1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶክተር አብይ ፈተና

እሑድ፣ መጋቢት 23 2010

ኢትዮጵያ ከንፁሕ የመጠጥ ዉኃ እጥረት እስከ ሥራ አጥነት--- ከጎሳ ግጭት እስከ ደን ጥፋት በርካታ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ፤ማሕበራዊ ችግሮች ሰቅዘዉ የያዝዋት፤ በሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ አድማ እና በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ሺዎች የተገደሉባት፤ ብዙ ሺዎች የታሰሩ፤ መቶ ሺዎች የሚሰደዱባት፤ የሚፈናቀሉባት ሐገር ናት

https://p.dw.com/p/2vGJ2
Abiye Ahmed in Addis Ababa
ምስል Reuters/Stinger

ውይይት፦ዶ/ር አብይ አሕመድ ለዉጥ ያመጡ ይሆን? 

በትክክል ባይረጋገጥም ከአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ባለሥልጣናት ወጣት ናቸዉ።41 ዓመታቸዉ።ዉልደት እድገታቸዉ ከቅይጥ ኃይማኖት ወላጆች፤ የተለያየ ኃይማኖት የሚከተል፤ የተለያየ ጎሳ አባላት ተሰባጥረዉ በሚኖሩባት ከተማ ነዉ። ኦሮሞ ናቸዉ።ትምሕርታቸዉም ኢንጂነሪግ፤ ኮምፒዉተር፤ የምስጠራ ሥልት (Cryptography)  አስተዳደር ብዙ ነገሮችን ያሰባጠረ ነዉ።ዶክተር አብይ አሕመድ።

ወታደር፤ የመረጃ ወይም ስለላ እና  የቴክኖሎጂ ሙያተኛ፤ ከሁሉም በላይ ፖለቲከኛ ናቸዉ።በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ፖለቲካ ዉስጥ ብቅ-ደመቅ ካሉበት ካለፈዉ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ወዲሕ «ለዉጥ አራማጅ» Reformist የሚል ቅፅል ከተሰጣቸዉ ጥቂት የገዢዉ ፓርቲ ሹማምታት አንዱ ናቸዉ።በቅርቡ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሊቀመንበር ሆነዉ ተመርጠዋል።ባለፈዉ ማክሰኞ ደግሞ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ሊቀመንበሩ አድርጎ መርጧቸዋል።

በግንባሩ የእስካሁን አሰራር እና በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር  ይሆናሉ።ከኦሮሞ ብሔር የጠቅላይ ሚንስትርነቱ ሥልጣን ሲይዝ ከአቶ ተስፋዬ ዲንቃ ወዲሕ ዶክተር አብይ የመጀመሪያዉ ፖለቲከኛ ይሆናሉ ማለት ነዉ።

ኢትዮጵያ ከንፁሕ የመጠጥ ዉኃ እጥረት እስከ ሥራ አጥነት፤ ከፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል እስከ የመናገር ነፃነት፤ ከመንቀሳቀስ መብት እስከ ዴሞክራሲ እጦት፤ ከጎሳ ግጭት እስከ ደን ጥፋት በርካታ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ፤ማሕበራዊ ችግሮች ሰቅዘዉ የያዝዋት፤ በሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ አድማ እና በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ሺዎች የተገደሉባት፤ ብዙ ሺዎች የታሰሩ፤ መቶ ሺዎች የሚሰደዱባት፤ የሚፈናቀሉባት ሐገር ናት።የመቶ ሚሊዮኖች ሐገር።ለብዙዎቹ ችግሮች መፈጠር ወይም መባባስ ብዙዎች  በሥልጣን ላይ ያለዉን ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ዶክተር አብይም የኢሕአዴግን አላማ የተቀበሉ፤ ከወታደርነት እስከ ዶክተርነት ኢሕአዴግ ያሰለጠነ፤ ያስተማራቸዉ፤ የሾመ የሸለማቸዉ፤  አሁንም ኢሕአዴግ ለመሪነት የመረጣቸዉ ፖለቲከኛ ናቸዉ።ግን ቀደም ሲል እንዳልነዉ ለዉጥ አራማጅ የሚል ቅፅል ተስጥቷቸዉ ተስፋም ተጥሎባቸዋል።ለዉጥ ያመጡ ይሆን? 

ነጋሽ መሐመድ