1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ

ሰኞ፣ ጥር 15 2009

በቆዳ ቀለማቸው ብቻ ሳይሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከባራክ ኦባማ ጋር በብዙ ነገሮች አይመሳሰሉም። አንዳቸው ስለ ሌላው የሰጧቸው አስተያየቶችም ቢሆኑ የዛኑ ያክል ተቃርኗቸውን ፍርጥርጥ አድርገው የሚያሳዩ ነበሩ።

https://p.dw.com/p/2WGky
USA Amtsübernahme Trump und Obama
ምስል Reuters/C. Barria

የዶናልድ ትራምፕ ዩ ኤስ አፍሪቃ

ዶናልድ ትራምፕ ቃለ-መኃላ ፈፅመው ፕሬዝዳንት ከተባሉ በኋላ ያሰሙት ንግግርም በጭብጡም ሆነ አቀራረቡ እጅጉን ልዩ ነበር። «ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ነገር አሜሪካ ትቅደም ይሆናል።  በንግድ፤ በቀረጥ፤በስደት፤ በውጭ ጉዳይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ አሜሪካዊ ሰራተኞች እና አሜሪካዊ ቤተሰቦች እንዲጠቅሙ ተደርገው ይወሰናሉ።» በየንግግራቸው ጣልቃ ፋታ እየወሰዱ የታዳሚዎቻቸውን ጭብጨባ ይሹ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ድኅነት እና ወንጀል የተንሰራፋባት አድርገው ጭምር ስለዋታል። «አሜሪካውያን ለልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት ቤት ለቤተሰቦቻቸው ሰላማዊ የመኖሪያ አካባቢ ለራሳቸው ደግሞ ጥሩ ሥራ ይሻሉ። ለበርካታ ዜጎቻችን እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። በከተሞች እናቶች እና ልጆቻቸው በድኅነት ተጠፍረዋል። የዛጉ ፋብሪካዎች በአገራችን እንደ ሐውልት ተገትረዋል።  በርካታ ገንዘብ የፈሰሰበት የትምህትር ሥርዓት ወጣት እና ውብ ተማሪዎቻችንን እውቀት አልባ አድርጓቸዋል። ደግሞ ወንጀሉ! ወሮበላዎቹ፤ አደንዛዥ እፁ.... ልብ ያልተባሉ እምቅ አቅም የነበራቸው ዜጎች ህይወት ቀጥፈዋል።»ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በንግግራቸው አገራቸውን ከፋፍሏል ያሉትን ቁስል ሊያክሙ ቃል ገብተዋል። የበዓለ ሲመታቸው ንግግር እንደ ቀደሙት አንድነትን የሚሰብክ እና ከወገንተኝነት የጸዳ መሆኑ ቀርቶ ጨለምተኝነት ተጭኖታል ብለዋል-ተቺዎቻቸው። 

Washington Amtseinführung Trump Parade
ምስል Picture-Alliance/AP Photo/E. Vucci


ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ኃውስ ከገቡ ሶስት ቀናት ቢሆናቸውም ገና ካሁኑ ተቃውሞ በዝቶባቸዋል። ከአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ጋር ያላቸው ግንኙነትም ለውጥ አላሳየም። በበዓለ ሲመታቸው የታደመውን የሕዝብ ቁጥር ከባራክ ኦባማ በዓለ ሲመት አኳያ እያነፃጸሩ ማነሱን የዘገቡ ጋዜጦች የፕሬዝዳንቱ ትንኮሳ ገና በጠዋቱ ደርሷቸዋል። ቃለ-መኃላ ከፈጸሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገሪቱ ማዕከላዊ የስለላ ቢሮ (CIA) ብቅ ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ዋሾ ናቸው ያሏቸው የመገናኛ ብዙኃን እጅ ከፍንጅ ይዘናቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

«ዛሬ ማለዳ ከመኝታዬ ተነስቼ አንዱን የቴሌቭዥን ጣቢያ ስከፍት በበዓለ ሲመቱ ላይ ብዙ ሰው እንዳልነበረ ባዶ ቦታ መርጠው ሲያሳዩ ተመለከትኩ። ንግግር አድርጊያለሁ። በወቅቱ በአካባቢው አንድ ሚሊዮን ወይም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ያህል ሰው ያለ ይመስል ነበር። እነርሱ ግን ማንም ሰው ያልቆመበትን መርጠው እያሳዩ ነው። የመጣው ሁለት መቶ አምሳ ሺ ሰው ነው እያሉ ነው። ያም ቢሆን መጥፎ አይደለም። ነገር ግን ሐሰት ነው። በገነባንው መድረክ ዙሪያ ብቻ ሁለት መቶ አምሳ ሺ ሰው ነበር። እና ይዘናቸዋል። እጅ ከፍንጅ ይዘናቸዋል። ለዚህም ትልቅ ዋጋ ይከፍላሉ።» 

ዶናልድ ትራምፕ ገና በጠዋቱ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ብቻ አይደለም። ከኒው ዮርክ እስከ ዋሺንግተን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ 5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የዶናልድ ትራምፕን በዓለ ሲመት ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል። እህቶች በሚል መፈክር በ50 ግዛቶች የተካሔዱት እና በአብዛኛው በእንስቶች በተመሩት የተቃውሞ ሰልፎች የእንስቶችን ጉዳዮች ለማሰማት የታቀዱ ነበሩ። በሒደት ግን በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር መገፋት የተሰማቸው ሁሉ ተቀላቅለውታል።  «ዶናልድ ትራምፕን እና እርሳቸው የቆሙለትን ሁሉ እንቃለሁ። ፕሬዝዳንት ለመሆን ብቃቱም ሆነ በራስ የመተማመን መንፈሱ የላቸውም። ወፈፌ እና ራስ ወዳድ ናቸው።ጥላቻዬን ለመግለፅ እዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረግ ውጪ ሌላ መንገድ የለኝም።» ይላሉ በሰልፉ የተካፈሉ ወይዘሮ።

Washington Women's March Trump Proteste
ምስል DW / F. Kroker


የመጀመሪያው ተቃውሞ ቅዳሜ ዕለት ከዋይት ሐውስ ደጃፍ እዚያው ዋሽንግተን ዲሲ ሲጀመር ኹከት አላጣውም። ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰልፈኞች  በተሳተፉበት ተቃውሞ ዶናልድ ትረምፕ በሕገ-ወጥ ስደተኞች ላይ እወስዳለሁ ያሉትን እርምጃ ተቃውመዋል። ፕሬዝዳንቱ በጸረ-ሽብር ዘመቻ ሰበብ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለመመዝገብ ባቀዱት ውጥንም ተወግዘዋል። የከባቢ አየር ለውጥ ላይ ባላቸው አቋም የጤና መድን ማሻሻያን ለመከለስ የወጠኑት ውጥን አስተችቷቸዋል።  ማይክል ሙርን የመሰሉ የፊልም ባለሙያዎች፤ አንጌላ ዴቪስን የመሰሉ ሥመ-ጥር የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች እንደ ማዶና ያሉ ሙዚቀኞችም ነበሩበት።  «ይኸንን አንድነት በመመልከቴ እጅግ ተገርሚያለሁ፤ተደስቻለሁ። ትራምፕ ሊከፋፍሉን አይችሉም። አንድጋ የተሻልን ነን።» በእንስቶች ተጀምሮ የዶናልድ ትራም ተቺዎችን ሁሉ ያሰሰበው ይኸ ተቃውሞ የት ድረስ እንደሚዘልቅ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። አዲሱ አስተዳደር የሚደርሱበትን ውግዘቶች ለመቀነስ የሚወስደው እርምጃም ያሳሰባቸው አልጠፉም። ዶናልድ ትራምፕ ግን ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት የምርጫው ዕለት ወዴት ነበሩ ሲሉ ለመሳለቅ ሞክረዋል።


ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫ ዘመቻቸው ጀምሮ የባራክ ኦባማ አስተዳደር የጀመራቸውን ክንውኖች ሁሉ እንደሚቀለብሱ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ሁሉም ግን ቀላል አይመስሉም። ፕሬዝዳንቱ የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ለመቀበል ያሳለፉትን ውሳኔ ታላቅ ስህተት ብለውታል። ኢራን ከልዕለ ኃያላኑ ጋር የተፈራረመችው የኑክሌር መርኃ-ግብር ሥምምነት እና የትራንስ አትላንቲክ ውል ዶናልድ ትራምፕ አብዝተው ከሚተቿቸው መካከል ይገኙበታል። 195 አገሮች የተፈራረሙት እና ባራክ ኦባማ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት የፓሪሱ የከባቢ አየር ሥምምነትም የዶናልድ ትራምፕ ጥላ የተጫነው ሌላ ዓለም አቀፍ ውል ነው። ሰውየው የከባቢ አየር ለውጥ የሚባል ጨርሶ የለም ባይ ናቸው። በእርግጥ ሥምምነቱ ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛ አገር ጋር የገባችው የተናጠል ውል ባለመሆኑ ዓለም አቀፍ ተግባራዊነቱን ለመቀልበስ ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይኖራቸው ይችላል። ሁሉን አውቃለሁ ባዩ ዶናልድ ትራምፕ በውጭ ጉዳይ በኩል ግልጥ ያለ ፖሊሲ የላቸውም እየተባሉ ይወቀሳሉ። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን ፣ ኔቶ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የሰነዘሯቸው አስተያየቶች የዓለም መሪዎች ሰውየውን በጥርጣሬ እንዲመለከቷቸው አስገድዷቸዋል። ትራምፕ መንግሥታቸውን ሲያዋቅሩ የመረጧቸው የካቢኔ አባላት በሙሉ የአመራር ክህሎትም ሆነ ልምድ የላቸው የሚል ሥጋት ፈጥሯል።  


አፍሪቃ ሆይ ወዴት ነሽ?

ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን ስለ አፍሪቃ ያላቸው እይታ ምስጢር ነው። የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደፃፈው የትራምፕ የቅርብ ሰዎች ለአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ፕሬዝዳንቱ ስለ አፍሪቃ ያላቸው አቋም በጥርጣሬ የተሞላ ነው የሚል ሥጋት የሚያጭር ነው። ዶናልድ ትራምፕ የውጭ እርዳታ እና ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪቃ ስላላት የጸጥታ ጥቅም ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ጋዜጣው ፅፏል። ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው ለአፍሪቃ እምብዛም ትኩረት አልሰጡም። ትራምፕ ተቀናቃኛቸውን በነገር ለመጎንተል  በሊቢያዋ ቤንጋዚ ከተማ ተፈፅሟል ያሉትን ሥህተት ከመንቀስ ያለፈ ያሉት ነገር የለም። አፍሪቃውያኑም በትራምፕ አሜሪካ አህጉራቸው ችላ እንደምትባል የምርጫው ውጤት ከታወቀበት ዕለት ጀምሮ ሳይገነዘቡት አልቀረም። ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ናፍታሊ ማውራ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ለይቶ የመጠበቅ ሥልት ለአፍሪቃ አዋጪ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።«በግሌ ለአፍሪቃም ይሁን ለኬንያ የሚያናድድ ውጤት ነው። አፍሪቃ ለእርሳቸው ትኩረት የሚሰጣት አህጉር አይደለችም። በምረጡኝ ዘመቻቸው የአሜሪካን ኩባንያዎችን መጠበቅን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ግለሰብ ናቸው።» 

USA US- Africa Business Forum in New York
ምስል Reuters/K. Lamarque

ከኬንያዊ አባት የሚወለዱት ባራክ ኦባማ በሥልጣን በነበሩባቸው ሥምንት አመታትም ቢሆን አፍሪቃ ከዩናይትድ ስቴትስ ያገኘችው ጥቅም ያን ያክል አልነበረም። በመጀመሪያዎቹ አራት የሥልጣን አመታት አህጉሪቱን ችላ ብለው የከረሙት ኦባማ በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ወደ ጋና አቅንተው ሥልጣን የሙጥኝ ያሉ መሪዎችን በቃችሁ ብለው ነበር።  የኦባማ ምክርም እንበለው ቁጣ ግን ለአህጉሪቱ የበጀው ነገር አልነበረም። እርሳቸው ሲመረጡ በደስታ የተቀበሏቸው አፍሪቃውያን ዛሬም የተቀየረላቸው ነገር የለም።  ባራክ ኦባማ በማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ እና ፓወር አፍሪቃ በተሰኙ ሁለት እቅዶቻቸው አህጉሪቱን ለመጥቀም መሞከራቸው ግን አልቀረም። ኦባማን አብዝተው ሲዘልፉ የተደመጡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪቃ ምን ይዘው እንደሚመጡ እስካሁን በግልጥ አይታወቅም። የሊቢያ ፖለቲካዊ ቀውስ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ከሚፈተኑባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑ ግን አይቀሬ ነው። የሶርያ ትርምስ፤ሩሲያ እና ቭላድሚር ፑቲን፤ዘመናት የተሻገረው የእስራኤል እና ፍልስጤም ውጥንቅጥ እና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዶናልድ ትራምፕ እና የአመራር ክህሎታቸውን ይፈትናሉ። ትራምፕ ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን በመጪው ሳምንት ከብሪታኒያዋ ጠቅላይ ሚኒሥትር ቴሬሳ ሜይ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ይጀምራሉ። እስከዚያው ግን አሜሪካ ትቅደም ብለዋል!


እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ