1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ በኢትዮጵያ

Merga Yonas Bulaሰኞ፣ ነሐሴ 16 2008

የመብት ተከራካሪው ድርጅት፣ «ሂዉማን ራይትስ ዋች» እንደሚለው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተካሄዱ ተቃዉሞዎች ከ500 በላይ የሰዉ ህይወት አልፎዋል። በሺዎቹ የሚቆጠሩም ታስረዋል።

https://p.dw.com/p/1Jn89
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

[No title]

ይህን ተቋም ጨምሮ ሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በአገሪቱ ይፈፀማል ያሉትን የመብት ጥሰትን ለማጣራትና ለመመርመር ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ እንደተከለከሉ ገልፀዉ ነበር። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮምሺን በቅርቡም በአገሪቱ የተከሰቱትን ተቃዉሞዎች ተከትሎ ተፈፀሙ የተባሉትን የግድያ እና እስራት ጉዳዮችን በገለልተኛ አካል ለመመርመር ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት መጀመሪያ ላይ ፍቃደኛ አለመሆኑን ቢገልፅም፣ ባለፈዉ ሳምንት ለኮሚሽኑ በላከዉ መልስ ራሱ ገለልተኛ ምርመራ እንደሚያሂህድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስለሰጠዉ ምላሽ የተባበሩት መንግስታት የመብት ከፍተኛ ኮምሺን ቃል አቀባይ ራቭና ሻምዳሳን ለዶይቼ ቬሌ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፣ «በእዉነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያና አማራ የተከሰተዉ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ ምርመራ አካሂዳለሁ ማለቱን እንቀበለዋለን። ነገር ግን የተከሰተዉን ግጭት ግምት ዉስጥ በማስገባት እኛ የራሳችን ገለልተኛ ምርመራ እንድናካሂድ፣ አሁንም ቢሆን እኛ ችግሮቹ ወደተፈጠሩባቸው ክልሎች መግባት እንድንችል መንግስትን እየጠየቅን ነው። የተባበሩት መንግስታትም አካባቢዉ ላይ በመድረስ ጉዳዩን እንዲመረምር የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ እንድያደርግልን እንጠብቃለን። እንደምታዉቀዉ ብዙ የተባበሩት መንግስታት ተቋም በአዲስ አበባ ይገኛል፣ ግን በችግሩ የተጎዱት የኦሮሚያና አማራ ክልሎች መድረስ አንችልም።»


የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን ገለልተኛ አካል አሰማርቶ ምርመራ እንደምያካሂድ ቢገልፅም፣ ካሁን በፊት በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ያካሄዳቸው ምርመራዎች መንግስት የሚፈልገዉን ብቻ እንጅ የተከሰተውን እውነታ አላመላከተም በሚል የሚወቅሱ አልጠፉም። ስለዚህ አሁን የሚያደርገው ምርመራ ምን ያህል ገለልተኛ ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ራቭኛ ሲመልሱ፣ «ይህ ምርመራ ምን ያህል ገለልተኛ ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ነው በእርግጥ ብዙ ሰዎችን ያስጨነቀዉ። ምክንያቱም ሁኔታዉ በአገሪቱ በጣም አከራካሪ ስለሆነና በተከሰተዉ እዉነታ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ስላሉ ነዉ። ሰዎች የሞቱትም ሆነ የቆሰሉት ቁጥር ብዛት ላይ አይስማሙም። በዚህ ሁኔታ ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ለማካሄድ፣ በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን፣ ተጎጅዎችንም ሆነ ምስክሮች እንድሁም የደህንነት ሃይሉን ለማነጋገር ከየትኛዉም የፖለቲካ ድርጅት ጋራ ቁርኝነት የለለዉ ቢሆን በጣም ይረዳል።»

Ravina Shamdasani
ምስል picture-alliance/Fatih Erel/Anadolu Agency


የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሺን ያቀረበውን ጥያቄ እስከመጨረሻ ካልተቀበለ ኮሚሽኑ ርምጃ ይወስድ እንደሆን ቃል አቀባይዋ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ «ለጊዜዉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ በመነጋገር ላይ እንገኛለን። መግባት እንዲፈቀድልን ግፊታችንን ቀጥለናል። እናም እንደሚፈቅዱልን ተስፋ እናደርጋለን፣ አሁን ያለንበት ደረጃ እዚህ ላይ ነዉ።»


ከኢትዮጵያ የመንግስት ኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ሚንስቴር በኩል ተጨማር ማብራርያ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም፣ በዚህ ወቅት የተቀናበረ መረጃ ስለሌላቸዉ ለጥያቄያችን መልስ ሊሰጡን እንዳልቻሉ ገልጸውልናል። አንዳንድ የፌስቡክ ተከታዮቻችን ምርመራው በኢትዮጵያ መንግስት ነው መካሄድ ያለበት ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ «የኢትዮጵያ መንግሥት አጣራለሁ ማለቱ ማን የገደለውን ነው የሚያጣራው፣ ወይም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዱን እንዳይሠማ፣ ለጋሽ ሀገራትም ፊታቸውን እንዳያዞሩና ስልጣኑን እንዳያጣ የተቀየሠ ሴራ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

መርጋ ዮናስ

አረያም ተክሌ