1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንታዊትዋና ዘመናዊትዋ አስመራ በዓለሙ የቅርስ መዝገብ  

ዓርብ፣ ሐምሌ 7 2009

አስመራ ግብፆች፤ ቱርኮች፤ጣልያኖች እንጊሊዞች ተዋግተዉባታል። ከተማዋን የጎዳ ማንም ኃይል ግን አልነበረም። ከአስመራ ውብ ኪነ-ሕንፃዎች መካከል ሲኒማ ኤንፔሮ፤ ሲኒማ ዳንቴ፤ ሲኒማ ካፒቶል፤ ሲኒማ ሮማ፤ ሲኒማ ኦዲዎን የሚባሉ ሲኒማ ቤቶች ይገኛሉ። ኢጣልያዉያኑ ወደ ኤርትራ የገቡት በጎርጎረሳዉያኑ  1889 / በ 1890 ዓ.ም ነበር።

https://p.dw.com/p/2gV7d
Eine afrikanische Insel der Architektur
በአስመራ የሚገኘዉ የካቶሊክ ካቴድራል ሕንጻምስል DW/Y.Tegenewerk

MMT _Kultur_ Asmara_Eine afrikanische Insel der Architektur_UNESCO - MP3-Stereo

«አስመራ በጣም ዉብ የሆነች ከተማ ናት። ከሁሉ ደግሞ ሕዝብዋ በዉስጥዋ እየኖረ ባህሉን እየጠበቀ ሥነ ሕንጻዉን እየጠበቀ በመሆኑ ነዉ። የአስመራ ሕንጻዎች ለየት ያለ ንድፍና ቅርስ የያዙ ናቸዉ።  ጣልያኖቹ በቅኝ ግዛት ወቅት ሃገራቸዉ ዉስጥ የሌለ ነጻነት አስመራ ዉስጥ፤ ቅኝ ሃገር ዉስጥ ነጻነት ተሰምቶአቸዉ ፤ በምህንድስናዉ ረገድ አብዮት ያካሄዱ ይመስላል። ምክንያቱም ኢጣልያ ዉስጥ የማይገኘዉ ሕንጻ አስመራ ዉስጥ አለ።»  

Eine afrikanische Insel der Architektur
በአስመራ የሚገኘዉ የካቶሊክ ካቴድራል ሕንጻምስል DW/Y.Tegenewerk

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት አስመራ የዓለም ቅርስ ሆና እንድትመዘገብ በፖላንድ ዋርሶ ባካሔደው ጉባዔ ላይ ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ መወሰኑን ተከትሎ በአስመራ የኤርትራ ብሔራዊ ሙዝየም ጀነራል ዮሴፍ ልብሰቃል ከሰጡን አስተያየት የወሰድነዉን ነበር ያደመጥነዉ። «ፒኮሎ ሮማ ትንሽዋ ሮም» አልያም «አፍሪካስ ማያሚ» ሲሉ የሚያንቆላጽስዋት የኤርትራ መዲና አስመራ፤ በኢጣልያ ቅን ግዛት ሥር በነበረችበት ወቅት ልዩ ጥበብና ክህሎት በሚታይባቸዉ በኢጣልያ የሥነ- ሕንፃ ግንባታ ባለሞያዎች በተሰሩት የተለያዩ ሕንፃዎች መንገዶች መሆኑም ተመልክቶአል። በእለቱ ዝግጅታችን የአስመራ ከተማ በመንግሥታቱ የቅርስ መዝገብ መካተትዋን በተመለከተ የተሰጠ አስተያየትና በዓለሙ ቅርስ መስዝገብ እንድትካተት ጥረት ያደረጉትን አነጋግረናል።

ከጎርጎረሳዉያኑ 1890 እስከ  ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ማብቅያ ማለትም እስከ 1941ዓ.ም በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት የነበረችዉ ኤርትራ ኢጣልያዉያን የሥነ ሕንፃ ባለሞያዎች ያለምንም ችግርና እገዳ  ኤርትራ በተለይም አስመራ ዉስጥ ግሩም ሕንፃዎችን እንደገነቡ ተነግሮአል። በፈረንሳይ የኤርትራ አምባሳደር እና የበዩኔስኮ የሀገሪቱ ቋሚ ተጠሪ ሐና ስምዖን ውሳኔው ከዓመታት ጥረት በኋላ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል። አምባሳደሯ ውሳኔው "የኤርትራውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ብሎም የመላው ዓለም ድል ነው" ሲሉ የገለፁት። አምባሳደር ሐና ስምዖን፤ ይህን ጌዜ ስንጠባበቀዉ ነበር ሲሉም ነዉ የተናገሩት

Eine afrikanische Insel der Architektur
የአስመራ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስትያን ምስል DW/Y.Tegenewerk

«ስንጠባበቀዉ የነበረዉ ጉዳይ ስኬታማ ሆነ። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ታሪካዊ ቅርሶችን የሚያጠናና እና ሪፖርት የሚያቀርብ ንዑስ ክፍል አለ። ኢኮሞስ ይባላል። ሌሎችም የተዋቀሩ ንዑስ ክፍሎች አሉ። ኢኮሞስ የመረጠዉ ሰዉ ኤርትራ ሄዶ ታሪካዊ የተባሉ ቅርሶችን ገመገመ።  ይህ ልዑክ የአስመራ ታሪካዊ ቅርሶችን በተመለከተ የቀረቡትን ጥናቶችና ሪፖርቶች በማገናዘብ ያጠናቀረዉን መሰረት በማድረግ በቀጣይ ሪፖርት አቀረበ። በአስመራ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን «አርት ዴኮ» በሚል ስያሜ የሚታወቁ ሕንጻዎችን በተመለከተ የቀረበዉ ዘገባ እጅግ ጥሩ ነበር። ኤርትራ ሕያዉ በሆኑ ቅርሶች በዓለም የቅርስ መዝገብ እንድትሰፍር ወስኖአል።»  

አምባሳደርዋ እንደገለፁት በአስመራ ከተማ ስዕል የተዋቡት ሕንጻዎች በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት  የተጀመረዉ  ከዓመታት በፊት ነዉ። በአስመራ በሚገኘዉ የኤርትራ ብሔራዊ ሙዝየምጀነራል  ዳይሬክተር ዮሴፍ ልብሰቃል በኤርትራ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጥናት ያደርጋሉ። በአስመራ የሚገኙ ሥነ ሕንጻዎች በዓለሙ መዝገብ ስር እንዲካተት ጥረት ካደረጉ ምሁራኖች መካከልም አንዱ ናቸዉ።

Kandidaten neue UNESCO-Welterbestätten | Eritrea Asmara
ጋራዥን አጣምሮ የያዘው «ፊያታ ሌሮ» የነዳጅ ማደያ በአስመራምስል picture alliance/robertharding/M. Runkel

« አስመራን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመረዉ ጥረት በጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓ.ም በአፍሪቃ ኅብረት አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተካሄደዉ  ስብሰባ አፍሪቃዉያን ሃገራት ስላላቸዉ የጥንታዊ ቅርስ ጉዳይ የሚነጋገሩበት ነበር። በዝያን ጊዜ የኤርትራ ብሔራዊ ሙዝየም የዓለምን ተመራማሪዎች ቀልብ ለመማረክ በኤርትራ ብቃት አላቸዉ ብሎ የገመተዉን ታሪካዊ ቦታዎች በዝያን ግዜ አጭቶ አስመዝግቦ ነበር። አምስት ቦታዎች እንደ ቆሃይቶ ፤ አዶሊስ ፤ ናቅፋን የመሳሰሉ ቦታዎች ታጭተዉ ነበር። በዝያን ጊዜ የጀመረ ስራ ነዉ ዛሬ አስመራ በዩኔስኮ ለመመዝገብ የበቃዉ» 

በጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓ,ም አዲስ አበባ ላይ የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ ሲካሄድ በዓለሙ የቅርስ መዝገብ በአፍሪቃ ሃገራት የሚገኘዉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርስ የተመዘገበዉ ጥቂት ነዉ በሚል በተደረገዉ ጥሪ ኤርትራም ተሳትፎ መጀመርዋን ዶክተር ዬሴፍ ተናግረዋል።

Eine afrikanische Insel der Architektur
ምስል DW/Y.Tegenewerk

« የ1996 ዓ,ም በነበረዉ ስብሰባ ላይ በዩኔስኮ ስለሚታየዉ ያልተመጣጠነ ምዝገባ ተነግሮ ነበር። ለምሳሌu ከአዉሮጳ ሃገር ብዙዎቹ ተመዝግበዉ ፤ ከአፍሪቃ ግን በጣም ጥቂት ቦታ ተመዝግበዉ በመኖራቸዉ ያንን ያልተመጣጠነ አሰራር እና አመራረጥ ለመቀየር የተደረገ የመጀመርያ ጥረት ነበር። ከዝያ ጊዜ በኋላ ብዙ የአፍሪቃ ቅርሶች በድርጅቱ መዝገብ ተመዝግበዋል፤ ዩኔስኮ  አሁን በኤርትራ አስመራ የሚገኘዉ ጥንታዊዉ ዘመናዊ ሕንጻን ማካተትዋ በጣም አስፈላጊ አዲስና ልዩ ምዕራፍ ነዉ ብለን ነበር የምንጠራዉ።»  

በኤርትራ ቆሃይቶ አዶሊስን ጨምሮ አምስት ከተሞች በጥንታዊ ቅርስነታቸዉ እንዲመዘገቡ ጥረት መደረጉን የገለፁት ዶክተር ዬሴፍ ልብሰቃል በመቀጠል።

 « ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያለዉ አዶሊስ በዝያን ጊዜ ከነበሩ ከታወቁ የተለያዩ ሃገሮች ጋር ትልቅ የንግድ ግንኙነት የነበረዉ፤ አዶላዉያን  በዝያን ጊዜ እስከ ሕንድ አልፈዉ እስከ ቻይና ግንኙነት ያደርጉባት የነበረዉ የወደብ ከተማ ናት። ሌላዉ ሰፊ ከተማ የነበረችዉ ቆሃይቶ እስከ 17 ኪሎሜትር ስፋት የነበራት ትልቅ የአፍሪቃ ከተማ ነበረች። ቆሃይቶ የዝሆን ጥርስ የሚካሄድባት የነበረች ከአክሱም ጋር ግንኙነት የነበራት ከተማ ናት። ሌላዉ መጠራ በለዉ ከለዉ የሚባለዉ ከተማ ከ 2000 ዓመት በላይ ስልጣኔ የነበረዉ ታሪካዉ ከተማ ነዉ። በዚህ ከተማ የመጠራ ሃዉልት የሚባል የታወቀ ጥንታዊ ኃዉልት ይገኛል። በሃዉልቱ ላይ አናባቢ የሌለዉ የግዕዝ ጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል ። ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ በአፍሪቃዉ ቀንድ ላይ ለሚገኙ ሁለቱም ሃገሮች የሥነ-ጽሑፍ የተከሰተበት ታሪካዊ ቦታ ነዉ። ዳህላክኬሪስ ሰፊ ሰፊ የሆነ የእስልምና እምነት የሚታይባት ስለነበረች በአፍሪቃ እስልምናን ከተቀበሉት አካባቢዎች የመጀመርያዉ ቡታ ነዉ ። በዚህ ቦታ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች ይገኛሉ ለምሳሌ ጥንታዊ መቃብሮች ጥንታዊ የዉኃ ማጠራቀምያ ገንዳዎች ይገኙበታል ። ዳሪሰላም ወይም የእስላም ማዕከል ተብላ ትጠራ የነበረች ትልቅና ጥንታዊ የእስልምና ታሪክ የሚገኝባት ቦታ ናት። ሌላዉ ናቅፋ የቅርብ ጊዜ የትግል ታሪክን ያቀፈ ታሪካዊ ቦታ ነዉ። »          

Italiienisches art deco Geschäftsgebäude  in Asmara
በአስመራ የሚገኘዉ የንግድ ሕንጻምስል picture alliance/robertharding

ኤርትራዊዉ የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን ለረጅም ዓመታት በአስመራ ከተማ ነዋሪ ነበር ። አስመራ  በተለይ በኢጣልያ ቅኝ ግዛት ዘመን ማደግዋን በመግለጽ ስለአስመራ ከተማ ታሪክ እንዲህ ሲል ነግሮናል።  

« በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ከተማ የሆነችዉን አስመራን በምናባችን ስናስብ የኤጣልያ ቅን ገዥዎች ፤ በዘመናዊ መልክ ተቆርቁራ ያደገች የተመነደገች መሆንዋን እንገነጠባለን አስመራ የተቆረቆረችዉ እንደሰንሰለት ከተሳሰሩት ተራሮች አናት ላይ ነዉ። የአየር ንብረትዋ ደጋማ ነዉ። እንግዲህ መጀመርያ አስመራ ስትቆረቆር አራት መንደሮች ነበሩ። በነዚህ መንደሮች ወረበሎች ሰርገዉ በመግባት ጥቃት ይፈጽሙ  ስለነበር አራቱም መንደሮች ግንባር ፈጥረዉ እንዲከላከሉ ስለተመከሩ ጠላቶቻቸዉን በጋራ መመከት ቻሉ። እነዚህ መንደሮች በጋራ ለከተማዋ «አርበአተ አስመራ» ሲሉ መጠርያ ሰጡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አርበአተ የሚለዉ ጠፋና አስመራ ከተማ ተባለች። በከተማዋ የሚገኙት ሕንጻዎች በጎርጎረሳዉያኑ 1930ዎቹ ጀምሮ የተሰሩ ናቸዉ። በዝያን ጊዜ በቅኝ ግዛት ኤርትራን የያዘዉ ኢጣልያዊዉ ፋሺስት ሞሶሎኒ በምስራቅ አፍሪቃ ለሚያካሂደዉ የቅኝ ግዛት ዘመቻ ማዕከል እና መነሻ እንድትሆነዉ ዓይኑን ያሳረፈዉ ኤርትራ ላይ ነበር። «ኢጣልያዉያኑ ወደ ኤርትራ የገቡት በጎርጎረሳዉያኑ 1889 / በ 1890 ነበር። በዝያን ጊዜ ፋሺስት ሞሶሎኒ ጣልያኖች ወደ ኤርትራ እየሄዱ መዋዕለ ንዋይ እንድያፈሱ አስመራን እንዲይዙ ይገፋፋ ስለነበር፤ በዝያን ወቅት በአስመራ ዉስጥ ከ 20 ሺህ እስከ 65 ሺህ ጣልያኖች ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። ኢጣልያዉያን የሥነ-ሕንጻ ባለሞያዎች አስመራ ዉስጥ እንደልብ ሕንጻን ይገነቡ ነበር። ይህን ግንባታ ሲያካሂዱ ለራሳቸዉ መኖርያ ለራሳቸዉ መስርያ ቤት ለራሳቸዉ ትያትር ቤትና ፀሎት ቤት ነበር። ይህን ለኤርትራዉያን ብለዉ አለገነቡም። ፋሽስት ሞሶሎኒም በዝያን ጊዜ አስመራን አፍሪቃዊትዋ ትንሽዋ የሮም ከተማ ሲል አንቆለጳጰሳት። የአስመራ ሰዎች እንደሚሉት በጣልያንኛ ፒኮሊ ሮማ ትንሽዋ የሮም ከተማ እንደማለት ነዉ። ፋሽስት ሞሶሎኒ በጎርጎረሳዉያኑ 1930ዎቹ ምስራቅ አፍሪቃን በቅኝ ለመያዝ ታላቅ ሴራ ላይ በነበረበት ወቅት አስመራ ላይ ያሰራቸዉ ሕንጻ ዉበቶች ዘመን የማይሽራቸዉ የዉበት መስብ ያላቸዉ መሆኑን በርካታ የዓለም ምሁራን ገልፀዋል። በኤርትራ አስመራ ከተማ የሚገኙት ከ 50 በላይ የሚሆኑት እነዚህ ሕንጻዎች አሁን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«ዩኔስኮ» ተመዝግበዋል»    

Eine afrikanische Insel der Architektur
በአስመራ የሚገኘዉ መስጂድ ምስል DW/Y.Tegenewerk

ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን በአስመራ ልብ ከሚያማልሉት ሕንጻዎች መካከል አለ በመቀጠል ፤« ግሩም ከሚባሉት ልብ ከሚያማልሉት ሕንጻዎች መካከል «ፊያታ ሌሮ» አንዱ ነዉ «ፊያታ ሌሮ » ነዳጅ ማደያ ነዉ፤ ጋራዥም አለዉ፤ በአዉሮፕላን ቅርፅ ነዉ የተሰራዉ። የቀኝና የግራ ክንፉ 30 ሜትር ይረዝማል፤ የፓይለት መቀመጫ የሚመስል ቢሮም አለዉ። ስለዚህ ይህ ድንቅ የሆነ ሕንጻ ነዉ። ሲኒማ ቤቶቹ ራሳቸዉ ድንቅ ናቸዉ ሲኒማ ኤንፔሮ፤ ሲኒማ ዳንቴ፤ ሲኒማ ካፒቶል፤ ሲኒማ ሮማ፤ ሲኒማ ኦዲዎን የሚባሉ ሲኒማ ቤቶች አሉ።ሁሉም ሲኒማ ቤቶች የተሰሩት በአዉሮጳ ደረጃ ነዉ። ሌሎቹ ሕንጻዎች ቡናማ ሰማያዊ አረንጓዴ ቀለም ያላቸዉ ናቸዉ። የአስመራ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስትያን ዉብ ቪላ ቤቶች ፤ ፋብሪካዎች አስመራ የሚገኘዉ ትልቁ መስጊድ የመሳሰሉት ሁሉ የሚያማልሉ  ናቸዉ። ከዝያ በተጨማሪ ከተማዋ እድለኛ ። 30 እና 40 ዓመት ጦርነት ተካሂዶ ከተማዋ ምንም አልተጎዳችም ከተማዋን የጎዳ ኃይል የለም። በመጀመርያ ከተማ አስመራን በኦቶማን ኤምፓየር በሚባለዉ ዘመን ቱርኩች ያዙ፤ ከዝያ በኋላ ግብጾች ያዙ ከዝያ በኋላ ጣልያኖች ያዙ ከዝያ በኋላ እንጊሊዞች ያዙ። ይህ ሁሉ ትርምስ ሲካሄድ ግን ከተማዋ አልተጎዳችም፤ እግዜርም ይጠብቃታል ማለት ነዉ።»      

Eine afrikanische Insel der Architektur
በአስመራ የሚገኘዉ ዋናዉ ፖስታ ቤት ምስል DW/Y.Tegenewerk

በአስመራ የሚገኙትና ቅኝ ግዛቱ ዘመን የተሰሩት ከ 50 በላይ ሕንፃዎች በሙሉ በዓለሙ መንግሥታት የቅርስ መዝገብ በመስፈራቸዉ ኤርትራ ጥንታዊና የባህል ቅሪቶች በሙሉ የተመዘገበላት ቀዳሚዋ የዓለም ሃገራት እንዳደረጋት ተገልፆአል። በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ የአስመራ ከተማ በቅርስ መዝገብ መካተት ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ኩራት ነዉ ብለዋል።    

«የአስመራ ከተማ በዓለም የቅርስ መዝገብ መካተት ለኛ ለሁላችንም ፤ ለሰዉ ልጆች በተለይም ለአፍሪቃ በዘመናዊነት ፤ ከ 19ኛዉ ክፍለ ዘመን ወዲህ ቅኝ ገዥዎች ጥለዉት የሄዱት የኪነ-ሕንጻ አሻራ፤ በተለይ ደግሞ የኢጣልያ የሥነ ሕንጻ ባለሞያዎች ኢጣልያ ላይ በዝያን ዘመን ሊሰሩት የማይፈቀድላቸዉን የተለያዩ ሥነ ሕንጻዎች አስመራን ፒኮሎ ሮማ በማለት አስመራ ላይ የተለያዩ ሕንጻዎችን ሰርተዋል። አስመራ ከተማ በኪነ ሕንጻ ብቻ ሳይሆን በጽዳትዋ ፤ በአየር ፀባይዋና በተለያዩ ሁኔታዎች ከአፍሪቃ የታወቁ ከተማ በመሆንዋ አስመራ በዓለሙ የቅርስ መዝገብ መመዝገብዋ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ኩራት ነዉ ነዉ የምንለዉ»  

Eine afrikanische Insel der Architektur
በአስመራ የሚገኘዉ ሲኒማ ኢምፔሮ ምስል DW/Y.Tegenewerk

በዓለም መዝገብ የሰፈረዉ የአስመራዉ ዉብ ታሪካዊ ቅርስ የኤርትራ ብቻ ሳይሆን የዓለም ነዉ ያሉት በፈረንሳይ የኤርትራ አምባሳደር እና  የበዩኔስኮ የሀገሪቱ ቋሚ ተጠሪ ሐና ስምዖን በመጨረሻ ፤ «ቀደም ካለዉ ትዉልድ የተወረሱ ቅርሶች በክብካቤና ጥንቃቄ ሲያዙ ዓለም አቀፍ የቅርስ ሐዉልትነታቸዉ ሕያዉ ሲሆን አዎንታዊዉ ገፅታ ይንፀባረቃል። የዓለም ሕዝብ ቅርስ በመሆኑ የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ቅርሶቹ ጉዳት እንዳያገኛቸዉ ክብካቤ ማድረግ ይጠበቅበታል። በዩኔስኮ በኩል ርዳታ የሚገኝበትን ማፈላለግ ድረስመዝለቅ ይኖራል። ይህ የኤርትራ ቅርስ የኤርትራና የኤርትራዉያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ቅርስም በመሆኑ ጉዳት እንዳያገኘዉ ክትትል ማድረግ ያሻል። ሃላፊነቱን ይዛ በመጀመርያ ደረጃ መቆም ያለባት ግን ራስዋ ኤርትራ ናት።» ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

 

አዜብ ታደሰ  

ሸዋዬ ለገሠ