1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ ኃይሉ ርምጃ በመብት ተሟጋቾች ዕይታ፤

ሐሙስ፣ ነሐሴ 5 2008

ባለፈዉ ቅዳሜ እሁድ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልላዊ መስተዳድር የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳዉን ሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃዉሞ ለመበታተን የመንግሥት ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀማቸዉን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች አመለከቱ።

https://p.dw.com/p/1JglA
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

[No title]

ፍሪደም ሃዉስ የተሰኘዉ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት የፀጥታ ኃይሉ በመቶ የሚቆጠሩትን ገድሏል፤ በሽዎች የሚገመቱትን ደግሞ አሥሯል ባለበት መግለጫዉ፤ መንግሥት ጭካኔ የተሞላበትን የሕዝብ ተቃዉሞ ማመቂያ ስልት ባስቸኳይ እንዲያቆም አሳስቧ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ሰላማዊ ሰልፎችን በመበተኑ ሂደት የተፈጸሙ ወንጀሎች በገለልተኛ ወገን ባፋጣኝ ተጣርተዉ ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ሕዝብ ተቃዉሞዉን ማሰማት የጀመረዉ ባለፈዉ ሕዳር ወር የተቀናጀ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በመቃወም ነዉ። ምንም እንኳን ዉሎ አድሮ መንግሥት ዉዝግብ ያስነሳዉን እቅድ ተግባራዊነት አቁሜያለሁ ቢልም የመልካም አስተዳደር እና የፍትሃዊነት ጥያቄዉ ወራት ሳምንታትን ተሻግሮም ዛሬም መቀጠሉ እየታየ እና እየተነገረ ነዉ። በሐምሌ ወር መባቻ ላይ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት ላይ ከመንግሥት ወገን የተወሰደ ርምጃ ኦሮሚያ ዉስጥ ሲብላላ የቆየዉን ቅሬታ ደርቦ ጎንደር ላይ መታየት ጀመረ። ከሳምንት በፊት በዕለተ እሁድ ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ያስተናገደችዉ ጎንደር፤ በሳምንቱ ጥይት ሲንጣጣባት ሰዎችም ሲወድቁ ሲቆስሉባት ታየ። ተቃዉሞዉ ወደ ባህር ዳር ሲሻገም ጥይቱ ቀጠሎ ቁጥሩ በርከት ያለ ሰዉ ሕይወት ቀጠፈ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳምንቱ ማለቂያ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎችን የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ለማመቅ የተጠቀመዉ የኃይል መንገድ ቢነቅፍም የተለመደ አካሄድ እንደሆነ ግን ሳይጠቅስ አላለፈም። የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍሰሃ ተክሉ እንዴትነቱን ይናገራሉ።

Logo Amnesty International

እሳቸዉ እንደሚሉት ባዶ እጁን ለሰላማዊ ሰልፍ የወጣ ሕዝብ ላይ ጥይት መተኮሱ ብቻም አይደለም የሚያነጋግረዉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ በአማራ ዳር እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸመዉ የኃይል ርምጃ ወደ አንድ መቶ ገደማ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታዉቋል። የተቃዉሞ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የዋለዉ ኃይል ያስከተለዉን ጉዳት እና ከሁሉም አቅጣጫ የተፈጸመዉን ወንጀል በገለልተኛ ወገን እና በአግባቡ ተመርምሮ ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ከ1997 ሀገራዊ ምርጫ ማግሥት የነበረዉ የዉጤት ዉዝግብ ያስከተለዉ የሕዝብ ተቃዉሞ ከመቶ በላይ ሰዎች ሕይወት አሳጥቶ፤ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ የተፈጠረዉን አቶ ፍሰኃ ያስታዉሳሉ፤ የከዚህ በፊት ምሳሌዎችን መሠረት አድርጎ አምነስቲ ከሰሞኑ ያጋጠመዉን የኃይል ርምጃ ያስከተለዉ ጉዳት በአግባቡ እንዲጣራ ላቀረበዉ ጥያቄ ምላሽ አገኛለሁ ብሎ ያምናል?

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ