1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ምሥቅልቅልና ተመድ

ሰኞ፣ የካቲት 14 2008

የቃዛፊ አገዛዝ ጨቋኝ አምባገነን እንደነበር አያጠያይቅም።ይሁንና ከየካቲት 2011 እስካሁን በተቆጠረዉ አምስት ዓመት ሊቢያ ዉስጥ የተገደለ እና ከሊቢያ የተሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር አርባ ዓመት በዘለቀዉ የቃዛፊ አገዛዝ ከተገደለና ከተሰደደዉ በብዙ ቁጥር ይበልጣል።የሊቢያ ዛሬ ምግብ፤ መድሐኒት፤ ዉሐና መብራት የሚናፈቅባት ሐገር ሆናለች።

https://p.dw.com/p/1I02V
ምስል Reuters/M. Ngan

ሊቢያ ምሥቅልቅልና ተመድ

ፖለቲከኞችዋ ይወነጃጀሉ፤ ይጋጩባታል።በየጎጡ የሸመቁ ታጣቂዎችዋ ይጋደሉ፤ ይገድሉ፤ ይዘርፉ፤ ያስሩ፤ይገርፉባታል።አሸባሪዎች አንገት ይቀሉባታል።ስደተኖች፤ ዲፕሎማቶች፤ይታገቱ፤ ይደፈሩ፤ ይገደሉባትል።ሊቢያ።አምስተኛ ዓመቷ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፖሎማቶች ለቁጥር የሚያታክቱ ፖለቲከኛ-ታጣቂዎችዋን ለማስታረቅ ለዓመታት ያደረጉት ጥረት-ሰሞኑን የተስፋ ጭላንጭል ፈንጥቆ ነበር።ከአራት-ዓመት ከመንፈቅ በፊት ከጨቋች አረመነዎች ነፃ አወጣናት ብለዉ የነበሩት አሜሪካኖችግንዳግም በጄት ያጋዩዋት ገቡ።ሊቢያ።

Kanada Luftwaffe Symbolbild
ምስል picture alliance/dpa/P. Reed/ Department of National Defence

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አልጋ-ወራሽ አከል ልጅ ሠይፍ ዓል ኢስላም ለዉጪ ጋዜጠኛ እንደ ባለሥልጣን የመጨራሻቸዉን መግለጫ የሰጡት ሚያዚያ 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር) ነበር።ለአርባ-ሁለት ዘመናትየፀናዉን የአባታቸዉን አገዛዝ ለማስወገድ የሐገራቸዉ አማፂያን ከምድር፤ የምዕራባዉያን ጦር ካየርና ከባሕር በሚገዘግዙበት በዚያን ወቅት«ሰወሰት ዕቅድ አለን»አሉት የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክሱ ወጣት ዶክተር ለለንደኑ ጋዜጠኛ።«ሰወስት ዕቅድ ሀ,ለና ሐ አለን።ዕቅድ ሀ ሊቢያ ዉስጥ መኖርና ሊቢያ ዉስጥ መሞት፤ዕቅድ ለ ሊቢያ ዉስጥ መኖርና ሊቢያ ዉስጥ መሞት፤ዕቅድ ሐ ሊቢያ ዉስጥ መኖርና ሊቢያ ዉስጥ መሞትሰይፍ አል ኢስላም ቃዛፊ ዛሬ «ከቆሙት በታች»የሚባሉ እንጂ በርግጥ አልሞቱም።ታሠሩ እንጂ በርግጥ ካገራቸዉ አልወጡም።ሐገራቸዉ ግን እንደአባት-ወድሞቻቸዉ «ሞተችወይም እንደ እሕቶቻቸዉ ተሰደደች እንዳትባል ሐገር ናት።አለች እንዳትባል ግን ፈርሳለች።በማዕከላዊ መንግሥት ፋንታ ሁለት መንግሥታት፤ በሐገር መከላከያ ጦር ምትክ በሺሕ የሚቆጠሩ የሚሊሺያ ቡድናት፤በፖሊስ ሐይል ምትክ አሸባሪ ድርጅቶች፤ በአንድ መሪ ምትክ ሁለት ጠቅላይ ሚንስትሮች፤ በመቶ የሚቆጠሩ የጦር አበጋዞች ይፈነጩባታል።የነዳጅ ጉድጓዶችዋ፤ የገንዘብ ማዕከለቷ፤ የመስሪያ-መኖሪያ ቤት ዉብ ሕንፃዎችዋ፤ አዉሮፕላን ማረሪያዎችዋ፤ ዘመናይ መንገድ፤ድልድይ-ወደቦችዋ ፈራርሰዋል። የነዳጅ፤የመብራት፤ የዉሐ መስመረችዋ ተበጣጥሰዋል።

ከሁሉም አስከፊዉ ከስድስት ሚሊዮን ያሕል ሕዝቧ፤ የመብት ተሟጋቾች እንደዘገቡት አንድ አራተኛዉ ተሰድዷል።ከተቀረዉ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሞቷል፤ የቆሠለ፤በየእስር ቤቱ የታጎረ፤ ለሚሊሺያነት የተመለመለዉን በትክክል የቆጠረዉ የለም።

በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛነቱን ሥልጣን ባለፈዉ ሕዳር የተረከቡት ጀርመናዊዉ ዲፕሎማት ማርቲን ኮብለር እንደሚሉት የወድመት-ጥፋቱ አንዱ ምክንያት በዲፕሎማሲዉ ቋንቋ «ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ» -የሚባለዉ ሐያል ዓለም ሊቢያን መዘንጋቱ ነዉ።«ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ያቺን ሐገር ከ2011 ጀምሮ ብቻዋን በመተዉ ስሕተት ሰርቷል።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቃዛፊ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሊቢያዉያን አብዮቱን ከግብ ያደርሱታል ማለቱ አልተሳካም።ይሕ ስሕተት ነበር።አሁን ሁላችንም እናዉቀዋለን።»

የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን መንግሥትን ያስወገደዉን ጦር የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ያዘመቱት የዓለም ሐያል-ሐብታም መንግሥታት መሪዎች ግን በያኔ ቃል-ምግባራቸዉ ከሊቢያ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዉ ነበር።የያኔዉ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኒኮላይ ሳርኮዚ-ከፓሪስ፤ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ከለንደን ተጠራርተዉ ትሪፖሊ ድረስ ተጉዘዉ የድል ጮቤ ለመርገጥ-ማስረገጥ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዛፊ እስኪገደሉ እንኳ ለመጠበቅ አልታገሱም ነበር።

Libyen Parlament
ምስል picture-alliance/dpa/S.Elmhedwi

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የብሪታንያ አጋራቸዉ ቶኒ ብሌር በ2003 ባግዳድ ላይ ያሉ-ያደረጉትን ሳርኮዚና ካሜሩን ትሪፖሊ ላይ ደገሙት።መስከረም 2011።«በጣም አስደሳች ቀን ነዉ።እዚሕ በመገኘታችን ተደስተናል።»ሳርኮዚ ናቸዉ።ካሜሩን አከሉ።«ብሪታንያ ያደረገችዉ አስተዋፅኦ አለ።በዚሕ እኮራለሁ።ለዚሕ ዉጤት ያደረሰዉን ተግባር የፈፀሙት ግን ሊቢያዎች ናቸዉ።የመጣሁት እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ነዉ።ለወደፊቱም ሐገራቸዉን መልሰዉ ሲገነቡ እንዴት እንደምንረዳቸዉ ለማየትም ነዉ።»

ሊቢያ ዳግም መገንባት አይደለም ያኔ በነበረዉ ጥፋትም አልቆመችም።RT በሚል የእንግሊዝኛ ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የሩሲያዉ ዓለም አቀፉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ እንደዘገበዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ሊቢያን ዳግም ለመገንባት መሐንዲስ፤ሐኪም፤አስተማሪ ሳይሆን ዘንድሮ በአምስተኛ ዐመታቸዉ እንኳ ተዋጊ ጦር ነዉ ያዘመቱት።

ጦሩ የሊቢያን ሕዝብ ወይም ስደተኞን ወይም ዲፕሎማቶችን ከታጣቂ፤ አሸባሪ፤ ወሮበሎች ግድያ፤ እገታ ዘረፋ የሚከላከል አይደለም።በየሥፍራዉ እንደተለመደዉ ሠላም የማስከበር ተልዕኮም የለዉም።ዓለማዉ ጠባቂ-ባለቤት የሌላቸዉን የሊቢያን የነዳጅ ጉርጓዶች መቆጣር ነዉ።

በዘገባዉ መሠረት የምዕራብ አዉሮጳ እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት በኢጣሊያዊ ጄኔራል የሚታዘዝ እስከ ስድስት ሺሕ የሚደርሱ ወታደሮች ለማዝመት አቅደዋል።እስካሁን ከዘመቱት ወታደሮች አንድ ሺዉ የብሪታንያ ልዩ ጦር ባልደረቦች ናቸዉ።

በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ዘገባዉን ማረጋገጥ አልፈለጉም።«ሊቢያ ዉስጥ እግረኛ ጦር ማሥፈር የማንም አጀንዳ አይመስለኝም።ምናልባት ሊቢያ ዉስጥ እንዳዲስ መገንባት ላለበት የፀጥታ አስከባሪ ሐይል ሥልጠና ለመስጠት የሚደረግ ዝግጅት ሊኖር ይችላል።የፀጥታ ጉዳይ በጣም ባስቸኳይ የሚያስፈልግ ነገር ነዉ።የምናወራዉ ሥለተመሰቃሰለች፤ ሥርዓተ-ዓልበኝነት ሥለነገሰባት፤ ሚሊሺያዎች ሥለተንሰራፉባት ሐገር ነዉ።ሥለዚሕ አንድ ወጥ ፀጥታ አስከባሪ ያስፈልጋታል።የተበታተነ ፖሊስ አይደለም አንድ የዕዝ ስርዓቱን የጠበቀ ሐይል።»

ለኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊም ሆነ ለጨቋኝ ሥርዓታቸዉ ያኔም-ዛሬም የሚቆረቀር ከነበረ እና ካለ የዚያ ሥራዓት ተጠቃሚዎች ብቻ ናቸዉ።ሰዉዬዉም አንባገነን ገዢ እንጂ ነበይ አልነበሩም።ከመገደላቸዉ ከጥቂት ወራት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ካነጋገሩት ጥቂት የሐያል መንግሥታት ፖለቲከኞች አንዱ የቀድሞዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ነበር።

ዘ-ጋርዲያን የተባለዉ የብሪታንያ ጋዜጣ ባለፈዉ ወር እንደዘገበዉ ቃዛፊ የካቲት 25 2011 ለቶኒ ብሌር ሥልክ ደዉለዉ ሥርዓታቸዉ ከተወገደ አካባቢዉን ፅንፈኞች እንደሚቆጣጠሩት አስጠንቅቀዉ ነበር።«እነሱ (ጂሐዲስቶች) ሜድትራኒያን ለመቆጣጠር እያደቡ ነዉ።» አሉ ቃዛፊ ይላል ዘጋርዲያን «ከዚያ አዉሮጳን ለማጥቃት ነዉ(ዕቅዳቸዉ» ቀጠሉ ሰዉዬዉ።ሥልጣን እንዲለቁ ከማሳሰብ ባለፍ ከብሌር ያገኙት ምክር አልነበረም።ቃዛፊ ሥልጣናቸዉን አይደለም ሕይወታቸዉንም አጡ።የቃዛፊና የሥርዓታቸዉ መጥፋት ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ያኔ እንዳሉት ለሊቢያ የሠለም፤ለዲሞክራሲ እና ለፍትሕ ጥሩ መሠረት የሚጥል ነዉ።«የቃዛፊ ሥርዓት ለአራት አስርታት በብረት ጡንቻ ሲገዛ ነበር።የሕዝቡ መሠረታዊ ሠብዓዊ መብቶች ተነፍገዋል።የዋሕ ሠላማዊ ሰዎች ታሥረዋል፤ ተደብድበዋል፤ ተገድለዋልም።የሊቢያ ሐብት ተዘርፏል።ሽብር እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አገልግሏል።የቃዛፊ ሥርዓት መወገዱን ዛሬ በርግጠኝነት መናገር እንችላለን።የሥርዓቱ የመጨረሻ ይዞታዎች ተማርከዋል።አዲሱ መንግሥት ሐገሪቱን መቆጣጠሩን እያጠናከረ ነዉ።ለረጅም ጊዜ ከገዙ የዓለም አምባገነኖች አንዱ ከእንግዲሕ የሉም።የጨቋኙ የጨለማ አገዛዝ ተወግዷል።የሊቢያ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ፤ሁሉን ያቻቸለችና እና ዴሞክራቲክ ከቃዛፊ አምባገነናዊነት ፍፁም ተቃራኒ የሆነች ሊቢያን የመገንባት ሐላፊነት አለበት።ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች ጋር በመሆን ለሊቢያ ሕዝብ የምሰጠዉን ድጋፍ ትቀጥላለች።»

NO FLASH Sarkozy und Cameron in Libyen
ምስል picture alliance/abaca

ኦባማ እንዳሉት የቃዛፊ አገዛዝ ጨቋኝ አምባገነን እንደነበር አያጠያይቅም።ይሁንና ከየካቲት 2011 እስካሁን በተቆጠረዉ ዓምስት ዓመት ሊቢያ ዉስጥ የተገደለ እና ከሊቢያ የተሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር አርባ ዓመት በዘለቀዉ የቃዛፊ አገዛዝ ከተገደለና ከተሰደደዉ በብዙ ቁጥር ይበልጣል።እስከ 2011 ሕዝቧን አቀማጥላ በማኖር አፍሪቃን የምትመራዉ የሊቢያ ዛሬ ምግብ፤ መድሐኒት፤ ዉሐና መብራት የሚናፈቅባት ሐገር ሆናለች።

ሠላም የለም።ከሁሉም በላይ ሽብር-ትርምስ የመዓልት ወሌት ምሷ ሆኗል።የሊቢያን ሕዝብ እንደሚረዱ ያኔ ቃል የገቡት ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ዛሬ ሊቢያን የነዳጅ ዘይት ጉርጓድ ጠባቂ ወታደር አለያም የሸማቂዎችን ምሽግ ደብዳቢ ጄቶ እያዘመቱ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች ባለፈዉ አርብ ሳብራታ በተባለችዉ የሊቢያ ሰሜናዊ ከተማ አጠገብ በጣሉት ቦምብ ብቻ ሐምሳ ሰዎች ገድለዋል።የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ጄቶቹ የደበደቡት እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት የተባለዉ አሸባሪ ቡድን ማሠልጠኛ መስክን ነዉ።ከተገደሉት ሰዎች ቢያንስ ሁለቱ ግን ታግተዉ የነበሩ የሠርቢያ ዲፕሎማቶች ናቸዉ።

ዓለም በሕግና ሥርዓት የምትመራ ቢሆን ኖሮ በአንድ ሐገርን ላይ ጦር የሚዘምተዉ የዚያች ሐገር መንግሥት ፍቃድና ይሁንታ ግድ ይላል።የአፍሪቃ ሕብረት በቅርቡ ወደ ቡሩንዲ ጦር ለማዝመት የነበረዉን ዕቅድ የሠረዘዉ የቡሩንዲ መንግስት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነዉ።ሊቢያ የሚፈቅድም፤ የሚከለክልም መንግሥት የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሊቢያ እንድትደበደብ አልወሰነም።ዓለም አቀፉ ድርጅትም ሆነ አባል መንግሥታቱ የድርጅቱን ሕግ ሊያስከብር ቀርቶ ሕጉ ሥለመጣሱም ያለዉ ነገር የለም።የዓለም አቀፉ ድርጅት ያሁን ትኩረት ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ኮብለር እንደሚሉት ግን ድርጅታቸዉ ያቺን ሐገር ከትርምስ ለማዉጣት እየጣረ ነዉ።

«አሁን (የሊቢያን) መንግሥትን ለመጠገን፤ቶብሩክና ትሬፖሊ ከሚገኙት መንግሥታት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት መመሥረት ነዉ።አዎ (ዓለም) ሐገሪቱን ዘንግቷታል።ደሞ በተቃራኒዉ አሁንም ብዙ አልዘገየም።ሊቢያን ከትርምሥና ከሥርዓተ ዓልበኝነት ለማዉጣትና ዳግም (ማዕከላዊ) አመራር እንዲኖራት በተቻለ አቅም ሁሉ እየጣርን ነዉ።ይሕን እያደረግን ሊቢያ ከችግር እንድትወጣ እያጀብናት ነዉ።»

የትሪፖሊና የቶብሩክ መንግሥታት ብሔራዊ መንግስት ለመመሥረት መስማማታቸዉ ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ተስምቶ ነበር።ወዲያዉ ግን ሥምምነቱን የየመንግሥታቱ ምክር ቤቶች አናፀድቅም ማለታቸዉ ተዘግቧል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብሔራዊ አንድነቱ መንግሥት መሪዎችና ሚንስትሮችን አስቀድሞ መርጦ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች እንዲቀበሉት ሥም ዝርዝራቸዉን ልኳል መባሉም ወትሮም ያልረገበዉን ጠብ ለማቀጣጠል ከጉርጓዷ እንደሚዛቀዉ ቤንዚን ነዉ-የሆነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ