ከጋምቤላ የታገቱትን ሕፃናት የመመለሱ ጉዳይ
ሐሙስ፣ ግንቦት 25 2008ከመጀመርያዉ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሃይል ከመጠቀም ይልቅ የታገቱትን ሕፃናት በድርድር እንድሚመለስ ከመናገር ወደ ኋላ አላለም። እስከ አሁን አንዴ በአስር አንዴ በሰላሳዎቹ ከስር ከስር ወደ 63 ሕፃናት እንዲመለሱ ተደርገዋል። ቀሪዎቹንም ታጋቾች መልሶ ለማምጣት ፍለጋዉ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እና በሁለቱም ሃገራት መካካል የተደረገዉ ስምምነት ሕፃናቱን መልሶ ለማምጣት እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባሳለፍነዉ ዓርብ የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ጋትላኡክ ቱትን ጠቅሶ ዘግቦታል።
የተመለሱት ሕፃናት ሁኔታን አስመልክተው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃልአቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለዶይቼ ቬሌ እንዳስታወቁት፣ ሕፃናቱን መመለስ የቻሉት በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ ማህበረሰብ እና ከመንግስታቸዉ ጋር ባደረጉት ድርድር ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ከድርድሩ ዉጭ የተጠቀመበት ሌላ ርምጃ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ተወልደ ካለኃይል ተግባር ልጆቹን በሰላም ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ሁሉንም ታጋቾች ለመመለስ ጊዜ የወሰደበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? በሚል በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ገፅ ላይ ያወያየናቸው አስተያየት ሰጭዎች መንግስት ጉዳዩን ችላ ብሏል የሚለውን ሀሳብ አጉልተዋል። አንዳንዶች መንግስት ሕፃናቱን ለመመለስ የጀመረው ድርድር እና እያደረገው ያለው ጥረት አበረታች ነዉ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ መንግስት ተጨማሪ የወታደር ሃይል በማስገባት ንፁኃኑን ሕፃናትን መመለስ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
መርጋ ዮናስ
አርያም ተክሌ