1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጋምቤላ የታገቱትን የማስመለሱ ጥረት

Merga Yonas Bulaሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2008

ከሁለት ሳምንት በፊት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ኢትዮጵያ ሰርገው በመግባት 182 ሰዎችን ገድለው 108 ሴቶች እና ህፃናትን አግተዉ መዉሰዳቸዉ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት የታገቱትን ለማስለቀቅ የጦር ሰራዊቱ ወደ ደቡብ ሱዳን መዝመቱን እና ጥቃት ፈጻሚዎቹን መክበቡን አስታውቆ ነበር።

https://p.dw.com/p/1Iggi
Karte Äthiopien Südsudan Gambella DEU

[No title]

ባሳለፍነዉ ቅዳሜ ከታገቱት መካከል 32 ህፃናት መገኘታቸዉን በደቡብ ሱዳን የቦማ ግዛት አስተዳዳሪዎች መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።ህጻናቱ ወደ ቦማ ግዛት ዋና ከተማ ፒቦር፤ ከዚያም ወደ ጁባ ከተወሰዱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ የቦማ ግዛት ተጠባባቂ አስተዳዳሪ ተናግረዋል። ቀሪዎቹ ህጻናትም እየተፈለጉ መሆኑን አስተዳዳሪው ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።


አካባቢዉ ሰፊ እና በረሃ ከመሆኑ አንፃር በቀላሉ የታገቱትን ለመመልስ እንደሚያስቸግር መገለፁን እና የኢትዮጵያ መንግስት ከባድ ርምጃ ከወሰደ የታገቱት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ እየተፈለጉ መሆናቸዉን አቶ አበበ አይነቴ፣ በኢትዮጵያ የሰላም እና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «ከትላንት ወዲያ ጀምሮ እየወጣ ያለዉ መረጃ፣ እንዳልከዉ 32 ህፃናት መገኘታቸዉን ነዉ። የተቀሩት የት ነዉ ያሉት ? ወዴት ነዉ የሚሄዱት የሚለዉን በተመለከተ ከመንግስት በኩል እስከ አሁን 32 መገኘታቸዉን ኦፊሽያል የተገለጻ አይመስለኝም። ባጠቃላይ ግን ሂደቱ መንግስት ከመጀመሪያዉ ጀምሮ የገባዉን ቃል ስላለ ሃላፊነቱን ወስዶ እነዚህ ዜጎች የደረሱበት፣ ያሉበት ሁኔታ አጣርቼ ለማስመለስ ጥረት አደርጋለሁ ብለዉ የገባዉን ቃል እንግዲህ ይፈፅማል ተብሎ ነዉ የሚታሰበዉ። ከደቡብ ሱዳን ጋርም በትብብር የሚሰራ በመሆኑ፣ በዚህ ሁኔታ ያለ ነዉ የሚመስለዉ።»


የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት የታገቱትን ለማስለስ በጋራ እየሰሩ መሆናቸዉን እና ጥረቱም ጥሩ ውጤት እንዳስገኘ በፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ ወርቁ መናገራቸው ይታወሳል። ሁለቱም አገራት የፀጥታ ስምምነት እንዳላቸዉ የሚናገሩት አቶ አበበ አይንቴ ያንን ስምምነት የሁለቱንም አገሮች በሚጠቅም መልኩ እና የደረሰዉን ጉዳት ለመቀልበስ ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸዉ ይናገራሉ። «ዲፕሎማሲው በሁለቱም አገር ድንብር ላይ ስለሆነ ይህ ነገር የተከሰተዉ ከሁለቱም መንግስታት ጋር ባለዉ ሂደት ላይ ነዉ። ሊኖር የሚችለዉም ወታደራዊ እና የሃይል ርምጃ ነዉ፣ የታገቱትን እና ዘርፎ የሄዱትን ንብረት የማስመለስ ነገር ነዉ እና ህብረተሰቡም የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች ሆነ መንግስት ቀደም ብሎ ችግሩ እንደተከሰተ ወድያዉኑ የገባዉን ቃል መተግበር አለበት። »>

UNHCR Flüchtlingslage in Gambella Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher


አከባቢዉ በረሃ እና ሰፊ ከመሆኑ አንፃር በየጊዜዉ ለህብረተሰቡ መረጃ ማቅረብ እንደሚከብድም አቶ አበበ አክለው ገልፀዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ