1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፤ የማይደን አብዮት፣ የክሪሚያ ባለቤትነት ጠቀመ ወይስ ጎዳ?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2016

በምዕራባዉያን የሚደረገፉት የማይደን አደባባይ አብዮተኞች ኪቭ ላይ ሲቦርቁ፣ ከ60 ዓመት በፊት ዋና ፀሐፊ ኽርሾቭ በጋዜጣ ቀላጤ ለዩክሬን የሰጧትን ግዛት ፑቲን በቀላሉ ግን በ«ሕዝበ ዉሳኔ» ከሩሲያ ቀየጧት።

https://p.dw.com/p/4dsG3
ድልድዩ የተገነባዉ ሩሲያ ክሪሚያንና ሴቫስቶፖልን ዳግም ከግዛትዋ ጋር ከቀየጠቻቸዉ በኋላ ነዉ።
ክሪሚያን ከዋናዉ የሩሲያ ግዛት የሚያገናኘዉ ረጅም ዘመናይ ድልድይ ምስል Sergei Malgavko/TASS/picture alliance

የማይደን አብዮት፣ የክሪሚያ ባለቤትነት ጠቀመ ወይስ ጎዳ?

የካቲት 21፣ 2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዩክሬን ፕሬዝደንት ቪክቶር ፌዶሮቪች ያኑኮቪች ከርዕሰ ከተማ ኪቭ ኮበለሉ።በማግስቱ የዩክሬርን ምክር ቤት ፕሬዝደንቱ ከስልጣን መወገዳቸዉን አወጀ። ተቃዋሚዎች ቦረቁ።ከሕዳር ማብቂያ ጀምሮ ቀኝ ፅንፈኞችን ከእዉነተኛ ለዉጥ ፈላጊዎች፣ አነጣጥሮ ተኳሾችን ከታዋቂ ስፖርተኞች፣ ምሑራንን ከማጅራት መቺ ቦዘኔዎች የቀየጠዉ፣የዋሽግተን-ብራስልስ መንግስታት ሙሉ ድጋፍ የጎረፈለት፣የምዕራባዉያን ሰላይ ቅጥረኞችን ከሩሲያ ብጤዎቻቸዉ ያተናነቀዉ የዩክሬን የአደባባይ አመፅ በድል ተጠናቀቀ።ለሩሲያ ሽንፈት።ለዋሽግተንና ተከታዮችዋ ድል። ከዚያስ? 

 

የሩሲያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ

ሰሞኑን የሩሲያ ህዝብ የወደፊት መሪዉን መርጧል።የምረጡኝ ዘመቻዉን፣ የድምፅ አሰጣጡን ሒደትና ዛሬ የተነገረዉን ዉጤት እንደተጠበቀዉ የምዕራባዉያን መንግስታት ባለሥልጣናት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል። የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ቀዳሚዋ ናቸዉ።

«ሩሲያ ዉስጥ የተደረገዉ ምርጫ ያለአማራጭ የተደረገ ነዉ።የምርጫዉ ሒደት እንዳሳየዉ የፑቲን ርምጃ የራሳቸዉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ቻርተር የሚፃረር ነዉ።»

የፈረንሳይ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የብሪታንያ ባለስልጣናትም ተመሳሳይ ተቃዉሞ አሰምተዋል።ብቻ የሩሲያ ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ ግን ቭላድሚር ፑቲንን ሌሎች ሶስት ፖለቲከኞች ተፊካክረዋቸዉ ነበር።የኮሚሽኑ የበላይ ኤላ ፓምፊሎቫ ዛሬ በይፋ እንዳወጁት ሰዉዬዉ ለአስምተኛ ዘመነ ሥልጣን ተመረጡ።በ87,29 ከመቶ በሆነ ድምፅ አሸነፉ።ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን።

ፑቲን ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ከተሰጠዉ ድምፅ ከ87 ከመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ነዉ ያሸነፉት
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ዘመነ ሥልጣን መመረጣቸዉ ከተረጋገጠ በኋላምስል Gavriil Grigorov/POOL/TASS/dpa/picture alliance

«75,932,111 መራጮች በሥልጣን ላይ ላሉት ርዕሠ ብሔር ድምፅ ሰጥተዋል።ይሕ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ነዉ።በ2018 ለቭዳሚር ፑቲን ድምፅ ሰጥተዉ የነበሩት መራጮች 56 ሚሊዮን 426 ሺሕ 399 ነበሩ።አሁን ግን 76 ሚሊዮን ግድም ነዉ።»

የክሪሚያ ዳግም ሩሲያዊነት

የዛሬ 10 አመት ልክ የዛሬን ዕለት የሞስኮዉ ጠንካራ ሰዉ ሌላ ድል አዉጀዉ ነበር።

«ክሪሚያ ዉስጥ በተደረገዉና በሕዝብ ፍላጎት በተመራዉ ሕዝበ ዉሳኔ ዉጤት መሠረት ዛሬ፣ የፌደራሉ ምክር ቤት ሁለት ግዛቶች ከሩሲያ ጋር ይቀይጡ ዘንድ ሕገ መንግስቱን እንዲያሻሻል እጠይቃለሁ።ግዛቶቹ  የክሪሚያ ሪፐብሊክና የሳቫስቶፖል ከተማ ናቸዉ።»

እንዳሁኑ ምርጫ ሁሉ የሞስኮዎችን እርምጃ ምሥራቆቹ ከሞልዶቫ እስከ ፖላንድ፣ምዕራቦቹ ከሞልታ እስከ ዩናይትድ ስቴት ሩሲያን ያላወገዘ  በሩሲያና በተባባሪዎችዋ ላይ ማዕቀብ ያልጣለ መንግስት የለም።ይሁንና ግሪኮች፣ሮሞች፤ ሞንጎሎች፣ ቬኒሲያዎች፣ ቱርኮች፣ ሩሲያዎች፣ ዩክሬኖች ለዘመናት የተፈራረቁባት ያቺ ጥንታዊ፣ ሥልታዊ፣ ዉብ ግዛትን ዳግም ከሞስኮዎች እቅፍ ፈርቅቆ ለማዉጣት እስካሁን በቀጥታና በኃይል የሞከረ የለም።

ክሪሚያ አዚመኛ ናት።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ንጉነገስት አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ትልቅ መድፋቸዉን ሳቫስቶፖል ያሉበት ምክንያት ብዙ እንደተተረከለት፣እንዳነጋገረም ነዉ።እየሩሳሌምን ጭምር ከእስላማዊዉ የቱርክ ሥርወመንግስት ነፃ ለማዉጣት የሚመኙት ኢትዮጵያዊዉ ክርስቲያኑ ንጉሰነገስት በ1862 ለብሪታንያዋ ልዕልት ቪክቶሪያና ለፈረንሳዩ ናፖሊዮን ሳልሳዊ ተመሳሳይ ደብዳቤ ሲፅፉ ግን የአዉሮጳ ክርስቲያናዊ ኃያላን መንግስታት ከሙስሊሟ ቱርክ ጋር ጥብቅ ወዳጆች እንደነበሩ በቅጡ ያጤኑ አይመስሉም።

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘዉዴ «ጣጠኛ» የሚሏት የአፄ ቴዎድሮስን የርዳታ ጥያቄ ያዘለች ደብዳቤ ለንደንና ፓሪስ የደረሰችዉ ሁለቱ የአዉሮጳ ገዢዎች በአብዛኛዉ የሩሲያን ወደ  ምስራቅና ደቡብ አዉሮጳ መስፋፋትን ለመግታት ከቱርክ ጋር የመሠረቱት ስልታዊ ወዳጅነት በጠነከረበት ወቅት በመሆኑ ኢትዮጵያዊዉ ንጉስ ያገኙት ድጋፍ የለም።

በማበጥ ላይ የነበሩት የለንደንና የፓሪስ ቅኝ ገዢዎች ክንዱ ከዛለዉ ከቱርክ ሥርወ-መንግስት ጋር አብረዉ እንደነሱዉ ሁሉ በመፈርጠም ላይ የነበረዉን የሩሲያያን ሥርወመንግስት ከ1853 ጀምረዉ ለ3 ዓመታት ወግተዋል።ዋናዉ የዉጊያ አዉድ ክርሚያ ነበረች።

ሩሲያ የክሪም ሪፐብሊክንና የሳቫስቶፖል ከተማን ከግማደ ግዛትዋ መቀየጧን ያወጀችዉ እግአ መጋቢት 18፣2022 ነዉ
የክሪሚያ ሪፐብሊክና የሳቭስቶፖል ከተማ ከሩሲያ ጋር በይፋ የተቀየጡበት ዕለት ሲከበርምስል Yevgeny Biyatov/AFP/Getty Images

ቱርክ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ሰርዲኒያ ባንድ በኩል፣ ሩሲያ፣ ሰርቢያና ግሪክ በሌላ በኩል ሆነዉ በገጠሙት ጦርነት ከሁለቱም ወገን ከ7 መቶ ሺህ የሚበልጥ ሰዉ አልቋል።ጦርነቱ የተደረገበት መቶኛ ዓመት በ1954 ሲዘከር ግን የያኔዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ኒኪታ ኽርሾቭ በአጭር የጋዜጣ አዋጅ ግዛቲቱን ለዩክሬን ሪፐብሊክ ሰጡ።የዛሬ 10 ዓመት ልክ የዛሬን ቀን እንደገና ከሩሲያ ተቀየጠች።የክሪሚያና የሳቫስቶፖል ነዋሪዎች እንደሚሉት ግዛታቸዉ ከሩሲያ ፌደሬሽን ጋር ዳግም ከተቀየጡ ወዲሕ ኑሯቸዉ ብዙ ተሻሽሏል።ግዛታቸዉ እያደገች፣ ባሕል፣ቋንቋቸዉም እየበለፀገ ነዉ።እሷ እንዲሕ ትላለች።

«የማንነጣጠል የመሆናችን ምልክት የክሪሚያ ድልድይ ነዉ።40 አካባቢዎችን የሚያገናኘዉ የታቭሪድ አዉራ ጎዳና።ማዕከላችን ሳምሾክ ነዉ።በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የረቀቀ ቀዶ-ሕክምና ለማግኘት ወደ ዋናዉ ግዛት መሔድ አያስፈልገንም።»

እሱም፣-

«አዉራ ጎዳናዎቹ፣ድልድዮቹ፣ሆስፒታሎቹ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዉ፣ መዋዕለ ሕፃናቱ ሁሉም ነገር ከዚሕ በፊት የሌለ ያክል እየታየ ነዉ።በየመጋዘኑ በርካታ ሸቀጦች አሉ።የኛ የክሪሚያዎች ሸቀጦች።ክሪሚያ ሩሲያ ናት።ሁሌም ሩሲያ እንደነበረች ሁሉ ወደፊትም እንደሆነች ትቀጥላለች።»

ይሁንና የምዕራባዉያን መንግስታት፣መገናኛ ዘዴዎችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ክሪሚያም ሆነ በተቀረዉ የሩሲያ ግዛት የቭላድሚር ፑቲንን አስተዳደር መቃወም፣ መተቸትም ሆነ ሐሰብን በነፃነት የመግለፅ መብት ክፉኛ ተሸርሽሯል።የፑቲን አስተዳደር በቅርቡ የሞተዉን አሌክሳንደር ናባልኒን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎቹን አስገድሏል ወይም አሳስሯል በማለትም ያወግዙታል።

ጠብ፣ ፍጥጫ፣ ሽኩቻ አዙሪት ለማን በጀ?

 

ወቀሳ፤ ዉንጀላ፣ ዉግዘት፣ የማዕቀብ ቅጣቱ መሰረት ኖረዉም አልኖረዉ ክርሚያ ዛሬም የሞስኮ-ሚኒስክ፣ የኪቭ-ዋሽግተን ብራስልስ ተዘዋዋሪ ጦርነት ይጨጓጉፋታል።ሕዳር 2013 ኪቭ ላይ የተቀጣጠለዉ ያደባባይ አመፅ የካቲት 2014 ላይ ፕሬዝደንት ያኑኮቪችን ከሥልጣንም-ከሐገርም በማባረር ሲጠናቀቅ ክሪሚያንጨምሮ ለዩክሬኖች የዲሞክራሲ-ብልፅግና መሠረት ተብሎ፣ ብዙ ተወርቶ ብዙ ተነግሮለት ነበር።

እርግጥ ነዉ የማይዳን አብዮት የአሜሪካኖች፣ የብሪታንያዎች፣ የጀርመኖች፣ የፈረንሳዮች ገንዘብ፣የስልለላ ጥበብ፣የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ጡንጫ፣ የምሥራቅ አዉሮጶች የመሐል ሰፋሪነት ደባና ሴራ አልተለየዉም። የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬተርቬለና የአሜሪካ ሴናተር ጆን ማክኬን ሳይቀሩ ኪቭ ድረስ ተጉዞዉ ደግፈዉታል።

ይህ ሁሉ ድጋፍ ሞልቶ የተረፈዉ የዩክሬን የአደባባይ ተቃዉሞ ሰልፍ በትንሽ ግምት ከመቶ በላይ ህይወት ጠፎቶበታል፤ በቢሊዮን ዶላር የተገመተ ንብረት ወድሞበታል።የመገናኛ ዘዴ ኃላፊዎች ሳይቀሩ ባደባባይ ተደብድበዋል።

ከዚሕ ሁሉ ምስቅልቅል በኋላ የተገኘዉ ዉጤት የሩሲያ ሽንፈት፣ የምዕራቦች ድል ተደርጎ መቆጠሩ ብዚዎች እንደሚሉት ለሞስኮዎች ሥጋት ለኋላ እርምጃቸዉም መሠረት ሆኗል።በምዕራባዉያን የሚደረገፉት የማይደን አደባባይ አብዮተኞች ኪቭ ላይ ሲቦርቁ፣ ከ60 ዓመት በፊት ዋና ፀሐፊ ኽርሾቭ በጋዜጣ ቀላጤ ለዩክሬን የሰጧትን ግዛት ፑቲን በቀላሉ ግን በ«ሕዝበ ዉሳኔ» ከሩሲያ ቀየጧት።የፖለቲካ ተንታኝ አባስ ጋልያሞቭ እንደሚሉት ፑቲን ክሪሚያን በቀላሉ መቆጣጣራቸዉ ሳያታልላቸዉ አልቀረም።

                              

«ፑቲን ክሪሚያን በቀላሉ መቆጣጣራቸዉ በራሳቸዉ አዕምሮ ዉስጥ መጥፎ ቧልት አሳድሯል።ይሕም ፑቲን በ2022 ዩክሬን የገቡትን ያንኑ (የክሪሚያዉን) እደግመዋለሁ ብለዉ ነበር።ለረጅም ጊዜ ለመዋጋት አላቀዱም ነበር።የክሪሚያዉ ዓይነት ነገር ግን ትንሽ ሰፋ ብሎ ይደገማል ብለዉ አስበዉ ነበር።»

የዩክሬን ጦር ኃይል ወይም ደጋፊዎቹ እንደሆኑ የጠረጠረዉ ጥቃት ድልድዩን የጎዳዉ ጥቅምት 2022 ነበር።ግን ወዲያዉ ተጠግኗል።
የዩክሬኑ ጦርነት የክሪምና የሩሲያ አንድነት ዋና ምልክት የሆነዉን ዘመናይ ድልድይም የጥፋት ኢላማ አድርጎታልምስል REUTERS

በምዕራባዉያንም በኩል የነበረዉ ግምትም ከሞስኮዎች የተለየ አልነበረም።በ1990ዎቹ ከሶቭየት ሕብረት እቅፍ የወጡት የምስራቅ አዉሮጳ ሐገራትን ያስከተሉት ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያ መንግስት፣ ኩባንዮች፣ በነዳጅ፣ በባንክ፣ በኢንዱስትሪ፣፣በአየር በረራ፣ በባለሥልጣናትና ቱጃሮች ላይ የጣሉት ማዕቀብ ሩሲያን ባጭር ጊዜ ዉስጥ ያሽመደምዳል ተብሎ ነበረ።አልሆነም።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ለኪየቭ የሚጋዘዉ ዘመናይ የጦር መሳሪያ ብዛት፣ ወታደራዊ ስልጠናዉ፣ የመረጃና የገንዘብ ድጋፍ በአብዛኛዉ የአዉሮጶችን ምጣኔ ሐብት እያቀጨጨ፣ ዩክሬንን እያወደመ፣ አስር ሺሕ ሕዝቧን እየገደለ\ ሚሊዮኖች እያሰደደ፣ ሩሲያን እያከሰረ፣ ዓመት ከመቁጠር ሌላ ለዓለም ሰላም የተከረዉ የለም።ዛሬም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ሕይወት የማዳን፣ የድርድር፣የዉይይት፣ የሰላም ድምፅ መስማት አለመሻታቸዉ ነዉ ሰቀቀኑ።

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ