1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶች መብት

ዓርብ፣ የካቲት 16 2010

ሴቶች ዛሬም በ21ኛውም ክፍለ ዘመን መብታቸውን ከወንዶች እኩል አይከበርም። እንብዛም በኃላፊነት ቦታ ላይ አይታዩም። ያሉት ደግሞ እኩልነታቸውን ለማስከበር ብዙ መታገል አለባቸው። በተለይ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ሴቶች አፍሪቃ ውስጥ በፖለቲካውም መድረክ ላይ እጅግ ስፍራ የላቸውም። አልፎ አልፎ ግን መድረኩን የሚደፍሩ አሉ።

https://p.dw.com/p/2t8ea
Frauenquote Symbolbild
ምስል imago/blickwinkel

የፆታን እኩልነት ከሚያስከብሩ የዓለማችን አምስት ቀደምት ሃገራት ተርታ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሩዋንዳ አንዷ ናት። እንደ Global Gender Gap የ 2016 ዓ ም መዘርዝር ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ከአይስላንድ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ እና ስዊዲን ቀጥላ በአምስተኛነት ደረጃ ትሰለፋለች። ከአፍሪቃም ለነጋዴ ሴቶች ምርጥ ከሚባሉ ቦታዎች አንዷ ናት። በመዲና ኪጋሊ ሴቶች 40 ከመቶውን የንግዱን ቦታ ተቆጣጥረው ይገኛሉ። ይህ ብቻ አይደለም። በሩዋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ሴቶች ከ 60 ከመቶው በላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ በፆታው እኩልነት መዘርዝር መሠረት 109ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች። በፖለቲካው ዓለም ደግሞ 23 ከመቶ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተሳትፎ እንዳላቸው መዘርዝሩ ይጠቁማል።

የ33 ዓመቷ ኬንያዊት ናሱላ ሌሱዳ የማህበረሰቧን ባህል እና ወግ ተጋፍጣ በኬንያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያዋ ሴት አባል ለመሆን በቅታለች። ሁሉም ነገር እንዴት እንደጀመረ ለዶይቸ ቬለ እንዲህ ስትል ነበር የገለፀችው « የፖለቲካ ሥራዬን የጀመርኩት የፕሬዲንት ኡሁሩ ኬንያታ የምረጡኝ ዘመቻ በሚካሄድበት ወቅት በ 2012 ዓም ነው። ለፓርቲው ካገለገልን በኋላ በተለይ የሴቶችን ፍላጎትን ለሴኔቱ እንዳቀርብ እጩ ሆኜ ተመረጥኩ። በዚህ አጋጣሚ ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት።»

USA - Women's March 2018 Washington DC
ምስል DW/R. Kalus

ፖለቲከኛ መሆን ናሱላ ሌሱዳ የምትመኘው ሥራ ነበር? ምክንያቱም ወደ ፖለቲካው ከመግባቷ በፊት ጋዜጠኛ ነበረች።« በፍፁም ማለቴ የጋዜጠኝነት ሙያዬን ማዳበር እፈልግ ነበር። እና ጋዜጠኛ ሆኜ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው የዜና ክፍል በምሠራበት ወቅት፤ የበለጠ የምረዳውን፣ መዘገብ ደስ እንደሚለኝ ይበልጥ አውቅ ጀመር። እና ብዙውን ግዜ ስለመጣሁበት የሳምቡሩ ማኅበረሰብ እንድዘግብ እታዘዝ ነበር። እና ሥራዬን በምሰራበት ወቅት በዚህ አካባቢ ብዙ ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን እታዘብ ነበር።  ልጆች ትምህርት ቤት አይሄዱም። ውኃ የለም። ረሃብ ፣ድርቅ የመሳሰሉትን። አዕምሮዬ ውስጥ የቀረው ግን በአካባቢው የነበረው ግጭት ነው። ሰዎች በዚህ አካባቢ የሚፈልጉትን ለማግኘት ይገዳደላሉ። መሣሪያ ስላለን ላሞቻችሁን መስረቅ እንችላለን በሚል አይነት። የዚህ ተጠቂዎች ደግሞ ሕፃናት፣ ሴቶች እና ወጣት ወንዶች ነበሩ። እና ከማኅብረሰቡ ጋር በነበረኝ ቅርበት ይህንን ነገር መቀየር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። እና በዚህ አጋጣሚ ነው የህዝብ ግንኙነት ሥራዬን ትቼ ከዚህ አካባቢ የሚመጡ ታሪኮችን መቀየር ከሚፈልጉት ጋር ለመቀላቀል የቻልኩት።»

 ለወንድም ይሁን ሴት ወደፖለቲካው ዓለም ለመግባት የራሱ የሆነ ሂደት አለው። ወጣቷ ናሱላ በአብዛኛው ወንድ ከሚወስንበት ማኅበረሰብ ነው የመጣችው። ይህንን  ሁሉ እንቅፋት ለመሻገር ከባድ ነበር ትላለች። «ስላላገባሁ ልጃ ገረዷ ብለው ነበር የሚጠሩኝ። እኔ ግን ቢያንስ አንዲት እንኳን ተነስታ ፈተናውን የምትጋፈጥ ሴት መኖር አለባት ብዬ ወሰንኩ።»

በፖለቲካ አባልነት ቀርቶ ለሴቶች በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለመገኘት እንኳን ተስፋ አስቆራጭ ነው የምትለው ኢትዮጵያዊት የ 32 ዓመቷ ጠይባ ናት። እሷ እንደምትለው የሴቶች እኩልነት ከትዳር አጋራቸው ጋር ባለ ፉክክር ያበቃል። « በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳትፌ ነበር ነገር ግን ለምን አርፋችሁ እቤታችሁ አትቀመጡም። ከምን ከማይመጥናችሁ ጉዳይ መግባት እያሉ ክብር የሚነካ ነገር ነበር የሚነግሩን።» ጠይባ በነበራት ተሞክሮ የተነሳ ሀሳቧን በአደባባይ ከመግለፅ ተቆጥባለች። የ26 ዓመቷ ኢየሩሳሌም ተስፋው ደግሞ በ 97 ዓም የነበራት ተሞክሮዋ ነው ወደ ፖለቲካው ዓለም ያስገባት። « ምንም በማናውቀው ነገር ነው በ14 ዓመታችን ወታደሮች ከትምህርት ቤት እየገሩፉ የወሰዱን። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነው በዚህ መንግሥት ላይ ውስጤ ጥሩ ያልሆነ ነገር ቋጥሬ ወደዚህ የገባሁት።»

Symbolbild Frauenrechte Anne-Sophie Brändlin
ምስል DW

ኢየሩሳሌም እስከ 2007 ዓም ድረስም የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆና ቆይታለች። ከዛ በኋላ ግን እሷ እንደምትለው ከዛ በላይ የሰላማዊ ትግል ይቻላል ብላ ስላላመነች፤ መንግሥት የአሸባሪ ቡድን ብሎ የፈረጀውን የግንቦት ሰባት ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ስትጓዝ እሷ እና ጓደኞቿ ድንበር ላይ ተይዘው ለእስር ተዳርገዋል። አራት ዓመት ከአምስት ወር ተፈርዶባት በአመክሮ ከ 3 ዓመት እስራት በኋላ ቅርብ ጊዜ ነው ኢየሩሳሌም ከወህኒ የወጣችው። ኢየሩሳሌም ከፖለቲካዊ ተሳትፎዋ ባሻገርስ ሴቶች በዕለት ከዕለት ኑሯቸው ፣ በሥራው ዓለም ምን ያህል ተቀባይነት አላቸው ትላለች? « በበፊቱ የተሻለ ነገር አለ።» ትላለች። ጠይባም ብትሆን በማኅበራዊ ኑሮ በኩል በሴቶች መብት ላይ የተሻሻለ ነገር አለ ብላ ታምናለች። ይሁንና በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ሴቶች አሁንም ብዙ መታገል አለባቸው።

የመጀመሪያ ደረጃ መምህር ሆኖ ሰሜን ወሎ ውስጥ ያገለገለው አበበ በላይ የፆታ እኩልነት መከበር በገጠሩ አካባቢ ገና ብዙ እንደሚቀረው ነው የታዘበው። «ምክንያቱም ራሳቸው ሴቶች የፆታ እኩልነትን አምነው አልተቀበሉትም። ሴት ልጅ በትዳር ትቆያለች ስትፋታ አንዲት ላም ከነበረቻት ያቺን ላም ነው ይዛ የምትሄደው»  አበበ የፆታ እኩልነት ልዩነቱን የታዘበው የፍች መብትን በማስከበር ላይ ብቻ አልነበረም። « የቅጥር ማስታወቂያ ራሱ የሆነ ጫና አለው። ሴቶች ከወንዶች አያንሱም ከተባለ እኩል ተፈትነው እና ተወዳድረው መቀጠር ይኖርባቸዋል።» ይላል።  አበበ ሴቶች በአንድ በኩል እኩለነታቸውን በመጀመሪያ አምነው መቀበል አለባቸው ከዛ ባሻገር ደግሞ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ እንደተሰራው ሰፊ ሥራ መሰራት አለበት ሲልም ይመክራል።

ልደት አበበ