1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዦን ፒየር ቤምባ ነፃ መባላቸው እና አንደምታው

ቅዳሜ፣ ሰኔ 9 2010

የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት፣ በምህፃሩ አይሲሲ በሰው ልጅ ላይ ፈጽመውታል በተባለ ወንጀል እና በጦር ወንጀል በእስራት የቀጣቸው የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ዦን ፒየር ቤምባ ነፃ ብሏቸዋል።

https://p.dw.com/p/2ze8q
Demokratische Republik Kongo Anhänger Jean-Pierre Bemba
ምስል Getty Images/AFP/J. Wessels

ዦን ፒየር ቤምባና የአይሲሲ ውሳኔ

የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ የተባለው የሚሊሺያ ቡድን በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የግድያና አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎችን በሰላማዊው ህዝብ ላይ ፈጽሟል በሚል ነበር ፍርድ ቤቱ ከጎርጎሪዮሳዊው 2008 ዓም ወዲህ በእስራት በቆዩት የ55 ዓመቱ ቤምባ ላይ በ2016 ዓም የ18 ዓመት እስራት የበየነው። ይሁንና፣ የሚሊሺያው ቡድን ታጣቂዎች ለፈጸሙት ወንጀል ቤምባን በኃላፊነት ማስጠየቅ የሚያስችል ማስረጃ የለም በሚል ቅጣቱን በመቃወም የቀረበውን የይግባኝ ማመልከቻ የመረመሩት ዳኞች  ብይኑን ሽረዋል። ሆኖም፣ በችሎቱ ወቅት የምስክሮችን ቃል ለማስቀየር ሞክረዋል በሚል የቀረበባቸው ሌላ ክስ ከሶስት ሳምንታት በኋላ በፍርድ ቤቱ በሚታይበት ጊዜ እስከ አምስት ዓመት እስራት እና የገንዘብ መቀጫ ሊበየንባቸው እንደሚችል የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።አሁን ነፃ ተብለው ከእስር የወጡት ቤምባ ጉዳያቸው በሚቀጥለው ጎርጎሪዮሳዊው ሀምሌ ወር መጀመሪያ እንደገና እስኪታይ ድረስ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዳኞች የቀረቡላቸውን  ጠንካራ መመሪያዎች መከተል እንዳለባቸው፣ ለምሳሌ፣ ከምስክሮች ጋር እንዳይገናኙ እና ስለ ችሎቱም እንዳይናገሩ ያሳስባል።

Niederlande Den Haag International Criminal Court
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. van Lonhuijsen

የቤምባ ነፃ መባል በኮንጎ እና በውጭ ባሉ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ደስታ ፈጥሯል። ይሁን እንጂ፣ የቤምባ ሚሊሹያ ቡድን ወንጀል ሰለቦች በአይሲሲ ውሳኔ እጅግ ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል። ወንድማቸው የተገደለባቸው ኤሪክ ያማዛምባ ውሳኔውን አሳዛኝ ብለውታል።

«የቤምባ ከእስር መለቀቅ ለኔ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። በጣም ልብ ሰባሪ ነው። ትልቅ ጉዳት ነው። ቤምባ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል፣ ገድለዋል፣ ዘርፈውናልም። እነዚህ ወንጀሎች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ ለብዙ አሰርተ ዓመታት ተካሂደዋል። አሁንም ገና እየተሰቃየን ነው። የቤምባ ነጻ መውጣት ለኛ ውርደት ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አዋርዶናል። ከዓለም አቀፉ ፍትሕ ይህን አልጠበቅንም ነበር።  አሳዝኖናል።»

ወሲባዊ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረት ያገኘው በቤምባ ላይ ክስ በቀረበበት ጊዜ ሲሆን፣ አይሲሲ ከተቋቋመ ከጎርጎሪዮሳዊው 2002 ዓም አንስቶ እስከዛሬ የወንጀል ክሳቸው ከታየባቸው አራት ግለሰቦች መካከል ቤምባ ከፍተኛው ባለስልጣን ነበሩ። 

በዚህም የተነሳ ፍትሕ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገው የነበሩት ልጃቸው በቤምባ ሚሊዩያ የተደፈረችባቸው አባት ዦን ኩኢቢን  እና  የቤንባ ሚሊሺያ ሰለባ ኤትየን ኩምባ የመሳሰሉ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሰለባዎች በሰሞኑ የአይሲሲ ውሳኔ ችላ እንደተባሉ እንደተሰማቸው ነው በቅሬታ ለዶይቸ ቬለ የገለጹት። 

« ልጄ ክብሯ ተደፍሯል። ከኔ ጋር ለማምለጥ ሞክራ ነበር፣ ግን የቤምባ ሚሊሺያዎች በኃይል ወሰደው ክብሯን ደፈሯት። ይህ ድርጊታቸው በጣም ነው የዘገነነኝ። በጎረቤቶቼ ላይ የተፈጸሙ ሌሎች ብዙ ወንጀሎች መዘርዘር እችላለሁ። » «በቤምባ ላይ ተበይኖ የነበረው ቅጣት መጨመር ነበረበት ብለን እናስባለን። ዕድሜ ልካቸውን በወህኒ መቆየት ነበረባቸው። በመፈታታቸው በጣም ነው የተገረምነው። እንደ ሰለቦች በጣም ቅር ተሰኝተናል። በዓለም አቀፉ ወንጀለኛ ተመልካች ፍርድ ቤት ውሳኔ ተበሳጭተናል። ስሜታችን ይህን ይመስላል። » ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የዓ/አቀፍ ፍትሕ ቡድን ኃላፊ ሰለሞን ሳኮ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የ2002/2003 ዓም በቤምባ ሚሊሺያ ቡድን ብዙ በደል እና መከራ የደረሰባቸው ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው በአይሲሲ ውሳኔ ቅር መሰኘታቸውን እንደሚረዱት በማስታወቅ፣ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ማን መጠየቅ እንዳለበት ተመርምሮ ተጠያቂዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳስበዋል። 

Internationaler Strafgerichtshof Jean-Pierre Bemba
ምስል picture-alliance/dpa/J. Lampen

«  ይህ ውሳኔ ለማዕከላዕ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሰለቦች ፍትሕ ለማስገኘት የተጀመረው ሙከራ መጨረሻ ሊሆን አይችልም፣ አይሆንምም።  በዚችው ሀገር ምርመራ ሊደረግ እና ክስ ሊመሰረት ይገባል። እኛም የአይሲሲ ዓቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤትን ምርመራዎቹን እንዲቀጥል እና ለተፈጸሙት ዘግናኝ ወንጀሎች በኃላፊነት የሚጠየቁትንም ለፍርድ እንዲያቀርብ መጠየቃችንን እንቀጥላለን። »

የዦን ፒየር ቤምባ ነፃ ያለበት ውሳኔ የቀድሞው የጦር ባለቤት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሊመለሱ ይችሉ ይሆናል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል። የቤምባ መመለስ፣ ከተመለሱ ፣  በወቅቱ የሀገሪቱ ፖለቲካ መድረክ ላይ በሚታየው ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይታመናል። የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣  ቤምባ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ እና የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላም ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው። እንደሚታወሰው፣ ቤምባ ካቢላ ድል ላደረጉበት የ2006 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሁለተኛ ዙር ደርሰው ነበር።  

የቤምባ ደጋፊዎች የቀድሞው  የሚሊሺያ ቡድን መሪ እንደገና ወደ ሀገሪቱ ፖለቲካ መድረክ እንዲመለሱ እንደሚፈልጉ የኮንጎ ነፃነት ንቅናቄ የተባለው የቤምባ ተቃዋሚ ፓርቲ ምክትል ዋና ጸሀፊ ፊዴል ባባላ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። « ይህ ማድረግ ግዴታቸው እና እጣቸው ነው። የኛ ምኞት ጀምረውት የነበረውን ስራ ከተቋረጠበት እንዲቀጥሉ ነው። »

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የፊታችን ታህሳስ 23፣ 2018 ዓም አዲስ ፕሬዚደንት ለመምረጥ እቅድ ተይዟል። ዦን ፒየር ቤምባ ነፃ በተባሉበት ዕለት የኮንጎ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የሀገሪቱ  ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሰረት ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንደማይወዳደሩ ጠቅላይ ሚንስትር ብሩኖ ሺባላ ተናግረዋል። ካቢላ አሁን ከፕሬዚደንታዊው ውድድር ራሳቸውን ማራቃቸው ዋነኖቹ የተቃዋሚ ቡድኖች፣ ማለትም፣ በኮንጎ የትልቁ ተቃዋሚ ቡድን፣ የዴሞክራሲ እና ማህበራዊ መሻሻል ህብረት መሪ ፌሊክስ ቺሴኬዲ እና የመልሶ ግንባታ እና የዴሞክራሲ የህዝብ ፓርቲ መሪ ሞይስ ካቱምቢ  ተፎካካሪዎቻቸው የወደፊቱን አካሄዳቸው በጥሞና እንዲያጤኑት ሳያደርጋቸው እንደማይቀር ታዛቢዎች ይገምታሉ። ካቱምቢ ተቃዋሚዎች በጋራ አንድ እጩ ይቅረብ የሚለውን ሀሳብ ነው ሲያራምዱ የቆዩት፣ አሁን ቤምባ ወደ ብሔራዊ ፖለቲካ ከገቡ ግን ይህ ሀሳባቸው እውን መሆኑ አጠያያቂ ነው።

Ruanda Kigali - Moise Katumbi Chapwe bei der Mo Ibrahim Award
ሞይስ ካቱምቢምስል DW/E. Topona

አሁንም በትውልድ ሀገራቸው ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ቤምባ  በምርጫ ቢወዳደሩ በመጀመሪያ ዙር ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ካቢላ በቀጣዩ ምርጫ እንደማይቀርቡ ከማስታወቃቸው በፊት የተካሄዱ የሕዝብ አስተያየት መለኪያ መመዘኛ መዘርዝሮች አሳይተዋል። የምርጫው ሂደት ቤምባ ወደፊት በሚወስዷቸው ርምጃዎች ላይ ጥገኛ እንደሚሆኑ በፈረንሳይ የናንሲ ዩኒቨርሲቲ የፓንአፍሪካን ጂዮፖሊቲክስ ተቋም ዳይሬክተር ምዋይላ ሺየምቤ ያስባሉ።

« ቤምባ ወደ ሀገር ከተመለሱ  አንድም የተቃዋሚውን ቡድን ፕሬዚደንቱን ጠንክሮ መፎካከር ይችል ዘንድ አንድ ለማድረግ የሚረዳ ብልህ መሪ መሆን አለባቸው፣ እኔ እበልጣለሁ የሚል ዓይነት አስተሳሰብ ይዘው ከተመለሱ ግን የተቃዋሚዎች ድምፅ ከማዳከም ከማድረግ ጎን አንድነትን የማይፈልጉትን ወገኖች ይበልጥ ወደ አክራሪነት ሊገፋፉ ይችላሉ። »

እንደ ሺየምቤ አስተያየት ይህ የካቢላን እና የገዢውን ፓርቲ የሚጠቅም ይሆናል። የኮንጎ መንግሥት ቤምባ ነፃ መባላቸውን መልካም ብሎ፣ ከፈለጉ ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንደ ነፃ ግለሰብ ሊመለሱ እንደሚችሉ ዋስትና መስጠቱን የአስር ዓመቱ የወህኒ ቤት ቆይታቸው ትምህርት ሰጥቷቸው ይሆናል ያሉት ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላን የሚደግፉ ብዙ ፓርቲዎች የተጠቃለሉበት ህብረት ምክትል ዋና ጸሀፊ ጆሴፍ ኮኮንያንጊ ተናግረዋል።  

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ