1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  የምግብ እጥረት፤ ደረጃዉ፤ ምክንያቱና መፍትሔዉ

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2009

«በአብዛኞቹ ሐገራት አሁን ያለዉን ቀዉስ የፈጠሩት ግጭቶች፤የመልካም አስተዳደር እጦትና ድርቅ ተዳምረዉ ነዉ።ብዙ ሕዝብ በረሐብ ከመሰቃየት አፋፍ ላይ የደረሰዉ በነዚሕ (ሰዎስት) ምክንያቶች ነዉ።የርዳታዉ ሥርዓት ደግሞ እነዚሕን መሠረታዊ ምክንያቶች በሚያቃልልበት መንገድ የተቀረፀ አይደለም።

https://p.dw.com/p/2ZlP8
Südsudan Dürre Volk Mundari
ምስል picture-alliance/abaca/AA/B. Bierrenbach Feder

Hunger in Afrika - MP3-Stereo

የተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራትን በመታዉ ድርቅና በአንዳዶቹ በሚካሔደዉ ጦርነት ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ እርዳታ እንዲሰጥ የሚደረገዉ ጥሪ እንደቀጠለ ነዉ።ግብረ ሠናይ ድርጅቶች እንደሚሉት እስካሁን በቂ እርዳታ አልደረሰም።በዚሕም ምክንያት በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ በሺሕ የሚቆጠሩ እንስሳት ሞተዋል።ደቡብ ሱዳንንና ሶማሊያ ዉስጥ ደግሞ የምግብ እጥረቱ ወደ ረሐብ ንሮ የሰዎችን ሕይወት እያጠፋ፤ በርካታ ነዋሪዎችን እያፈናቀለም ነዉ።ብሪታንያዊቷ እጥኚ ክርስቲና ቤኔት እንደሚሉት የምግብ እጥረቱ ሕይወት ማጥፋት ደረጃ ላይ መድረሱ የርዳታዉ ሥርዓት ትክክል አለመሆኑን ጠቋሚ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

Kenia Dammbau gegen Dürre
ምስል picture-alliance/AA/R. Canik

ረሐብ፤ ችጋር ይባል የምግብ እጥረት የዘንድሮዉ ጠንከር፤ በርከት፤ ሰፋ ብሏልም።ከሰሜን ናጄሪያ እስከ ዙምባቡዌ የሚገኝ ከአስራ-አምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚላስ-የሚቀመስ የለዉም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበዉ ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ወዲሕ አፍሪቃ የዘንድሮዉን ያክል ሰብአዊ ቀዉስ አጋጥሟት አያዉቅም።
የባሰዉ ምሥራቅ አፍሪቃ ነዉ።ደቡብ ሱዳን፤ ሶማሊያ፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ።ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ደግሞ ከባሰባቸዉም የባሰባቸዉ ናቸዉ።ምክንያቱ በርግጥ አዲስ አይደለም።ግልፅ ነዉ።የብሪታንያዉ የባሕር ማዶ ልማት ተቋም የሰብአዊ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ክሪስቲና ቤኔት እንደሚሉት ደግሞ ግልፁን ምክንያት ማስወገድ ይቻል ነበር።
                            
«እንዲያዉ የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ እንናገር ከተባለ የርዳታዉ ሥርዓት እልሰራም።ብዙ ሕዝብ አስቸኳይ ርዳታ ከሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።በነዚሕ ሐገራት ያለዉ ሁኔታ እና ቀዉሱን ያስከተለዉ ምክንያት ግን አስቀድሞ ሊወገድ ይችል ነበር።»
የርዳታዉ ሥርዓት በርግጥ ከጊዚያዊ መፍትሔነት ባለፍ ለዘለቄታዊ የተከረዉ ነገር የለም።ርዳታ ሁሌም የሚደርሰዉ ዘግይቶ በመሆኑ ለበጊዚያዊ መፍትሔነት ማገልገሉም እያጠራጠረ ነዉ።ዘላቂ ሊሆን የሚገባዉ የሠባዊ ቀዉሱን ምክንያት መርምሮ ከመሠረቱ ማስወገድ ነበር።
  ብዙ አጥኚዎች እንደሚሉት የዘንድሮዉ የምግብ እጥረት የተከሰተዉ በሰወስት ምክንያት ነዉ።ግጭት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት እና ድርቅ።ወይዘሮ ክርስቲና ቤኔትም በዚሕ ይስማማሉ።ምክንያቶቹ ከታወቁ መፍትሔም አይገድም ነበር ባይ ናቸዉ።
                                  
«በአብዛኞቹ ሐገራት አሁን ያለዉን ቀዉስ የፈጠሩት ግጭቶች፤የመልካም አስተዳደር እጦትና ድርቅ ተዳምረዉ ነዉ።ብዙ ሕዝብ በረሐብ ከመሰቃየት አፋፍ ላይ የደረሰዉ በነዚሕ (ሰዎስት) ምክንያቶች ነዉ።የርዳታዉ ሥርዓት ደግሞ እነዚሕን መሠረታዊ ምክንያቶች በሚያቃልልበት መንገድ የተቀረፀ አይደለም።የርዳታዉ ሥርዓት የተመሠረተዉ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ በአለቀ ሰዓት፤ አስራ-አንድ ሰዓት ላይ የገንዘብ ርዳታ እንዲደረግ ጥሪ በማድረግ ላይ ነዉ።ገና ከጅምሩ ችግሩ ከመድረሱ በፊት ብዙ ነገር ማድረግ እየተቻለ ችግሩ ከከፋ በኋላ መራወጡ ለችግረኞች የጠቀመዉ ነገር የለም።»
በአጥኚዋ እምነት ለረሐብ ወይም ለምግብ እጥረት ምክንያት የሆኑትን ሰወስቱን መሠረታዊ ችግሮች ለማስወገድ መወሰድ የሚገባዉ ርምጃ ሰዎች ለረሐብ ከመጋለጣቸዉ ከብዙ ዓመታት በፊት ሊወሰዱ ይገባል።በተለይ ግጭቶችና የመልካም አስተዳደር እጦት ዉጤታቸዉ አስቀድሞ ሥለሚታወቅ «ዓለም አቀፍ» የሚባለዉ ማሕበረሰብ  ገና ሲጀመሩ ማስወገድ ወይም ለማስወገድ መጣር በተገባዉ ነበር።በተለይ ግጭት።
                            
«ከዝርዝሬ መሐል ቀዳሚዉ በነዚሕ ሐገራት ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት መፍታት ነዉ።እንደ ደቡብ ሱዳን፤ የመን እና ሶማሊያ ያሉ ሐገራት ለበርካታ ዓመታት በግጭት እየተተራመሱ ነዉ።በየግጭቶቹ ትላልቆቹ ሐገራት ይሳተፋሉ።ከሁሉ በፊት ግጭቶቹን ለማስወገድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መደረግ አለበት።»
ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፤ ደቡብ ሱዳን ላይ ተደርጎ ነበር።ግን በግማሽ ልብ የተደረገዉ ጥረት ያመጣዉ ዉጤት ሌላ ጦርነት ነዉ።ለሶማሊያዉ ግጭት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ የሚገባዉ ዓለም ራሱ ተዋጊ ነዉ።የመንም እንዲሁ።የናይጄሪያም የተለየ አይደለም።እና በሰወስቱ የአፍሪቃ ሐገራትና የመን ዉስጥ 20 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል።

Äthiopien Dürre
ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene
Südsudan WFP Hilfe in Rubkuai
ምስል Reuters/S. Modola

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ