1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬፕለር፤ የመሬት ዘመድ አዲሷ ፕላኔት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 22 2007

የሥነ-ፈለክ እና የጠፈር ተመራማሪዎች ሰሞኑን አንድ አዲስ ፕላኔት ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። ፕላኔቷ ከመሬት ጋር ተመሳሳይነት አላት ተብሏል። ይኽች ፕላኔት ለሕይወት ተስማሚ የሆኑ ነገሮች እንዳሏትም ትንታኔ ተሰጥቷል። ፕላኔቷ ኬፕለር -452b ትሰኛለች። ስያሜውን ያገኘችው ኬፕለር ከተሰኘው ቴሌስኮፕ ነው።

https://p.dw.com/p/1G77Z
Nasa Forschung Kepler-452b
ምስል NASA/Ames/JPL-Caltech/T. Pyle via AP

ኬፕለር፤ የመሬት ዘመድ አዲሷ ፕላኔት

የሰው ልጅ ከምድር አልፎ በኅዋ ላይ እጅግ ርቀው የሚገኙ ፕላኔቶችን ሲያስስ ዘመናት ተቆጥረዋል። የሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ጠበብት የጨረቃን ድንጋይ ከስክሰው፥ ወደ ማርስ ማማተር ከጀመሩም ሰነባብተዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክዋክብት የተሰባሰቡባቸው ፀሐያዊ ጭፍሮች(ጋላክሲዎች)ላይ ማተኮር ከጀመሩ ደግሞ ምዕተዓመታት ተቆጥረዋል። ጠበብቱ አንድ ቀን የሰው ልጅን ከምድር ውጪ በሌሎች ፕላኔቶች ላይ ማኖር ሳይቻል አይቀርም በሚል መላ ምትም ነው ለዘመናት መማሰናቸው። ከሰሞኑ ታዲያ አንድ ከምድር ጋር ተመሳሳይ እንደሆነች የተነገረላት ፕላኔት መገኘቷ ይፋ ሆኗል። በዚህች ፕላኔት ውስጥ ለሕይወት እጅግ አስፈላጊው ውኃ እንደሚገኝም ሣይንቲስቱ ተናግረዋል። ኬፕለር 452b፤ የመሬት ዘመድ አዲሷ ፕላኔት

እንደ ሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪዎች ከሆነ ምድር ከምትገኝበት ፀሐያዊ ጭፍሮች(ጋላክሲ)ውጪ ሰሞኑን ሣይንቲስቶች ኬፕለር 452b የተባለች ከምድር ጋር የምትመሳሰል ፕላኔት ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። አዲሷ ፕላኔት የተገኘችው ፀሐያዊ ጭፍሮቹበፈጠሩት ቅርጽ የተነሳ «ዳክዬ» የሚል ስያሜ በተሰጠው የከዋክብት ስብስብ መካከል ነው።

Flash-Galerie Veil Nebel in der Milchstraße
ምስል picture-alliance/dpa

ይኽች አዲስ ፕላኔት የተገኘችው ኅዋ ላይ በሚሽከረከር የሩቁንአጉልቶበሚያሳይ ልዩ ግዙፍመነጽር(ቴሌስኮፕ)አማካኝነት ነው። ፕላኔቷ ከምንኖርባት ምድር ጋር ዝምድናዋ ልክ እንደ የአክስት ልጅ አይነት ነው ተብሏል። ኬፕለር 452bፕላኔት «ለሕይወት ተስማሚ» ናት ሲሉ የጠፈር ተመራማሪዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ወደኅዋ የተላከችው እና ኬፕለር 452b የተሰኘውን ፕላኔት ያገኘችው ኬፕለር ቴሌስኮፕ ተልዕኮ ዋና አስተናባሪ ጆን ግሩንስፌልድ አዲሷ ፕላኔት ከምድር ጋር እንደምትቀራረብ ይፋ አድርገዋል።

«ዛሬ ይፋ የምናደርገው ምድራችን ከምትገኝበት ፀሐያዊ ጭፍሮች(ጋላክሲ)ውጪ በሌላ ፀሐያዊ ጭፍሮችውስጥ የምትገኝ፤ ዝምድናዋ የምድር የአክስት ልጅ ሊባል የሚችል አዲስ ፕላኔት ማግኘታችንን ነው። ይኽ ግኝት እስካሁን ባለን መረጃ የተመሠረተ ነው፣ እስካሁን የሚለው ላይ ሆን ብዬ ነው ያተኮርኩት፤ ምክንያቱም በኬፕለር የተሰበሰበው መረጃ እጅግ የዳበረ ከመሆኑ ባሻገር የሣይንሱ ማኅበረሰብ ይኽን መረጃ በመተንተን ወደፊት በርካታ ግኝቶች ላይ መድረስ ይችላል። ሆኖም ግን ዛሬ ይፋ ማድረግ የምንሻው እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ከምድር ጋር ተቀራራቢነት ያላት መንታ ፕላኔት ማግኘታችንን ነው። »

የኬፕለር 452b ውጪያዊ አካል ምናባዊ ገጽታ ምንነት ገና ሙሉ ለሙሉ አልተብራራም። ሆኖም ጠቢባኑ ብርሃንን በመተንተን ፕላኔቷ ምናልባትም ከእሳተ-ጎመራ የተገኘ አለታማ ቋጥኞች ሳይኖራት አይቀርም ብለዋል። የኬፕለርን ገጽታ በቦታው ተገኝቶ ለማጥናት እጅግ አዳጋች እና በአሁኑ ወቅት የማይሞከር ያደረገው ፕላኔቷ የምትገኝበት ርቀት ነው። ኢትዮጵያዊው የሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን ደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፊዚክስ ያስተምራሉ። የሰው ልጅ አሁን በእጁ የሚገኘውን ስነቴክኒክ ተጠቅሞ ኬፕለር 452bፕላኔት ጋር ለመድረስ 26 ሚሊዮን ዓመት ይፈጅብታል ብለዋል።

ከግራ ወደ ቀኝ ሦስተኛው፥ የናሣው ሣይንቲስት ጆን ግሩንስፌልድ
ከግራ ወደ ቀኝ ሦስተኛው፥ የናሣው ሣይንቲስት ጆን ግሩንስፌልድምስል Reuters

በሰአት 138,000 ኪሎ ሜትር መክነፍ በሚችለው በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ፈጣኑ እናት መንኰራኰር የሚደረግ ጉዞ እንኳን ኬፕለር 452b ጋር ለመድረስ የ11 ሚሊዮን ዓመትን ያስጠብቃል ተብሏል።

ተመራማሪው አቶ ጌታቸው መኮንን በቅርቡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለማግኘት የሚያስችላቸውን ጥናት የሚያኪያሂዱት ርእደ-ከዋክብት ላይ ነው። መሬት ሲንቀጠቀጥ እና ውስጡ ሲናጥ ርእደመሬት እንደሚባለው ሁሉ ከዋክብትም ውስጣቸው ይርዳል ብለዋል። ተመራማሪው አቶ ጌታቸው መኮንን በአሁኑ ወቅት የሚያኪያሂዱት ጥናት የከዋክብቱን ውስጣዊ ትርታ በማድመጥ ውስጣቸው ከምን እንደተሠራ መተንተን ነው። ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ሣይንቲስት አዲሷ ፕላኔትን ስላገኘው ኬፕለር ቴሌስኮፕ ምንነት ያብራራሉ።

አዲሷ ፕላኔት የ6 ቢሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠረች እንደሆነ እና በውስጧም ውኃ ሊገኝበት እንደሚችል ተገልጧል። ኬፕለር 452b ምድር ከምትገኝበት ፀሐያዊ ጭፍሮች(ጋላክሲ)ውጪ ብትገኝም ለሕይወት ተስማሚ እንደሆነች ሣይንቲስቱ ይፋ አድርገዋል።

Hubble Reparatur an Bord des Space Shuttles
ምስል picture-alliance/dpa/Nasa

በነገራችን ላይ ጠበብቱ አዲሱን ፕላኔት አገኘን፤ ምናልባትም ለሕይወት ተስማሚ ሳትሆን አትቀርም ቢሉም የአሁን ዘመን ሰው ግን አሁን ባለው ስነቴክኒክ ታግዞ ኬፕለር 452b ፕላኔት ላይ መድረስ አይችልም። «ወደፊት ግን » አሉ ተመራማሪው አቶ ጌታቸው መኮንን «ወደፊት ግን የሰው ልጅ እጅግ በርቀት ላይ ወደሚገኙ ፕላኔቶች መጓዙ አይቀርም የሚል ተስፋ አለኝ»። የሰው ልጅ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን እየከሰከሰ ከዋክብቱን እና ጠፈርን በማጥናት ላይ የሚገኘውም ያንን ተስፋ ሰንቆ እንደሆነ ተናግረዋል ሣይንቲስቱ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ