1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስዊትዘርላንዱ ግዙፍ የግንባታ ሥራ እንዴትነት?

ሐሙስ፣ ሰኔ 9 2008

ስዊትዘርላንድ «ጎትሃርድ ባሲስቱኔል» በመባል የሚታወቀዉና ከዓለም በርዝመቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የዋሻ ውስጥ የባቡር መንገድ ዝርጋታን አጠናቃ አስመርቃለች። ስዊትዘርላንድ እጅግ ግዙፍ የሆነ የመሠረተ ግንባታን ለመሥራት ስታቅድ ግንባታዉ ይጠናቀቃል ብላ ባስቀመጠችበት ቀነ ገድብ ነዉ ያጠናቀቀችዉ።

https://p.dw.com/p/1J7H9
Schweiz Gotthard Basistunnel
ምስል picture alliance/KEYSTONE

እንዲሁም ያስወጣል የተባለዉ የገንዘብ ወጭም ከታቀደዉ እንደማይዘል የዘርፉ ባለሞያዎች ይመሰክራሉ። ስዊትዘርላንዶች ፤ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታን ባሉት ጊዜና ወጭ እንዴት ነዉ የሚያጠናቅቁት?

ባለፈዉ ሰሞን የተመረቀዉና ከዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የዋሻ ዉስጥ የባቡር ሃዲድ ርዝመት 57 ኬሎ ሜትር ሲሆን፤ በዚሁ የባቡር ሃዲድ መገናኛ የሆኑ መንገዶችን ጨምሮ በዋሻ ዉስጥ በአጠቃላይ 151 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ላይ ግንባታዉ መጠናቀቁ ነዉ የተመለከተዉ። የግንባታ ሥራዉም 17 ዓመታትን ፈጅቶአል። ይህ በጥልቀቱም ሆነ በርዝመቱ በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የዋሻ ዉስጥ የባቡር መስመር ዝርጋታ ግንባታዉ በተባለበት ጊዜ መጠናቀቁና ወጭዉም እንደቃቀደዉ ተመጣጣኝ በመሆኑ የብዙዎችን የግዙፍ ግንባታ ሥራ እቅድ ባለሞያዎችን ቀልብ ስቦአል። በኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ «ሰይድ የንግድ ትምህርት ቤት» የግዙፍ ግንባታ ሥራ እቅድ አስተዳደር መምህር ቤንት ፍላይቤርግ፤ የስዊትዘርላንዱን የዋሻ ዉስጥ የባቡር ሃዲድ መስመር ሥራ ግንባታን በጣም አስደናቂ ሲሉ ነዉ የገለፁት። እንደ ቤንት ፍላይቤርግ ተመሳሳይ አይነት ግዙፍ የሃዲድ መስመር ዝርጋታ 23 % ከታሰበለት የመጠናቀቅያ ጊዜ ዘግይቶ ነዉ የሚያበቃዉ። 57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለዉ የስዊትዘርላንዱ የዋሻ ዉስጥ የባቡር ሃዲድ መስመር ዝርጋታ ግን ይጠናቀቃል ከተባለለት ጊዜ ቀደም ብሎ ነዉ የተጠናቀቀዉ። እንደ እቅዱ ከሆነ ግንባታዉ ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበዉ በመጭዉ የጎርጎረሳዉያን 2017 ዓ,ም መጀመርያ ላይ ነበር። ወጭዉም ቢሆን ያን ያህል ከፍተኛ የሚባል እንዳልሆነ ተመልክቶአል። ቤንት ፍላይቤርግ እንደሚሉት የግንባታዉ ሥራ ከተመደበለት ወጭ ተጨማሪ 20 % ይጨምራል ተብሎ ነበር። ግንባታዉ ግን 12 ቢሊዮን የስዊትዘርላንድ ፍራንክ ወይም ወደ 10 ቢሊዮን ይሮ ወጭን ብቻ ነዉ የጠየቀዉ።
« 23 % ጭማሪን ይጠይቃል ተብሎ ነበር የታሰበዉ፤ የጠየቀዉ ግን ጭማሪ ይህ ነዉ የሚባል አይደለም። በዚህም አስደናቂ ስኬታማ ሥራ ነዉ»
የግዙፍ ግንባታ እቅድ መምህሩ ቤንት ፍላይቤርግ እና ባልደረባቸዉ በስድስቱም የዓለም አህጉራት በቢሊዮን የሚቆጠር ወጭንና ረጅም የግንባታ ጊዜን የጠየቁ ከ 6000 የሚበልጡ የግዙፍ ግንባታ እቅዶችን ሰብስበዉ እንደተመለከቱት፤ የተሰሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች 90 % ዉ ከታቀደላቸዉ ጊዜ እጅግ ዘግይተዉ ነዉ የተጠናቀቁት። ወጭያቸዉም ቢሆን ከታሰበለት በላይ ነዉ የጠየቀዉ። ጥሩ መረሃ-ግብርና እቅድ የወጣለት ግዙፍ የግንባታ እቅድ ከፍተኛ ዋጋን ሊጠይቅ ይችላል። ለዚህ የስዊትዘርላንዱ የዋሻ ዉስጥ የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ ነዉ። ስዊትዘርላንዳዉያኑ በጎርጎረሳዉያኑ 2007 ዓ,ም በግንባታዉ ሥራ በተለይ የቴክኒክ ነክ ጉዳዮች ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ከተገነዘቡ በኋላ፤ በርጋታ እንዳሰቡበት የተናገሩት በበርሊን «Hertie School of Governance» የግል ኮሌጅ ባልደረባ ጆብስት ፊድለር፤ ችግሩ ከገባቸዉ በኋላ ባለዉ እቅድ ላይ የጠቅላላ ወጭዉንም ከፍ አድርገዋል። ከዝያ በኋላ ግን በአቀዱት ፀንተዉ ለ 9 ዓመታት ሥራቸዉን ቀጥለዋል። የስዊትዘርላንዱ ግዙፍ የዋሻ ዉስጥ የባቡር መስመር «ጎትሃርድ ባሲስቱኔል» የግዙፉ ግንባታ እቅድ ዉጤት ሲሆን፤ የእቅዱ ሙሉ ወጭ ወደ 24 ሚሊዮን የስዊዘርላንድ ፍራንክ ይገመታል። በአልፐስ ተራራ ለታጠረችዉ ሃገር ለስዊትዘርላንድ ደግሞ ትልቅ የኤኮኖሚ አዉታርም ነዉ። «በበርሊን የጀመረዉ የአዉሮፕላን ግንባታ ሥራ መጓተት ጉዳይ በዓለም ታዉቆ መሳቅያ እስከመሆን ደርሶአል። እንዲህ አይነት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ማየትን ማንም አይፈልግም ምክንያቱም ስምን የሚያጎድፍ በመሆኑ ነዉ። የጀርመን ኩሩ የሆነ የምህንድስና የግንባታ ሥራንም የሚረብሽና የሚያጎድፍ ነዉ። ድንገት ይህ ሁሉ ፕሮጂ ባልታሰበ አቅጣጫ ሲያመራ ፤ ለስም ጥሩ አይደለም ። ይህ ደግሞ ለበርሊን ብቻ ሳይሆን ለመላ ጀርመንም ጭምር ነዉ ፤ ሲሉ ቤንት ፍላይቤርግ፤ በሃንቡርግ የፊላርሞኒ አዳራሽ፤ የሽቱትጋርቱ የባቡር ጣብያ ግንባታ፤ በጀርመን ከፍተኛ ወጭና የግንባታ ጊዜን የጠየቁ ግዙፍ የግንባታ እቅዶች መሆናቸዉን በምሳሌ ጠቅሰዋል።

Schweiz Gotthard-Basistunnel
ምስል picture-alliance/Keystone/C. Beutler


በበርሊን የሚገኘዉ የግል ኮሌጅና የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት «OECD» በ36 ሃገራት የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግዙፍ እቅዶችን ምን ያህል ጥሩነታቸዉን በጋራ ፈትሸዋል። በጥናቱ መሠረት ስዊትዘርላንድ በሁሉም መስፈርቶች ቀዳሚዉን ቦታ ይዛ ትገኛለች። ቤንት ፍላይቤርግ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ስዊዘርላንድ ከጀርመን ቀድማ 11 ኛ አልያም 15ኛ ቦታ ላይ ትገኛለች።
በጀርመን የሚገኙ ምሁራን በሃገሪቱ የሚታየዉ ቢክሮክራሲን ጨምሮ የግዙፍ ግንባታ ሥራ እቅዶች ሂደት ላይ ትልቅ ጉድለት ይታያል ሲሉ ትችት ያቀርባሉ። እንደ ምሁራኑ ነፃ የሆነ የቁጥጥር ክፍል የለም፤ በማዕከላዊና ክልላዊ የግዙፍ እቅድ ግንባታ ተሳታፊዎች ላይ የቅንጅት ጉድለት አለ። ለዚህ በምሳሌነት ተጠቃሹ በበርሊን የተጀመረዉ ግዙፉ የአዉሮፕላን ማረፍያ ግንባታ ሥራ ነዉ። የግንባታዉ ሥራ ወጭ በእጥፍ ጨምሮአል፤ የግንባታ ጊዜም በሦስት እጥፍ ጨምሮአል፤ እንድያም ሆኖ ይህ ግዙፉ የግንባታ ሥራ እቅድ አሁንም አልተጠናቀቀም። ምናልባትም ይህ ጉዳይ ስዊትዘርላንድ ቢሆን ባልተከሰተ ነበር፤ሲሉ ፊድለር ይገልጻሉ።
« በበርሊን የተጀመረዉ የአዉሮፕላን ግንባታ ሥራ መጓተት ጉዳይ በዓለም ታዉቆ መሳቅያ እስከመሆን ደርሶአል። እንዲህ አይነት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ማየትን ማንም አይፈልግም ምክንያቱም ስምን የሚያጎድፍ በመሆኑ ነዉ። የጀርመን ኩሩ የሆነ የምህንድስና የግንባታ ሥራንም የሚረብሽና የሚያጎድፍ ነዉ። ድንገት ይህ ሁሉ ፕሮጂ ባልታሰበ አቅጣጫ ሲያመራ ፤ ለስም ጥሩ አይደለም ። ይህ ደግሞ ለበርሊን ብቻ ሳይሆን ለመላ ጀርመንም ጭምር ነዉ»
በዚህም ምክንያት ብቻ በዉጭ ሃገራት ግዙፍ ሥራን ለመስራት የሚፈልጉ የጀርመን ኩባንያዎች ለዉድድር ሲቀርቡ ችግር ገጥሞአቸዋል። በሌላ በኩል የስዊትዘርላንዱ የዋሻዉስጥ የባቡር መስመር ዝርጋት « ጎት ሃርድ ባሲስቱኔል» ጊዜዉን ጠብቆ በመጠናቀቁ ጥሩ ሁኔታን እይታንና ግምትን አስገኝቶአል። እንዲህ አይነቱን ግዙፍ ፕሮዤ ይላሉ በኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ «በሰይድ የንግድ ትምህርት ቤት» የግዙፍ ፕሮዤ አስተዳደር ሥራ መምህር ቤንት ፍላይቤርግ ዓለም ሁሉ የሚያተኩርበት የሚያዉ የዓለም በረከት ነዉ።

Schweiz Gotthard Basistunnel
ምስል picture alliance/KEYSTONE


አንድርያስ ቤከር / አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ