1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወዲፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚና

ረቡዕ፣ መጋቢት 19 2010

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት ለማስቆም ከአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሳሰቡ። በኢህአዴግ አዲስ ሊቀመንበርነት የተሾሙት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶክተር  አብይ አህመድ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ቀዳሚ ተግባራቸው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/2v9W4
Amnesty international Logo
ምስል picture-alliance/dpa/S.Kahnert

የወደፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚና በሰብዓዊ ድርጅቶች እይታ

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ኢህአዴግ ለሳምንታት ካካሄደው ስብሰባ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሊቀመንበር መመረጡ በኢትዮጵያ ለውጦችን የማየት ተስፋ የሚሰጥ እርምጃ ብለውታል። ድርጅቶቹ ተስፋው ተስፋ ሆኖ እንዳይቀር ግን  አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የበኩላቸውን ድርሻ  እንዲወጡ አሳስበዋል። በሀገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ሊወሰዱ ይገባል ያሏቸውን ማሻሻያዎችም ዘርዝረዋል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ እንዳሉት ድርጅታቸው የወደፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ ይሰጣሉ ብሎ ይጠብቃል።  

«የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተና የሆነ ኃይል በሚወጡበት ጊዜም የፀጥታ ኃይሎች ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ኃይል በመጠቀም የመግደል ማቁሰል እና የመደብደብ ጥሰቶች ፈጽመው ያውቃሉ። ሰዎች ሲታሰሩም የማሰቃየት እርምጃ ኢሰብዓዊ ከሆነ አያያዝ ጋር በማቀናጀት እንደዚሁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ታይተዋል። በሰፊው በአገሪቱ በሙሉ ። ይሄ እንዳይደገም ማድረግ መቻል አለባቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የህግ እና የአስተዳደር ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ እንጠብቃለን። ሰብዓዊ መብት የመጀመሪያ ተግባራቸው እንደሚሆን አምነስቲ ይጠብቃል ።»

Human Rights Watch Logo

አምነስቲ እንደሚለው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያን ችግሮች ብቻቸውን ይፈታሉ ተብሎ አይጠበቅም።ለመፍትሄ የሀገሪቱ ምክር ቤት እና የሌሎች ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ ናቸው። አቶ ፍስሀ

«እንደ አንድ እርምጃ ልናየው እንችላለን። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መጥቷል። ብቻውን የነበረውን ይህን ሁሉ የተከማቸ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ስርዓት ብቻውን ማስተካከል አይችልም። ግን በአመራር ብቃት እና ሌሎችንም አስተባብሮ በመሥራት በተለይም ደግሞ የኢህአዴግን የተለያዩ አካላት በመምራት የማሻሻያ አጀንዳውን ማስፈጸም ይሆናል እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዛ አንድ ወሳኝ ናቸው ብለን እናስባለን።»

መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋች በበኩሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ በአደባባይ ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ በሚወጡ ሰዎች ላይ ከመጠን ያለፈ እርምጃ የሚወስዱ የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያሳስባል። በድርጅቱ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ፌሊክስ ሆርን ከዚህ ሌላ በአስቸኳይ ሊወስዱ ይገባቸዋል ያሏቸውን  ሌሎች እርምጃዎችንም ዘርዝረዋል።   

«የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት የመጀመሪያው ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። ሁለተኛው ደግሞ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ነው። የፖለቲካ ምህዳሩም መስፋት አለበት። ባለፉት ዓመታት ይሄ ጉዳይ ሲነሳ ነበር። ግን ያን ያህል የረባ ነገር አልታየም በዚትዮፕያ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ታዋቂ ተቃዋሚዎችን ለማሳተፍ የለስጋት እንዲናገሩ አባላትን እንዲመለምሉ ለማስቻል ጠንካራ ለውጥ ያስፈልጋል። ይህ በአስቸኳይ ተግባራዊ መሆን ያለበት ነው። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጣዳፊ ይህ ሊሆን እንደሚችል ለህዝቡ ተስፋ የሚሰጥ መልዕክት ማስተላለፍ አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተቃውሞዎችን ማየታችን አይቀርም»

LOGO CPJ

ለጋዜጠኞች መብት መከበር የሚታገለው መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው በምህጻሩ ሲፒጄ በመባል የሚጠራው ድርጅት አጋጣሚው ለኢትዮጵያ ጥሩ መሆኑን ገልጿል። ድርጅቱ በዚህ ወቅት ላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ካላቸው ጉዳዮች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እና በአዋጁ ሰብብ የታሰሩት በአስቸኳይ መፈታት ይገኙበታል።

«አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመገናኛ ብዙሀንን ነፃነት እና ሀሳብን በነጻ መግለፅን ለማስከበር በገዥው ግንባር ውስጥ ቁልፍ ለውጦችን የማድረግ በቂ ተጽእኖ ይኖራቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በመጀመሪያ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ በጣም አስፈላጊ ነው ። ሁኔታዎች እንዲረጋጉ መንግሥትም የዴሞክራሲ ምህዳሩን እንዲያሰፋ እና ጋዜጠኞች ብሎገሮች እና ሌሎች ራሳቸውን መግለጽ እንዲችሉየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ ማየት እንፈልጋለን። በአዋጁ ምክንያት የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ካለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተፈተው ማየት እንፈልጋለን። እንደሚመስለኝ  ኢትዮጵያም ሆነች ሌላው ዓለም እንዲሆን የሚመኘው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ጥረት ያደርጋሉ ብለን ተስፋ የምናደርግባቸው አዲሱ ወጣት የፖለቲካው ስርዓት ውስጥ ብቅ ማለታቸው ለኢትዮፕጵያ ጥሩ አጋጣሚ ነው።»

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል የሚሉት መቀመጫውን ብራሰልስ ያደረገው ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ማህበር  ሃላፊ አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ደግሞ በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አባብሰዋል የሚባሉት ህጎችና እና የፍትህ ስርዓቱ እንዲያስተካክል ጠይቀዋል።

«የሰብዓዊ መብት ጥሰት ህጋዊ መልክ እንዲይዝ ያደረጉ የህግ ማዕቀፎች በጠቅላላ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲወገዱ እንዲስተካከሉ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው። ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ አይደሉም። ስለዚህ የፍትህ ስርዓቱን ማስተካከል ተቀዳሚ ሥራቸውም ጭምር ካደረጉት ሰብዓዊ መብት የማክበሩ ነገር ተስፋ እየሰጠ ይሄዳል።»

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ