1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስምንቱ ኢትዮጵያውያን የስእል አውደ ርእይ በቶሮንቶ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 2009

በካናዳ በስደት የሚኖሩ ሰዓሊያን በቅርቡ በቶሮንቶ ከተማ ‹‹ኅብረ ቀለማት›› በሚል ርእስ የስእል ኢግዚቢሽን አቅርበው ነበር፡፡ ሰዓሊያኑ በቁጥር ስምንት ሲሆኑ በካናዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥምርት ያዘጋጁት ነው አውደ ርእዩ፡፡ በዚህ የስእል አውደ ርእ ትኩረት ስብው ከነበሩት ስእሎች መካከል ‹‹ጥበቃ›› ትኩረትን ስቦ ነበር።

https://p.dw.com/p/2bG0N
Kanada | Erste äthiopische Kunstausstellung in Toronto
ምስል A. Negash

የስምንት ኢትዮጵያውያን የስእል አውደ ርእይ በቶሮንቶ

አቶ ጌታቸው ፋንቱ ኢትዮጵያ ለቅቆ ካናዳ ከከተመ ከ30 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የስነ ጥበብ ፍቅር ነበረው፡፡ ወደ ካናዳ ከመምጣቱ በፊት ጥቂት በቆየባት ጣሊያን የስእል ትምህርትን ተምሮ ተመርቋል፡፡ የግል ሞያና ክህሎትን ጠብቆ መኖር አስቸጋሪ በሆነበት ሰሜን አሜሪካ የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ነው፡፡ ጌታቸው በራሱ የስእል ማሳያ ስቱዲዮ ውስጥ ያዘጋጃቸውን ስእሎት ሲያቀርብ ነበር ለዛሬው ‹‹ኅብረ ቀለም›› የስእል አውደ ርእይ መጸነስ ምክንያት የኾነው፡፡  

Kanada | Erste äthiopische Kunstausstellung in Toronto
ምስል A. Negash

ሌላኛው ሰዓሊ ደግሞ አዲስ አለም ኋ/ማርያም ይባላል፡፡ በአዲስ አበባ ስነ ጥበብ ትምህት ቤት ተማሪም አስተማሪም ነበር፡፡ ወደ ካናዳ ከመጣ አራት አመታት የተጠጉት ሲሆን ከዚህ ቀደም ስእሎቹን የማሳየት እድል ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በዚህኛው ኢግዚቢሽን መሳተፉ ግን የበለጠ አስደስቶታል፡፡

ለሶስት ሳምንታት በዘለቀውና በርካታ የቶሮንቶ ነዋሪዎች በጎበኙት በዚህ የስእል አውደ ርእ ትኩረት ስብው ከነበሩት ስእሎች መካከል የተስፋዬ እርገጤ ‹‹ጥበቃ›› የሚል ርእስ የተሰጠው ስእል ይገኝታል፡፡ ስእሉ ያለችው ብቸኛ ሱሪው የተቀደደበት ወጣት ሱሪው እንዲጣፍለት ለልብስ ሰፊ አውልቆ ሰጥቶ ግማሽ አካሉን እርቃኑን ሆኖ ልብሱ ተሰፍቶ እስኪያልቅ የሚያርደገውን ጥበቃ በቀለም ብሩሹ ያሳያበት ነው፡፡ በዚህ አግዚቢሽን ብቸኛ ሴት ሰዓሊ ሆና የተካፈለችው እንስት አሚራ አል አማሪ ትባላለች፡፡ አሚራም እንደ ጌታቸውና ፋንታሁን የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ናት፡፡ ኤግዚቢሽኑ የተካሄደበት ጋለሪ ባለቤት ስትሆን የስእል አውደ ርእዩ እውን እንዲሆን የእሷ አሪጅ ጋለሪ ትልቅ አስተዋጽኦ ድርጓል፡፡

Kanada | Erste äthiopische Kunstausstellung in Toronto
ምስል A. Negash

ካናዳ ከመጣ በኋላ የስእል ት/ቤት ገብቶ በመማር ራሱን የሙሉ ጊዜ ሰዓሊና የግራፊክስ ባለሞያ ያደረገው ፋንታሁን አባተ ከስምንቱ ሰዓሊያን አንዱ ሲሆን፤ ከእሱ በተጨማሪም ከአሜሪካ አትላንታ ዘይኑ ሙደሲር እንዲሁም አቶ በላይነህ ስዩምና በኋይሉ አጥናፉ ሌሎቹ የቶሮንቶ ነዋሪና የኢግዚብሽኑ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

በስእል አውደ ርእዩ የታዩት ስእሎች በብዛት የኢትዮጵያውያን ባህል፣ ሃይማኖት፣ አኗኗርና ትውፊትን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ሆኖም የሁሉም ሰዓሊያን የስእል አሳሳልና ቀለም አጣጣል ይትባህል ለየቅል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በሰእል አውደ ርእይ  ከታደሙት ኢትዮጵያውን የተደረገላቸውን የሞቀ አቀአቀባበል ተከትሎ ሰዐሊየኑ ሌሎች  መሰል ዝግጅቶትን የማዘጋጃትም እቅድ  አላቸው፤  በሌሎች ከተሞችም ተገኝተው  ዝግጅታቸውን ለማቅረብና ለታዳጊዎች የሰእል ጥበብ ትምህርትን በተቋም ደረጃ ለማስተማርም አቅደዋል፡፡

አክመል ነጋሽ

አርያም ተክሌ