1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳዑዲ ምህረትና ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች፤

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2009

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የሰጠውን የምህረት ጊዜ ተጠቅመው ወደ ሀገር ለመግባት ባለፉት 10 ቀናት ከ 4 ሺህ በላይ ትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የመጓጓዣ ሰነድ መውሰዳቸውን ኤምባሲው አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/2b47F
Saudi Arabien Arbeiter kehren nach Äthiopien zurück
ምስል DW/S. Shiberu

Beri Riyadh (Saudi Amnesty -Ethiopian returnees) - MP3-Stereo

በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለ ሚካዔል የተመራ እና 10 አባላት ያሉት ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ቡድንም የመመለሱ ሂደት ያለበትን ደረጃ ለመቃኘት በሳዑዲ ዓረቢያ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ዘጠና ቀናት የተሰጠው የምህረት ጊዜ 14 ቀናት ተነስተውለታል፡፡ ጊዜው በራሱ ፍጥነት መሄዱን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ግን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚያስፈልጋቸውን የጉዞ ሰነድ ይኖራል ከሚባለው ብዛታቸው አንጻር የወሰዱት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የኤምባሲው ምንጮች እንደሚሉት በጂዳ አንድ ሺህ ያህል በሪያድ ደግሞ ሶስት ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከኤምባሲው የሚያስፈልጋቸውን ዋነኛ የጉዞ ሰነድ ወስደዋል፡፡ ጊዜው ገና ቢሆንም የመውጫ ሰነድ የመውሰዱ ፍጥነት የሚጠበቀውን ወይንም መሆን የነበረበትን ያህል ያለመሆኑን አብዛኞቹ ይስማማሉ፡፡

አብዱ ሳብር አህመድ ሳዑዲ ዓረቢያ አራት አመት ቆያቷል ህጋዊ ለተባለ የሳዑዲ የመኖሪያ ፍቃድ ለርሱ እና ለባለቤቱ 170 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ከፍሎ ነው የመጣው ፡፡ ሁለተኛው አመት ላይ የመኖሪያ ፍቃዱን ለማሳደስ ሲል የገዙት የመኖሪያ ፍቃድ ፎርጅድ መሆኑ ተነገራቸው ፡፡ ላለፉት ሁለት አመታትም ህገ ወጥ በሚለው መደብ ቆይቷል፡፡ 

ያም ሆኖ አብዱ ከነ ባለቤቱ ምህረት የተባለውን ጊዜ ተጠቅሞ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ቆርጧል፡፡  

ሀለፎም ተክላይ ደግሞ በባህር በህገወጥ መልኩ ወደ ሳዑዲ የገባ ነው፡፡ ዶሮዎችን እየበለተ ለገበያ በሚያቀርብ አንድ ድርጅት ስራ ላይ እያለ የሚሰራበት ማሽን አውራ ጣቱ ሲቀር የግራ እጁን አራት ጣቶች ቆረጠበት፡፡ አሰሪዎቹም ካሳከሙት በኋላ ከሆስፒታል አውጥተው ጣሉት እንደማያውቁትም ካዱት ፡፡ የአካሉን ጉድለት ካሳ ቢጠይቅ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም ቢያስጠይቅ ላለፉት ሶስት አመታት ምንም አልሆነለትም፡፡ ለሀለፎም ታዲያ ጎዶሎ አካል ይዞ ሀገር መግባት የሸክሞች ሁሉ ሸክም ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ የኢትዮጵ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ እና የዳያስፖራ ሚኒስትር ዴኤታ በሆኑት ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካዔል የተመራ እና አስር አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን የተመላሾችን ጉዳይ እንዲያጤን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ልኳል፡፡ የልዑካን ቡድኑ መሪ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ኃይለሚካዔል ትላንት ምሽት ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው በፊት ለዶቸ ቨሌ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት መንግስት የዛሬ አራት አመት ከነበረው ልምድ በመውሰድ ከወዲሁ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሳዑዲ ተመላሾችን ጉዳይ የሚከታተል ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴርም እንዲሁ ከሳዑዲ ከሚገኙ የሚስዮን ጽህፈት ቤት የስራ ሀላፊዎች የእለት ተዕለት ክትትል የሚያደርግ አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡

ዜጎች ከተመለሱ በኋላ ወደ መጡበት አካባቢ በሰላም እንዲደርሱ የማድረግ ሀላፊነት ለዚሁ ሀገር አቀፍ ግብረ ሀይል መሰጠቱን ሚንስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡

ከሳዑዲ አረቢያ በሀይል እንዲወጡ የተደረጉ ኢትዮጵያዊያን በርካቶች በዚያው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ዳግም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይገባሉ ፡፡ አንዳንዱቹማ ለበርካታ ጊዜያት መመላለሳቸው እንደ ዝና ይወራላቸዋል ፡፡ ይህ ሁኔታ ካልተለወጥ ከዚህ መመለሱ ብቻ ምን ፋይዳ አለው ከሀገር እየወጣ ያለው እዚያው የሚቀርበት መንገድ ካልተፈለገ የመመላለስ ቀለበቱን ማቆም ይቻላል ወይ ለሚንስትር ዴኤታው የቀረበ ጥቄ ነው፡፡

47 ሚሊዮን የሚጠጋ ለስራ የደረሱ ወጣቶች የያዘችው ኢትዮጵያ ልጆቿን በሀገራቸው የስራ እድል ፈጥራ ለማሰማራት ታላቅ ስራ ይጠብቃታል፡፡ ዶክተር አዲሱ እንደሚሉት የኢንዱስትሪ መንደር መስፋፋትን ጨምሮ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ትኩረት ወጣቱን ከህገወጥ ስደት ለመታደግ ነው፡፡

ስለሺ ሽብሩ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ