1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እንደማሸንፍ አውቅ ነበር» አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ

ዓርብ፣ የካቲት 12 2013

በቅርቡ ፈረንሳይ ሀገር በተካሄደው የዓለም አትሌቲክ የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም ይሁን በሴቶች ውድድር ፤ ድል ቀንቷቸዋል። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን በሰሞኑ ሩጫ የ 1500 ሜትር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ያስመዘገበችው ጉዳፍ ፀጋይ ናት።

https://p.dw.com/p/3pZ25
Gudaf Tsegay | äthiopische Läuferin Leichtathletik
ምስል Chai v.d. Laage/imago images

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ

ጉዳፍ ፀጋይ የመካከለኛ እና ረዥም ርቀት አትሌት ናት። የ 24ቷ  ወጣት በውድድር ሜዳ ላይ ስትሆን በአእምሮዋ የሚመላለሰው አንድ ነገር ብቻ ነው። «ከሰዓት ጋር መሮጥና ማሸነፍ »ትላለች።  ይህንንም በቅርቡ በፈረንሳይ ሀገር በተካሄዱ የ 800 ሜትር እና የ1500 ሜትር የዓለም አትሌቲክ የቤት ውስጥ ውድድሮች ለማሳየት ችላለች። ወጣቷ በቅርቡ ባካሄደቻቸው ውድድሮች ሌላም ስኬት ነበራት። በ 1500 ሜትር ለሰባት አመታት በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን  የዓለም ክብረ ወሰን በ 2  ሴኮንድ በማሻሻል  3 ደቂቃ ከ 53 ሰከንድ በመሮጥ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ችላለች። ክብረ ወሰኑንን እንደምታስመዘግብም አስቀድማ ርግጠኛ ነበረች።  « በደንብ ጠንክሬ እየተለማመድኩ ነበር ፣ ለኦሎምፖክ ማጣሪያም የሮጥኩት ፈጣን ሰዓት ነው። ያኔ ሪኮርዱን እንደምሰብር አውቅ ነበር» ትላለች ጉዳፍ ።  በልምምድ ወቅት ጥሩ ውጤት ብታስመዘግብም ወደ ፈረንሳይ ከመጓዣ ጥቂት ቀናት በፊት የጤና ችግር ገጥሟት ስለነበር ስጋት ላይ ነበረች። « እዛ ስሄድ ነው አንድ ቀን ሲቀረኝ ደህና የሆንኩት፤ እና ሪከርዱን እንዳላጣው ፈርቼ ነበር»

ታድያ ወጣቷ የውድድር ሜዳ ውስጥ እንደገባች ወዲያው ከሁለቱ አሯሯጮቿ ወይም ፔስሜከር አትሌት ሂሩት መሸሻ እና ኬንያዊቷ ጆሴፌኒት ጋር በመሆን ከሌሎቹ ሯጮች መለየት ጀመረች።  ግን የዓለም ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ላቀደችው ጉዳፍ ሩጫው ቀዝቅዞባት ነበር ። በመጨረሻም ቀሪዎቹን ሦስት ዙሮች ብቸዋን በራሷ ፍጥነት ገሠገሠች።  ወጣቷ  ለ ሀገሯ እስካሁን ሶስት ሜዳሊያዎች አግኝታለች። ከሁሉም ሩጫዎች ደግሞ ለ1500 ሜትር ሩጫ ልዩ ፍቅር አላት።  ግን ሌላም ርቀት ትሞክራለች።  በ 1500 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ካስመዘገበች ከአምስት ቀናት በኋላ እዛው ፈረንሳይ ውስጥ ቫል ዴ ሩዌል በተካሄደው  የ 800 ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ አንደኛ ብቻ ሳይሆን የወጣችው፤ እስካሁን ኢትዮጵያውያን ከሮጡት ቀዳሚ የሚባለውንም ውጤት አስመዝግባለች ። ከዓለም ደግሞ የ9ኛውን ቦታ ይዛለች። 

Gudaf Tsegay | äthiopische Läuferin Leichtathletik
ምስል Chai v.d. Laage/imago images

አሰልጣኟ ህሉፍ ይደጎ ጉዳፍ ምን አይነት አትሌት እንደሆነች ሲገልፁ፣ « ሀገሯን የምትወድ ፣ጠንካራ፣ ሙሉ ልምምዷን ሳትሸፍን ወደቤት የማትመለስ አትሌት ናት» ሲሉ ይገልጿታል። እንጦጦ ሰንዳፋ እና ሱሉልታ በብዛት የምትልማመድባቸው ቦታዎች ናቸው። እሷምሆኑ አሰልጣኟ ግን የሚኖሩት አዲስ አበባ ከተማ ነው።  በቪዛ ምክንያት ወደ ፈረንሳይ ያልተጓዙት አሰልጣኟ በኮቪድ 19 የተነሳ ቪዛ የለም ስለተባለ ለፈረንሳይ ቪዛ አልጠየኩም ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት አትሌቶቹም « በነጭ ወረቀት ነው የተጓዙት ፈረንሳይ ከገቡ ነው ቪዛ ያገኙት» ይላሉ። ይህ ባይሆን ኖሮ ጉዳፍም እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ አሰልጣኟ አብረዋት ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው ቢሆን ኖሮ ምኞቷ ነበር። « ለሪኬርድ አስቤም ስለሄድኩ አለመምጣቱ ትንሽ ቅር ብሎኝ ነበር። ቢሆንም ግን ያለኝን ስላሳካሁ ደስ ብሎኛል። » ጉዳፍ ወደ ሩጫ ስትገባ እሷን ማሰልጠን የጀመሩት አሰልጣኝ ህሉፍ ከጉዳፍ ሌላ ስኬታማ የሆኑ ሌሎች አትሌቶችም አሏቸው። ጉዳፍ አብዛኛው ጊዜዋን ጠዋት እና ከሰዓት በልምምድ ነው የምታሳልፈው ከዛ ውጪ መዝሙር መስማት እና ፊልም ማየት ያስደስታታል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ