1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ የአሜሪካን ኮንግረስ አፀደቀ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 2010

ኤች አር 128 የተባለው የውሳኔ ሀሳብ አስገዳጅ ህግ ባይሆንም የሀገሪቱ መንግስት ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ጫና ይፈጥርበታል ተብሎ ተገምቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት ግን የውሳኔ ሀሳቡ “ከመግለጫነት ባለፈ ምንም አይነት ህጋዊ ትርጉምና አንዳች ተጽዕኖ የለውም” ሲል በዛሬው መግለጫው ውድቅ አድርጎታል፡፡

https://p.dw.com/p/2vrIT
USA Kapitol in Washington
ምስል picture-alliance/dpa/A. Shelley

የአሜሪካ ኮንግረስ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት እና የዲሞክራሲ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ኤች አር 128 ተብሎ የሚታወቀውን የውሳኔ ሀሳብ ትላንት ለሊቱን አጸደቀ፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲጣሩ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና አፋኝ የተባሉ ሕግጋት እንዲሻሩ ይጠይቃል፡፡ 
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩ እና ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ የመብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይም ማዕቀብ እንዲጣል ይሻል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ እንዳይጸድቅ የኢትዮጵያ መንግስት ግፊት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን በሚመለከት ትላንት ያጸደቀው ኤች አር 128 የተሰኘ የውሳኔ ሀሳብ “ወቅታዊ እና ያልተገባ ነው” ሲል አጣጣለው፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲጣሩ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና አፋኝ የተባሉ ሕግጋት እንዲሻሩ ይጠይቃል፡፡ 

 ኤች አር 128 “የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ የጋራ ጥቅም እንዲሁም በመሬት ላይ ያሉ የተለወጡ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና አፍራሽ ነው” ሲልም ተችቶታል፡፡

ከብዙ ማግባባት እና ግፊት በአሜሪካ ኮንግረስ የጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩ እና ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ የመብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይም ማዕቀብ እንዲጣል ይሻል፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት በዛሬው መግለጫ “የኮንግረሱ የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያ መንግስት እስረኞችን በመፍታት፣ ሰፊ ፖለቲካዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማካሄድ እየወሰዳቸው ያሉትን በጎ እርምጃዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

“ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ትኩረት እንደምትሰጥና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ረገድ በጋራ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች” ያለው መግለጫው “የአሜሪካ ኮንግረስም ይህንን በጎ ግንኙነት ከግምት በማስገባት አካሄዱን እንዲያስተካክል” ምክር ያለውን ለግሷል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ እንዳይጸድቅ የኢትዮጵያ መንግስት ግፊት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ተስፋአለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ