1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመልካም አስተዳደር ጉድለት በኢትዮጵያ

Merga Yonas Bulaሐሙስ፣ የካቲት 3 2008

የሕግ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ 10 ቡድን አቋቁሞ የአገሪቱን የመልካም አስተዳደር ይዞታ እንደፈተሸ እና ዉጤቱንም በ26 ገጽ ዘገባ በማካተት ለፓርላማ አባላት እና የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት እንዳቀረበ ነዉ ዘገባዎች የሚያሳዩት።

https://p.dw.com/p/1HsjI
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

[No title]

ከመንግስት ተቋሞች የመልካም አስተዳደር ችግር አለባቸዉ ተብለዉ በዘገባዉ ከተጠቀሱት መካከል የፍትህ ሚንስቴር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትርክ ኃይል አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ዉኃና ፍሳሽ ባለስልጣን፤ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን እንደምገኙበት ዘገባዉ ሲቀርብ ምክር ቤት ተገኝቶ የነበረዉ ጋዜጤኛ ዮሐንስ አንበርብር ለዶቼ ቬሌ ገልጿል። የሕግ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዉ በዘገባዉ ከኅብረተሰቡ ተገልጋዮች እና ሠራተኞችን አነጋግሮ እንደነበር ዮሐንስ ይጠቅሳል።


ትራንስፓረንሲ ኢንቴርናሽናል የተሰኘዉ ተቋም በኢትዮጵያ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማቶች ሙስና ተንሰረፋፍቶ እንደሚገኝ ባወጠዉ ዘገባ አሰነብቧል። በምክር ቤት የቀረበዉ ዘገባ ሙስናን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቋቋመዉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ራሱም ለትልቅ ትቸት እንደተጋለጠ ዮሐንስ ይናገራል። ኮሚሽኑ የተተቸበት ምክንያት አድሎአዊ አሰራር በኮሚሽኑ ዉስጥ መፈጠሩ፣ ፀረ ዴሞክራስያዊ ግንኙነት መኖሩ፣ ጤናማ የአመራርና የሠራተኛ ግኑኝነት ያልተፈጠረ መሆኑን እና ለሥራ የሚፍጨረጨሩ ሠራተኞችን ከቦታ ወደ ቦታ ማዘዋወሩ እና ኮሚሽኑ ዉስጥ ቆይቶ ሃብት ያካበቱ ሰዎች ላይ ምርመራ አለማካሄዱ ነዉ ሲል ዘገባዉ ያትታል።

Äthiopien Addis Abeba Parlamentssitzung
ምስል DW/G. Tedla

በዚህ ምክንያትም ዘገባዉን ተከትሎ ከፍትህ እና ከፀረ ሙስና አካል የተገኙት ኃላፊዎች ከፍተኛ ትችት እንደቀረበባቸዉ ተሰምቷል። ስለዚህ፣ ይላል ዮሐንስ፣ ኮሚሽኑ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ የሙስና ጉዳዮችን መቆጣጠር ይችላል ብሎ መጠበቅ ከባድ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን መልካም አስተዳደርን ለማምጣት ምንም አይነት እርምጃ የማይወስዱ ኃላፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ አፈ ጉባኤዉ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናግረዋል።


ተመሳሳይ የመልካም አስተዳደር ችግር በጉሙሩክ ባለስልጣን እና በባንኮች አካባቢ እንዳለም ዘገባዉ እንደሚጠቅስ ያመለከተዉ ጋዜጠኛ ዮሐንስ፤ የዘገባዉ ዓላማ የኮምሽኑ ምክትል ኮሚሽነር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እናም ሌሎች ባለስልጠኖች በተገኙበት የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስዱ እንደሆነ አመልክቷል።


የፓርላማዉ ስነምግባር ደንብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃለፊዎች ከሥራ የማስወገድ እርምጃ መዉሰድ እንደሚችሉ፣ እሳቸዉም ካልወሰዱት የመታመኛ ድምፅ ማለትም vote of confidence ተጠቅሞ ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ እርምጃ መዉሰድ እንደሚችል እንደሚደነግግ ጋዜጠኛ ዮሐንስ ጠቅሷል። በዶቼ ቬሌ የፌስቡክ ገፅ ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በተደረገዉ ዉይይት አብዛኞቹ ተሳታፊዎች አገሪቱ ዉስጥ ያለዉ የመልካም አስተዳደር ችግር ይሻሻላል ብለዉ እንደማይጠብቁ የገለፁ ሲሆን፤ እንዲሻሻል ኃላፊዎቹ ራሳቸዉ በቅድሚያ ከሙስናና አድሏዊ አሰራር መፅዳት አንዳለባቸዉ አመልክተዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ