1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ንብ የማንባቱ ፕሮጀክት ደንን የሚጠብቅ ነዉ፤

ማክሰኞ፣ ኅዳር 19 2010

ዘላቂነት የሌለዉ የግብርና ስልት ለተፈጥሮ አካባቢ እና ለስነምህዳር አስጊ እንደሚሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2050ዓ,ም የዓለም ሕዝብ 9 ቢሊየን ይደርሳል ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለዉጥ ለሰዉ ልጆች ብቻ ሳይሆን ሕይወት ያለዉን ፍጥረት ሁሉ ከሚያሳስብ የችግር አፋፍ እንዳደረሰዉም ያሳስባሉ።

https://p.dw.com/p/2oOgd
Deutschland Bonn - Solution Search Farming for Biodiversity Preisträger Jonny Girma Beekeeper aus Äthiopien
ምስል Shewaye Legesse

ጆኒ ግርማ ከጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዶክተር ኤልሳ ኒከል ሽልማቱን ሲቀበል፤

ስጋቱን ለመቀነስ ታዲያ ስነምህድርን ለጉዳት የማያጋልጥ የግብርና ስልት የሚያፈላልግ  ዓለም አቀፍ ዉድድር ተካሂዷል። መቀመጫዊዉን እዚህ ጀርመን ሀገር ቦን ከተማ ያደረገ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ስነምህዳርን ከጉዳት የሚጠብቁ  የግብርና መፍትሄዎችን ከመላዉ ዓለም ሲያፈላልግ መክረሙን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ IFOAM የተሰኘዉ ይህ ድርጅት ኅብረተሰቡ በየአካባቢዉ በልማድ ከሚጠቀምበት የግብርና ስልት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተለያዩ ሃገራት ባሉት አጋሮቹ አማካኝነት ይንቀሳቀሳል። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2017 በዓለም አቀፍ ደረጃ ባካሄደዉ ሶልዩሽን ሰርች በተሰኘዉ ዉድድር ከመላዉ ዓለም 338 ፕሮጀክቶች ተሳትፈዋል። ፕሮጀክቶቹ የየአካባቢዉን ኅብረተሰብ ባህላዊ ስልት ተጠቅመዉ በተለያዩ ምክንያቶች ከጥቅም ዉጭ የሆኑ አካባቢዎች አገግመዉ ዳግም ፍሬያማ እንዲሆኑ ያስቻሉ፤ የተራቆተ አካባቢ ደን እንዲለብስ ያደረጉ እንዲሁም በዘመናዊ የንብ ማንባት ስልትም ለበርካቶች የሥራ ዕድልን የፈጠሩም ይገኙበታል። ከእነዚህ መካከል ታዲያ 10 ብቻ ናቸዉ ለሽልማት የተመረጡት። ከአስሩም ስድስቱ የገንዘብ እና ለዚሁ ሲባል የተዘጋጀ ሽልማትን አግኝተዋል።

ለሽልማት ከበቁት መካከል በንብ ማንባት ሥራ ወጣቶች ተሰማርተዉ የአካባቢያቸዉን ደን እየጠበቁ ማር በማምረት ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ያበቃ ኢትዮጵያዊ አንዱ ነዉ። የአፒስ አግሪቢዝነስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጆኒ ግርማ ከኬሚካል የፀዳ ማለትም ኦርጋኒክ ማር በማምረት በሚያደርገዉ አስተዋፅኦ የብዙዎችን ድምጽ በኢንተርኔት ማለትም ኦንላይን በማግኘት ነዉ የዚህ ዉድድር አሸናፊ የሆነዉ።

Deutschland Bonn - Solution Search Farming for Biodiversity Preisträger Jonny Girma Beekeeper aus Äthiopien
በዉድድሩ ከተሳተፉት ለሽልማት የበቁት አስር ፕሮጀክቶች ምስል Shewaye Legesse

በነገራችን ላይ እዚህ ጀርመን ሀገር የንቦች ሕልዉና አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዉ ጀምሯል። በዚሁ ምክንያትም ጀርመን ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም አንስቶ ለንቦች ጠንቅ የሆኑ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ አግዳለች። የደኑ ይዞታ ከዕለት ወደ ዕለት እያሳሰበ ቢሄድም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘዉ የተሻለ የደን ሀብት ታግዞ ነዉ የኢትዮጵያዊዉ የንብ ማንባት ሥራ የተስፋፋዉ። ተሸላሚዉ ጆኒ ግርማ ቦን ከተማ ላይ በተካሄደዉ የሽልማት ሥርዓት ላይ ባደረገዉ ንግግር «ዛፍ ከሌለ ንብ የለም፤ ንብ ከሌለ ማር የለም፤ ማር ከሌለ ደግሞ ገንዘብ የለም» በማለት ንቧን እና ማሯን የሚፈልግ ደንን መከባከብ እንዳይረሳ ሲያሳስብ የታዳሚዎቹን ቀልብ ገዝቷል።

ጂኒ ግርማ የመጀመሪያ ዲግሪዉን በጠቅላላ ግብርና ላይ ከሠራ በኋላ በሆለታ የምርምር ማዕከል ንብ ላይ በሚመራመረዉ ዘርፍ አግልግሏል፤ ማር ላይ በሚሠራ የግል ድርጅት ዉስጥም ሠርቷል። ከዚህም ሌላ  ሁለት የድህረ ምረቃ ዲግሪዎች ከኔዘርላንስዱ ዋግን ንገን ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። አንደኛዉ ጥናቱ ያተኮረዉ ታዲያ ኦርጋኒክ ግብርና ላይ ነዉ። ለዓለም አቀፍ እዉቅና ያበቃዉ ስነምህዳርን የሚንከባከበዉ ፕሮጀክቱም ኦርጋኒክ ማለትም ከኬሚካል የፀዳ ማር አምራች ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ