1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጥረት በኢትዮጵያ፥የምዕራባውያኑ ማስጠንቀቂያ

ዓርብ፣ የካቲት 16 2010

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የውጭ ሀገር መንግሥታት የተቃውሞ አጸፌታ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት የተከናወነው የሥራ ማቆም አድማ እና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሦ ጊዳዳ ከኦሕዴድ የተበረከተላቸው የግል ተሽከርካሪ ስጦታ መነጋገሪያ ኾነዋል።

https://p.dw.com/p/2tAtn
Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሣምንቱ እንደባለፈው ሣምንት አስደማሚ ነገሮች በፍጥነት የተከሰቱበት ባይኾንም፤ ለማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች እንደተለመደው የመነጋገሪያ ርእስ አልጠፋም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተገቢ አይደለም በሚል የተለያዩ ሃገራት ተቃውሞና ምክር መሠንዘራቸውም ያነጋገr ጉዳይነው። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንሥትር ማን ይኾናል የሚለውም በርካቶችን አነጋግሯል። በሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች በሕርዳር፣ በጎንደር፣ ወልዲያን በመሳሰሉ ቦታዎች ለሦስት ቀናት የተጠራው የሥራ ማቆም አድማ እና የእስረኞች መለቀቅም ሌላኛው ርእስ ነበር። 

ከሣምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ መካከል በኢትዮጵያ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የምዕራባውያኑ ተቃውሞ መጠናከር ይገኝበታል።  ለስድስት ወራት እንደሚቆይ የተነገረለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብአዊ መብቶችን ይገድባል ሲሉ ነው ምዕራባውያን ሃገራት የተቃወሙት። የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች፦ «አንድ የማረጋግጥላችሁ ነገር ቢኖር አሁን ሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በተሻለ ሠላም ላይ ናት» ብለዋል።

ይህን የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ ንግግርን የተሳለቀበት እሸቱ ሆማ ቄኖ ፌስቡክ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል። «ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአገሪቱ የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስና የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር ስለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ ለመስጠት በተጠራ ስብሰባ ላይ ምን ቢሉ ጥሩ ነው???? በአገሪቱ ምንም አይነት የሰላም መድፈርስም ሆነ የፀጥታ ችግር እንደሌለ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ» እሸቱ ከጽሑፉ ጋር የሳቅ ምልክት አያይዟል።

31 አንቀፆች እንዳሉት የተገለፀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያ፣ ዝርዝር በርካታ የሰብአዊ መብቶችን ይገድባል። የጀርመን የብሪታንያ እና የኖርዌይ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ አዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ትችት እና ተቃውሞዋቸውን ሠንዝረዋል።

አሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባውያን ሃገራት መንግሥታት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቃወማቸውን በተመለከተ ጋሻው ገብሬ ፌስቡክ ላይ ቀጣዩን ጽፏል።  አዋጁን የተቃወሙት «ሽብርተኝነትን አብሬያችሁ እዋጋለሁ እያለ ሕወሓት ሲዋሻቸው መኖሩን ዛሬ ሊረዱ በመቻላቸው ነው» ሲል ይነበባል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ፦ «የኢትዮጵያ መንግሥት የመሰብሰብ እና ሐሳብ መግለጽን ጨምሮ መሰረታዊ መብቶች የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የደረሰበትን ውሳኔ በብርቱ አንስማማበትም» ብሏል። የአሜሪካ ኤምባሲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በጽኑእ የተቃወመበት መግለጫን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መጠየቁን የሚገልጥ ጽሑፍም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተንሸራሽሯል።

Dr Workneh Gebeyehu äthiopischer Außenminister 23.01.2018
ምስል Getachew Tedla, HG

ከዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በተጨማሪ የምክር ቤት አባሉ ዳና ሮህራባቸርም አጭር ግን ጠንካራ መልእክት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስነብበዋል። አሜሪካዊው የምክር ቤት አባል ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ ጠቅሰው፥ «ሕወሓት ጨዋታው አክትሟል» ሲሉ ነው በትዊተር ገጻቸው የጻፉት። ይኽን አስተያየት በርካቶች ተቀባብለውታል።

በአውሮጳ ምክር ቤት የፖርቱጋል እንደራሴ የሆኑት ወይዘሮ አና ጎሜሽ በእንግሊዝኛ የትዊተር ጽሑፋቸው «ስለ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሳይቀሩ ተጨንቀዋል» ብለዋል። አያይዘውም የአውሮጳ ኅብረት «አይኔን ግንባር ያድረገው» ሲል «ጆሮ ዳባ ልበስ» ብሏል ሲሉ ኮንነዋል።

የትዊተር ጽሑፋቸውንም፦ ለአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን እና ምክር ቤት፣  በኅብረቱ የውጭ ጉዳይ እና የፀጥታ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ብሎም የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንቷ ፌዴሪካ ሞገሬኒ፣ ለኅብረቱ ዓለም አቀፍ ትብብር እና ልማት ኮሚሽነር ኔቨር ሚሚቻ፣ ለኅብረቱ የሰብአዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ስታቭሮስ ላምብሪንዲስ፣ ለኅብረቱ የውጭ ጉዳይ እና የፀጥታ አገልግሎት ክፍል፣ ለአውሮጳ ኅብረት የልማት ኮሚቴ ሊቀ-መንበሯ ሊንዳ ማክአቨን እንዲሁም ለኅብረቱ ሶሻሊስት እና ዲሞክራቶች ቡድን ፕሬዚዳንት ፒየር አንቶኒዮ ፓንዜሪ የትዊተር አድራሻቸውን አያይዘው መልክታቸውን አስፍረዋል።    

የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌውን በተመለከተ የአውሮጳ ኅብረት መግለጫ ማውጣቱን ሉሊት መስፍን ለወ/ሮ አና ጎሜዝ በሰጠችው የትዊተር መልስ፤ «ይኽን ደካማ መግለጫ አውጥተው የዕለቱን ሥራቸውን አጠናቀዋል። ታላቅ ውድቀት የአውሮጳ ኅብረት» ስትል ተችታለች። ከመልዕክቷ ጋር ያያያዘችው የአውሮጳ ኅብረት መግለጫ የተሰጠው በአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የፀጥታ ፖሊሲ ቃል አቀባዩዋ ካትሪን ሬይ ነው ።  

በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ለሦስት ቀናት የተጠራው ቤት የመቀመጥ እና የሥራ ማቆም አድማ የጀመረው ባለፈው ሰኞ ነበር። በባሕርዳር፣ በጎንደር፣ እና በወልዲያ ከተሞች መደብሮች ተዘግተው መዋላቸው፣ የመጓጓዛ አገልግሎት መቋረጣቸውን፤ ወጣቶችም መታሰራቸውን በተመለከተ በተለይ አዲስ ጋዜጣ የተባለው የትዊተር ገጽ ተከታታይ መልእክቶችን በፎቶግራፍ እያስደገፈ አቅርቧል። ፎቶግራፎቹ በከተማዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሱቆች በመደዳው እንደተቆለፉ፤ መንገዶችም ያለ ተሽከርካሪ ረጭ ብለው፤ ጥቂት ሰዎች ብቻ ይታይባቸዋል።

Äthiopien US Botschaft in Addis Abeba
ምስል U.S. Embassy/S. Dumelie

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወልቃይት ማንነት አስተባባሪዎች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ወጣት ንግሥት ይርጋ እንዲሁም እነ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ እና አሳምነው ጽጌም ከእስር መለቀቃቸዉ በርካቶችን አነጋግሯል።    

«ጀግናው ከሕዝቡ ጋር ተቀላቀለ! ጃሎ በልማ!» ሲል ለኮሎኔል ደመቀ አድናቆቱን የገለጠው አስናቀው አበበ ነው፤ ፌስቡክ ላይ። መልካም ሠላም ሞላ ከቪዲዮ ጋር ያቀረበው ጽሑፍ፦ «ጎንደር ጀግናዋን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ስትቀበል! እንወድሃለን ጀግናችን» በሚል ይነበባል። የቪዲዮ ምስሉ ላይ ነጭ መለስተኛ ክፍት የጭነት ተሽከርካሪን ከበው የሚጨፍሩ ሰዎች ይታያሉ።

የምንሊክ ቢትወደድ የፌቡክ መልእክት ደግሞ ከሁለት ፎቶግራፎች ጋር የተያያዘ ነው። በአንደኛው ፎቶግራፉ ላይ እንደነገሩ ከቆመች አጥር ወዲህ ኮሎኔል ደመቀ በእጃቸው አነስተኛ ነገር ይዘው ፈገግ እንዳሉ ይታያል። ከአጥሩ ወዲያ ከተሰባሰቡ ሰዎች መካከል በአዳፋ አለባበሱ እና በገጽታው የተጎሳቆለ፣ አንገቱ ትከሻው ስር የተቀበረ ግለሰብየኮሎኔሉን እጅ ጨብጦ ይታያል። ፈገግ ለማለት ሞክሯል። በአካባቢው ያሉት ሰዎች በፈገግታ ተውጠዋል።

«እነዚህ ሁለት ፎቶዎች የምር ልቤን ነክተውኛል» ይላል የምንሊክ ጽሑፍ። «ከወገራ ጎንደር ድረስ በእግሯ ኮሎኔልን ለመጠየቅ የተጓዘች እናትና በዝቅተኛ ሥራ የሚተዳደር ወንድማችን ያለውን ነገር ያለ ስስት ለኮሎኔል ደመቀ ሲያበረክት ነው» የሚል ጽሑፍም ይነበባል። ኮሎኔል ደመቀ በአንድ እጃቸው ጎስቋላውን ግለሰብ ጨብጠው በሌላ እጃቸው ለፎቶግራፍ አንሺው በፈገግታ የሚያሳዩት ሳንቲም ነው። «ሕዝብ ሲወድህ እንዲህ ነው» ሲል ይጠናቀቃል የልብ ስዕል የሚታይበት የምንሊክ ጽሑፍ። 

እስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሣትም እንዲፈቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ እየተደረገ ነው።

Frankreich Eurokorps-Soldaten hissen die EU-Fahne vor dem Parlament in Straßburg 2014
ምስል Getty Images/AFP/P. Hertzog

ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሰሞኑ መነጋገሪያ ርእስ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ተሿሚ ማን ይኾናል የሚለው ነው። በእርግጥ በጠቅላይ ሚንሥትርነት ማን ሊሾም እንደሚችል በውል ባይታወቅም የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እንደስሜታቸው እና የፖለቲካ ዝንባሌያቸው ስለቀጣዩ ጠቅላይ ሚንሥትር ጽፈዋል።

መቅደስ ጂ ትዊተር ላይ ባሰፈረችው አጭር መልዕክት፦ «ጠቅላይ ሚንሥተርነትም በቲፎዞ ሆነ እንዴ፤ ይቺ ሀገር ወዴት እየሄደች ነው? ለማለት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው» ስትል ስለቀጣዩ ጠቅላይ ሚንሥትር የሚሰጠው ግላዊ አስተያየት ላይ ከት ብላ መሳቅዋን በምስል እና በጽሑፍ ገልጣለች።

«ማንም ይኹን ማንም ኢትዮዽያን በጥሩ ሆኔታ የሚመራ ስው ነው የምንፈልገው» የዳንኤል ተክሉ የፌስቡክ አጭር አስተያየት ነው። «ማንም ይሁን ማን የሕዝብ ጥያቄ ይመልስ፤ መልካም የሥራ ጊዜ» የዖመር አስተያየት ሲኾን፤  ቢላል ሼካ «እኛ የምንፈልገው አትዮጵየን ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት የሚቀይራትን ነው» ብሏል።

«ስለ ሥርዓት ሲወራ ስለ ሰው ካወራን ተሳስተናል» ይላል ነጋሳ ኦዶ ዱቤ ፌስቡክ ላይ። «የሥርዓት ለዉጥ ጥያቄ በግለሰቦች ለዉጥ ሊፈታ አይችልም» ያለው ነጋሳ «ከሕዝባዊ መንግስት ያነሰ ነገር የኢትዮዽያ ሕዝብ አይቀበልም። ማንም ወደ ሥልጣን የሚመጣ ግለሰብ ወደ ዴምክራሲ የሚደረገዉን ጉዞ ለማምራት ነዉ መሆን ያለበት። ባለበት እየረገጥኩ አስቀጥላለሁ ቢል ሕዝቡ ያፈናጥረዋል» ሲል አስጠንቅቋል።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተነሱ ተጨማሪ ነጥቦች መካከል የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ለቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ያበረከተላቸው የግል ተሽከርካሪ ነው። ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹን እናቅርብላችሁ።  አስቻለው ምስጋናው «ኡፍ እንዴት ደስ ይላል» ሲል ዩሱፍ አብዱልአዚዝ «ዕውነት ትዘገያለች እንጂ አትሞትም» ብሏል። «ግሩም ነው ኦሕዴድ፤ እናመሠግናለን» በናንዛ ኃይሉ የተሰጠ አስተያየት ነው።

ዶክተር ነጋሶ ከቀድሞ ድርጅታቸው በሥጦታ የተበረከተላቸው ኒሳን ተሽከርካሪ እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። «ኦሕዴድ ለዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ላንድክሩዘር መኪና አበረከተ» ከሚል መልእክት ጋር ዶክተሩ ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ከጥቁር ላንድክሩዘር መኪና ፊት እና እውስጡ ኾነው የሚታዩበት ፎቶግራፍ በፌስቡክ እና ትዊተር ተዘዋውሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ