1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልጅ ስደተኞች፤ ሶሪያና አፍጋኒስታን

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2008

ኔማት ከአፍጋኒስታን ነው የፈለሰው፤ አቡድ ደግሞ ስደቱ ከሶሪያ ነው። ሁለቱም ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት በጎርጎሪዮሱ 2015 ዓ.ም. ወደ ጀርመን ለብቻቸው የተሰደዱ ልጆች ናቸው። 60,000 ገደማ ኔማት እና አቡድን የመሰሉ የልጅ ስደተኞች በ2015 ዓ.ም. ጀርመን ገብተዋል። ሁለቱ ታሪካቸውን ለዶይቸ ቬለ ይነግራሉ።

https://p.dw.com/p/1HTRj
Weihnachtsserie Flüchtlingskinder Landsberg kochen
ምስል DW/W.Dick

[No title]

ኔማት እና አቡድ ጀርመን የልጆች መጠለያ ማዕከል ውስጥ ምግባቸውን የሚያበስሉት በአንድነት ነው። የ16 እና የ17 ዓመት ታዳጊ ወጣቶቹ የልጅ ስደተኞች ከመጠለያው ውጪ ደግሞ ከጀርመናውያን ጓደኞቻቸው ጋር እየተቀላለዱ ዞር ዞርም ይላሉ። ላንድስበርግ ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት እና ታዳጊዎች ማቆያ ማዕከል ማዕድ ቤት መደርደሪያ ላይ የተለያዩ የምግብ አይነቶች አበሳሰልን የሚያብራራ መጽሐፍ ተቀምጧል። ኔማት እና አቡድ ግን ምግብ ሲያበስሉ እጅግ የሚያስደስታቸው ስጋ በሩዝ መቀቀሉን ነው። ለውጥ ሲያስፈልጋቸውም ያው ስጋ በሩዝ ነው ምርጫቸው። አንዳንዴ የግድ ሲሆንባቸው ብቻ ፓስታ ይቀቅላሉ።

ኔማት እና አቡድ ጀርመን የልጆች መጠለያ ማዕከል ውስጥ
ኔማት እና አቡድ ጀርመን የልጆች መጠለያ ማዕከል ውስጥምስል DW/W.Dick

ሁለቱም ታዳጊዎች ጀርመን በገቡ በአንድ ዓመታቸው ጥሩ ጀርመንኛ መናገር ጀምረዋል። የሚኖሩበት አካባቢ የባየር የነጋገር ቅላፄ ተፅዕኖ አላሳረፈባቸውም።

«የባየር የአነጋገር ለዛ ለኔ አስቂኝ ነው። ደግሞም የተማርኩት ያን አይደለም። በመላ ሀገሪቱ የሚሰጠው ከፍተኛ ጀርመን የሚባለውን ጀርመንኛ ነው የተማርኩት። ለእኔ እሱ ይቀለኛል።»

በአፍጋኒስታናውያን እና ሶሪያውያን መካከል በሚፈጠር የአመለካከት ልዩነት ብዙውን ጊዜ ውጥረት እንደሚከሰት የላንድስበርግ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ማቆያ ማዕከል የምክር አገልግሎት ሠራተኛ ይናገራሉ። ለኔማት እና አቡድ ግን ማንነት እና እምነት ብዙም ግድ አይሰጣቸውም። ሁለቱን ያገናኛቸው ውስጣዊ ስሜት ነው። ኔማት ስለ አቡድ ሲናገር፤

«ዝምተኛ እና ጭምት ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ደስ ይሉኛል።»

ላንድስበርግ ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት እና ታዳጊዎች ማቆያ ማዕከል
ላንድስበርግ ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት እና ታዳጊዎች ማቆያ ማዕከልምስል DW/W.Dick

ሁለቱ ታዳጊዎች በእጃቸው ሳይሆን በአዕምሯቸው ነው መሥራት የሚፈቅዱት። አቡድ መሆን የሚሻው የመረጃ ሠራተኛነት ነው። ኔማት ለመኪና ሜካኒክነት ዝንባሌ አለው። ሁለቱም ታዲያ የሚፈልጉትን ለማግኘት በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ መሆን ያሻቸዋል። ለዚያም በሥራ ሥልጠና መስጪያ ውስጥ ተግተው እየሠሩ ነው።

ኔማት ቤተሰቡን ያጣው አፍጋኒስታን ውስጥ ነው። ስለዚያ ግን ብዙም መናገር አይሻም። የስደት ጉዞው የሚጀምረው ባለፈው ዓመት ነው። መጀመሪያ ለመንፈቅ ያኽል ኢራን መቆየት ነበረበት። ከዚያ ተነስቶም ወደ ቱርክ ያቀናል። ከቱርክ ደግሞ በመናኛ ጀልባ ከሌሎች ስደተኞች ጋር ታጭቆ ጉዞ ወደ ግሪክ። ከግሪክ የባልካን መስመር በሚባለው አድርጎ ነበር ጀርመን የገባው።

«ሁሌም ስለ ጀርመን የምሰማው ድንቅ ሀገር እንደሆነች ነበር። እዚያ ሣንቲም መያዝ እንደሚቻል፤ በነፃነትም እንደሚኖር ነበር የምሰማው።»

ነፃነት እና ፍትኅ ለአቡድ ከምንም በላይ የሚሻቸው ነገሮች ናቸው። በሶሪያ ጦርነት ቤተሰቦቹ ምርጥ የሚባል ቤታቸውን፤ ሥራቸውን እና ሀገራቸውን አጥተዋል። ከወላጆቹ እና ስምንት እህት ወንድሞቹ ጋር በሊባኖስ አድርጎ ግብፅ ቢገባም እዛ የገጠመው ሌላ ፈተና ነበር። ልጅ ቢሆንም ጀርመን ለመምጣት በቀን ለ12 ሰአታት ይሠራ ነበር። እናም እንደምንም 3000 ዩሮ አጠራቅሞ በአነስተኛ ጀልባ ጉዞ ወደ ጀርመን። ለ6 ቀናት ባሕር ላይ እንደተንከራተቱም ይገልጣል። ከሞት የተረፈውም ለጥቂት ነበር። 300 ስደተኞችን አጭቃ የነበረችው አነስተኛ ጀልባቸው ነፍስ አድን ሔሊኮፕተር ባይደርስላት ኖሩ ዛሬ አቡድ የለም ነበር።

ይኽን ሁሉ መከራ አልፎ የመጣው አቡድ እና ጓደኛው ኔማት ጀርመን ውስጥ ቆይተው መኖር ነው ፍላጎታቸው። አንድ ወቅት ግን ወደ ሀገራችን እንላካለን የሚል ስጋት ሁሌም እንዳጠላባቸው ነው። እንዲያም ሆኖ ጀርመን ሕፃናት እና ታዳጊዎች ማቆያ ውስጥ ለተደረገላቸው አቀባበል ምጋናቸው ይገልጣሉ።

ቮልፍጋንግ ዲክ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ