ ለማግኘት ነዉ። አንዳንዶች እንደዉም በቀን ሠራተኝነት ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ ለማግኘት ይሠራሉ። የ23 ዓመቷ ቪክቶሪያ የደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ ተወላጅ ነች። አጋዱዝ ከተማ ከአንድ ዓመት በላይ ቆይታለች። ሀገሯ ዉስጥ የምታዉቀዉ አንድ ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪ ነበር ያመጣት። ትምህርትና የተሻለ ዕድል ጣሊያን ዉስጥ እንደምታገኝ ነበር ቃል የገባላት። ያ ሕልሟ አሁን ቅዠት ሆኗል።

«አንድ ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪ ነዉ እዚህ ያመጣኝ። ከዚያም እዚህ ተሸጥኩ ማለት ነዉ። ነፃነቴን መልሼ ለመግዛት እንድችል ገንዘብ ማግኘት ይኖርብኛል። እዚህ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ነዉ፤ በተለይ ደግሞ ለዉጭ ዜጋ። እዚህ ምንም ዓይነት ነፃነት የለንም።»

Niger Agadez Afrika
ምስል Getty Images/Afp/Boureima Hama

ይህም ማለት ወጣቷ ለአንድ ዓመት ያህል በሴተኛ አዳሪነት ሠርታለች፤ አዉሮጳም ብትሻገር የሚጠብቃት ያዉ ሊሆን ይችላል። በዚህ አንድ ዓመት ዉስጥ ምን እንደተፈጠረ ግን መናገር አትፈልግም። አሁን እንደሚስቱ ከሚያስተዋዉቃት አንድ ወንድ ጋር አጋዳዝ ትኖራለች። አንድ ክፍል ተጋርተዉ ነዉ የሚኖሩት። ከአዉሮጳ ባረፈባት ጫና ምክንያት ባለፈዉ ግንቦት ወር ኒዠር ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ላይ ጠንከር ያለ ሕግ ካጸደቀች ወዲህም ስደተደኞች የማንንም ትኩረት እንዳይስቡ በመጠንቀቅ ሁኔታዎች እስኪመቻቹላቸዉ ተደብቀዋል። ቪክቶሪያ አሁን ጊዜዋን በወየበዉ ፍራሽ ላይ ቁጭ ብላ ናይጀሪያ ዉስጥ የምትወዳቸዉን መንፈሳዊ ትምህርቶች በዲቪዲ ትከታተላለች። በዚህ ሁኔታ እዚያ መቀመጡን ግን በፍፁም አትፈልገዉም።

ኻሊድ ደግሞ ሴኔጋላዊ ወጣት ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ወደጣሊያን ለመሄድ ሞክሮ ነበር። ሊቢያ ድረስ ላለዉ ጉዞ ብቻም 1,200 ዩሮ ገደማ ከፍሏል። እጅግ ምህረት የለሽ ከሆኑ ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች እጅ ካመለጠ ወዲህ ወደአዉሮጳ የመጓዝ እቅዱን ሰርዟል። ዛሬ ካሊድ ከአጋዳዝ ወጣ ብሎ በሚገኘዉ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ዉስጥ ይገኛል።

«ሊቢያ ዉስጥ ለአራት ወራት ተኩል ነበርኩ። ወደጣሊያን ለማደርገዉ ለመጨረሻዉ ጉዞዬ የሚበቃኝ ያህል ገንዘብ ስላልነበረኝ መሥራት ፈለኩ። ሆኖም ግን እቅዴ አልሠራም። ይዘዉ አሠሩኝ። አሁን ደክሞኛል ወደሀገሬ መመለስ እፈልጋለሁ።»

Niger Agadez Afrika
ምስል Imago/alimdi

እንግዲህ ወጣቶቹ በየሀገራቸዉ እንዲቀሩ ይህን መሰሉን አስቸጋሪ አካሄድ ራሳቸዉ መሞከር ይኖርባቸዋል ይላል ጋዜጠኛ ማማኔ ካናታ። እንደሱ ሃሳብ ከሆነም በተለይ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ምርጫ የሚያካሂዱ አምስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት ዋና ተግባራቸዉ ሊያደርጉት የሚገባ ጉዳይ አለ። ይህም ሥራ ላጣዉ ወጣት ዕድሎችን ለመክፈት ጠንክሮ መሥራት።

«ፕሬዝደንቶቹ ይህን ከማድረግ ይልቅ በምርጫ ቅስቀሳቸዉ ዝም ብለዉ ወሬ ካበዙ የሚያመጡት ለዉጥ አይኖርም። ይህን ችግር በግሌ የዛሬ አስር እና ሃያ ዓመታት አይቸዋለሁ። የመንግሥታቸዉን ቅርፅ መቀየር አለባቸዉ።»

ይህ ካልሆነም የስደተኞዉን ጎርፍ ማስቆም በምንም መንገድ አይቻልም ባይ ነዉ።

ካትሪን ጋንዝለር /ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ